በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃስሞናውያንና ትተው ያለፉት ቅርስ

ሃስሞናውያንና ትተው ያለፉት ቅርስ

ሃስሞናውያንና ትተው ያለፉት ቅርስ

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአይሁድ እምነት በሕዝቡ ላይ የበላይ ለመሆን ይሻኮቱ በነበሩ የተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሎ ነበር። የወንጌል ዘገባዎችም ሆኑ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው የጆሴፈስ ጽሑፎች የሚገልጹት ይህን ሁኔታ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሕዝቡ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን እንዳይቀበል እስከ ማድረግ ድረስ የሕዝቡን አመለካከት መለወጥ የቻሉ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ሆነው ብቅ አሉ። (ማቴዎስ 15:​1, 2፤ 16:​1፤ ዮሐንስ 11:​47, 48፤ 12:​42, 43) ሆኖም ተደማጭነት ያላቸው እነዚህ ሁለት ቡድኖች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድም ቦታ ተጠቅሰው አናገኝም።

ጆሴፈስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዱቃውያንንና ፈሪሳውያንን የጠቀሰው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከነበረው ሁኔታ ጋር አያይዞ ነው። በዚህ ወቅት ብዙ አይሁዳውያን ማራኪ ለሆነው ለሄለናዊነት ማለትም ለግሪክ ባሕልና ፍልስፍና እጅ እየሰጡ ነበር። የሰሉሲድ ገዥዎች በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ለዜዩስ አገልግሎት እንዲውል በማድረግ ባረከሱት ጊዜ በሄለናዊነትና በአይሁድ እምነት መካከል የነበረው ውጥረት በጣም ተካረረ። ሃስሞናውያን ከሚባለው ቤተሰብ የመጣው ኃይለኛ የሆነው አይሁዳዊ መሪ ጁዳ መቃብ የዓማፅያን ጦር በመምራት ቤተ መቅደሱን ከግሪካውያን እጅ አስለቀቀ። a

ከመቃብያን የዓመፅ እርምጃና ድል በኋላ የነበሩት ዓመታት ተቃራኒ በሆኑ ንድፈ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ ኑፋቄዎችን በማቅረብ አብዛኛውን የአይሁድ ማኅበረሰብ በበላይነት ለመቆጣጠር እርስ በእርስ በሚደረጉ ሽኩቻዎች ተለይተው የሚታወቁ ነበሩ። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ የተፈጠረው ለምንድን ነው? የአይሁድ እምነት ይህን ያክል የተከፋፈለው ለምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት እስቲ የሃስሞናውያንን ታሪክ እንመርምር።

ተጨማሪ ነፃነትና መከፋፈል

ጁዳ መቃብ በይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚካሄደውን አምልኮ መልሶ የማቋቋም ሃይማኖታዊ ግቡን ዳር ካደረሰ በኋላ አቅጣጫውን ወደ ፖለቲካ አዞረ። ከዚህ የተነሳ ብዙ አይሁዳውያን እሱን መከተል አቆሙ። ይህም ሆኖ በሰሉሲድ ገዥዎች ላይ የሚያካሂደውን ውጊያ አላቆመም፤ ከሮም ጋር ስምምነት አደረገ እንዲሁም ነፃ የአይሁድ መንግሥት ለመመሥረት ሞከረ። ጁዳ ውጊያ ላይ እንዳለ ሲሞት ወንድሞቹ ጆናታንና ሳይመን በትግሉ ቀጠሉ። መጀመሪያ ላይ የሰሉሲድ ገዥዎች መቃብያንን በኃይል ተቃውመው ነበር። በኋላ ላይ ግን ገዥዎቹ ሃስሞናውያን ወንድማማቾች በተወሰነ ደረጃ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖራቸው በመፍቀድ የፖለቲካ ስምምነት ለማድረግ ተስማሙ።

ሃስሞናውያን የካህናት ዘር ቢሆኑም እንኳ አንዳቸውም በሊቀ ካህንነት አገልግለው አያውቁም። ብዙ አይሁዳውያን ይህ ቦታ መያዝ ያለበት ሰሎሞን ሊቀ ካህን አድርጎ በሾመው በሳዶቅ መስመር በመጡ ካህናት መሆን አለበት የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። (1 ነገሥት 2:​35፤ ሕዝቅኤል 43:​19) ጆናታን ሰሉሲዶች ሊቀ ካህን አድርገው እንዲሾሙት ለማግባባት በጦርነትና በዲፕሎማሲ ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ ከጆናታን ሞት በኋላ ወንድሙ ሳይመን ከዚያም በላይ አግኝቷል። መስከረም 140 ከዘአበ በነሐስ ጽላት ላይ በግሪክኛ የተጻፈ አንድ ከፍተኛ ትርጉም ያለው አዋጅ ኢየሩሳሌም ውስጥ ወጥቶ ነበር:- “ንጉሥ ዲሚትሪየስ [የግሪክ ሰሉሲድ ገዥ] [ሳይመንን] ሊቀ ካህን አድርጎ ሾሞታል፣ ወዳጁ እንዲሆን መርጦታል፣ ታላቅ ክብርም ሰጥቶታል . . . አይሁዳውያንም ሆኑ ካህናቶቻቸው እምነት የሚጣልበት ነቢይ እስኪነሳ ድረስ ሳይመን ለዘላለም መሪያቸውና ሊቀ ካህናቸው እንዲሆን ወስነዋል።”​—⁠1 መቃብ 14:​38-41 (አዋልድ ውስጥ የሚገኝ የታሪክ መጽሐፍ)

ሳይመን እሱም ሆኑ ዘሮቹ ገዥና ሊቀ ካህን እንዲሆኑ የተሰጣቸውን ሥልጣን ባዕድ የሆነው የሰሉሲድ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሱን ሕዝብ ያቀፈው “ታላቅ ጉባኤ” ተስማማበት። ይህ ከፍተኛ ለውጥ የተደረገበትን ጊዜ ያመለክታል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ኢሚል ሹረር እንዳሉት ሃስሞናውያን የፖለቲካ ሥርወ መንግሥት ካቋቋሙ በኋላ “የሚያሳስባቸው ዋናው ነገር ቶራህን [የአይሁዳውያንን ሕግ] መፈጸም ሳይሆን ፖለቲካዊ ኃይላቸውን ማስጠበቅና ማስፋፋት ሆነ።” ይሁን እንጂ ሳይመን አይሁዳውያንን ላለማስቆጣት ይጠነቀቅ ስለነበር “ንጉሥ” በሚለው የማዕረግ ስም ከመጠቀም ይልቅ “የሕዝቡ መሪ” ተብሎ መጠራት መርጧል።

ሃስሞናውያን ሃይማኖታዊውንም ሆነ ፖለቲካዊውን ሥልጣን አለአግባብ ጠቅልለው መያዛቸው ያላስደሰታቸው ሰዎች ነበሩ። በርካታ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ የኩምራን ማኅበረሰብ የተመሠረተው በዚህ ወቅት ነው። በኩምራን ጽሑፎች ላይ “የጽድቅ አስተማሪ” ተብሎ የተጠራው ሰው እንደሆነ የሚታመን በሳዶቅ መስመር የመጣ አንድ ካህን ከኢየሩሳሌም ወጥቶ የተቃዋሚ ቡድን በመምራት ሙት ባሕር አቅራቢያ ወደሚገኘው የይሁዳ በረሀ ሄደ። ከሙት ባሕር ጥቅልሎች አንዱ የሆነው በዕንባቆም መጽሐፍ ላይ የቀረበ ሐተታ “መጀመሪያ ላይ በእውነት ስም የተጠራው ክፉ ካህን በእስራኤል ላይ ሲገዛ ግን ልቡ ታበየ” ሲል አውግዟል። ኑፋቄው “ክፉ ካህን” ስለሆነው ገዥ የሰጠው መግለጫ ከጆናታን ወይም ከሳይመን ሁኔታ ጋር እንደሚስማማ በርካታ ምሁራን ያምናሉ።

ሳይመን በሥሩ ያለውን ግዛት ለማስፋፋት ወታደራዊ ዘመቻዎች ማካሄዱን ቀጠለ። ሆኖም እሱና ሁለት ወንዶች ልጆቹ ኢያሪኮ አቅራቢያ በግብዣ ላይ እንዳሉ የልጁ ባል በሆነው በቶሌሚ እጅ በተገደሉ ጊዜ አገዛዙ በድንገት ወደ ፍጻሜ መጣ። ቶሌሚ ሥልጣን ለመጨበጥ ያደረገው ይህ ጥረት ከሸፈ። በሕይወት የቀረው የሳይመን ልጅ ጆን ሂርካነስ፣ እሱን የመግደል ዕቅድ እንዳለ ማስጠንቀቂያ ደረሰው። ሊገድሉት ያሰቡትን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ በአባቱ ምትክ የመሪነቱንም ሆነ የሊቀ ካህንነቱን ቦታ ያዘ።

ተጨማሪ መስፋፋትና ጭቆና

መጀመሪያ ላይ ጆን ሂርካነስ ከሶርያውያን ጦር አስጊ ሁኔታ ተደቅኖበት የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን በ129 ከዘአበ የሰሉሲድ ሥርወ መንግሥት ከፓርታውያን ጋር ባደረገው ወሳኝ ጦርነት ሽንፈት ደረሰበት። ጦርነቱ በሰሉሲዳውያን ላይ ያደረሰውን ተጽእኖ በተመለከተ አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር የሆኑት ሜናኪም ስተርን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የመንግሥቱ መዋቅር ባጠቃላይ እንዳለ ተንኮታኮተ።” ከዚህም የተነሳ ሂርካነስ “የይሁዳን ፓለቲካዊ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ማስመለስና በተለያዩ አቅጣጫዎች መስፋፋት መጀመር ችሎ ነበር።” በእርግጥም የግዛት ክልሉን ማስፋፋት ችሏል።

በዚህ ጊዜ ሶርያ የምትፈጥርበት ምንም ዓይነት ስጋት ሳይኖር ሂርካነስ ከይሁዳ ውጪ ያሉ ክልሎችን እየወረረ በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ጀመረ። ነዋሪዎቹ የአሁድን እምነት የግድ መቀበል ነበረባቸው፤ አለዚያ ከተማቸው ይደመሰሳል። እንዲህ ዓይነት ዘመቻ በኤዶማውያን ላይ ተካሂዷል። ዘመቻውን በተመለከተ ስተርን እንዲህ ብለዋል:- “የአይሁድን እምነት የተቀበሉት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኤዶማውያን ወገን ስለነበረ ይህ መለወጥ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነበረ።” በኃይል ከተያዙት ቦታዎች መካከል ሰማርያ የምትገኝበት ሲሆን ሂርካነስ በገራዚም ተራራ ላይ የነበረውን የሳምራውያን ቤተ መቅደስ ደምስሷል። የሃስሞናውያን ሥርወ መንግሥት የያዘው አስገድዶ እምነት የማስቀየር ፖሊሲ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ሲገልጹ የታሪክ ምሁር የሆኑት ሰሎሞን ግራዜል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የማትያስ [የጁዳ መቃብ አባት] የልጅ ልጅ የቀድሞዎቹ ትውልዶች በከፍተኛ ሁኔታ ይታገሉለት የነበረውን የሃይማኖታዊ ነፃነት መሠረታዊ ሥርዓት ጥሷል።”

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ብቅ አሉ

ጆሴፈስ እየጨመረ ስለመጣው የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን ተጽእኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወሳው ስለ ሂርካነስ የግዛት ዘመን በጻፈበት ጊዜ ነበር። (ጆሴፈስ በጆናታን የንግሥና ዘመን ወቅት ስለኖሩት ፈሪሳውያን ተናግሯል።) አነሳሳቸውን በተመለከተ የተናገረው ነገር የለም። አንዳንድ ምሁራን ፈሪሳውያንን በአጠቃላይ ከሐሲዲም የፈለቁ ቡድኖች እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸው ሲሆን ሐሲዲሞች ጁዳ መቃብ በነበሩት ሃይማኖታዊ ግቦች ድጋፍ ሲሰጡት ከቆዩ በኋላ የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ባደረበት ወቅት የከዱት መናፍቃን ናቸው ይላሉ።

ፈሪሳውያን የሚለው ስም ምንም እንኳ አንዳንዶች “አስተርጓሚዎች” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና እንዳለው ቢያስቡም በጥቅሉ “የተለዩ” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ግንኙነት አለው። ፈሪሳውያን ልዩ የሆነ ዝርያ የሌላቸው ከተራው ሕዝብ መካከል የተውጣጡ ምሁራን ናቸው። የክህነት ቅድስናን ለማስጠበቅ የሚያገለግሉ የቤተ መቅደስ ሕጎች ተራ በሆኑ የዕለት ተዕለት ሕይወት ገጠመኞች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆኑ በማድረግ ልዩ የቅድስና መርሕ በመከተል ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ግድፈት ራሳቸውን ለይተዋል። ፈሪሳውያን ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚተረጉሙበት አንድ አዲስ ዘይቤና ከጊዜ በኋላ የቃል ሕግ ተብሎ የተጠራ ጽንሰ ሐሳብ አዳበሩ። ፈሪሳውያን በሳይመን የንግሥና ዘመን አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ ሳንሄድሪን ተብሎ የተጠራው የየሮሲያ (የሽማግሌዎች ምክር ቤት) አባል ሆነው ሲሾሙ ከፍተኛ ተደማጭነት አገኙ።

መጀመሪያ ላይ ጆን ሂርካነስ የፈሪሳውያን ተማሪና ደጋፊ እንደነበረ ጆሴፈስ ይናገራል። ሆኖም በሆነ ወቅት ላይ የሊቀ ካህንነቱን ቦታ ባለመልቀቁ ፈሪሳውያን ወቀሱት። ይህ ያልተጠበቀ መለያየት አስከተለ። ሂርካነስ የፈሪሳውያንን ሃይማኖታዊ ድንጋጌ ሕገ ወጥ አደረገው። እንደ ተጨማሪ ቅጣት በማድረግ የፈሪሳውያን ሃይማኖታዊ ተቀናቃኞች ከሆኑት ከሰዱቃውያን ጋር ወገነ።

ሰዱቃውያን የሚለው ስም ከሰሎሞን ዘመን አንስቶ ልጆቹ የክህነቱን ቦታ ይዘው ከነበሩት ከሊቀ ካህኑ ከሳዶቅ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰዱቃውያን ከዚህ መስመር የመጡ አይደሉም። ጆሴፈስ እንደሚለው ከሆነ ሰዱቃውያን በብሔሩ ያሉ መኳንንቶችንና ቱጃሮችን ያቀፉ ከመሆናቸውም በላይ የብዙሐኑ ድጋፍ አልነበራቸውም። ፕሮፌሰር ሺፍማን እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “አብዛኞቹ ሰዱቃውያን . . . ካህናት አሊያም ከሊቀ ካህናቱ ቤተሰቦች ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ ሰዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው።” በመሆኑም ሥልጣን ላይ ከነበሩት ሰዎች ጋር የረጅም ጊዜ የቅርብ ትስስር ነበራቸው። ስለዚህ ፈሪሳውያን በሕዝቡ ሕይወት ላይ ያላቸው እየጨመረ የመጣ ተጽእኖ እንዲሁም ካህናት የሚጠብቁትን ዓይነት የቅድስና ደረጃ ባጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ለማስፈን የነበረው ፈሪሳዊ አስተሳሰብ ሰዱቃውያን በራሳቸው ያገኙትን ሥልጣን ሊያዳክም እንደሚችል አድርገው ተመልክተውታል። አሁን በሂርካነስ የሥልጣን ዘመን የመጨረሻዎቹ ዓመታት ሰዱቃውያን መልሰው ሥልጣን ጨበጡ።

ከሃይማኖት ይልቅ ወደ ፖለቲካ ያደሉ

የሂርካነስ የመጀመሪያ ልጅ አሪስቶቡለስ ለአንድ ዓመት ብቻ ነግሦ ሞተ። ኢቱርያውያንን አስገድዶ እምነት የማስቀየር ፖሊሲውን ማራመዱን የቀጠለ ከመሆኑም በላይ ላይኛውን የገሊላ ክፍል በሃስሞናውያን ቁጥጥር ሥር አደረገ። ሆኖም የሃስሞናውያን ሥርወ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን እርካብ ላይ የደረሰው ከ103 እስከ 76 ከዘአበ በገዛው በታናሽ ወንድሙ በአሌክሳንደር ጃናየስ የግዛት ዘመን ነበር።

አሌክሳንደር ጃናየስ የቀድሞውን ፖሊሲ በመሻር ራሱን ሊቀ ካህንና ንጉሥ አድርጎ በይፋ አወጀ። በሃስሞናውያንና በፈሪሳውያን መካከል ያለው ግጭት እየተፋፋመ መጥቶ 50, 000 የሚሆኑ አይሁዳውያን ላለቁበት የእርስ በርስ ጦርነት መንስኤ ሆነ። የዓመፅ እንቅስቃሴው ከተጨፈለቀ በኋላ ጃናየስ 800 ዓማፅያንን በስቅላት በመቅጣት የአረማዊ ነገሥታትን አድራጎት የሚያስታውስ ተግባር ፈጸመ። ጃናየስ ከቁባቶቹ ጋር በግልጽ ግብዣ ላይ እንዳለ ዓማፅያኑ ተሰቅለው እያጣጣሩ በዓይናቸው ፊት ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ታረዱ። b

ጃናየስ ፈሪሳውያንን ቢጠላም እንኳ እውነታዎችን የሚቀበል የፖለቲካ ሰው ነበር። ፈሪሳውያን እያደገ የመጣ የሕዝብ ድጋፍ እንዳላቸው ተገነዘበ። በሞት አፋፍ ላይ ሳለ ለሚስቱ ለሰሎሜ አሌክሳንድራ የሰጣት መመሪያ ቢኖር ለፈሪሳውያን ሥልጣን እንድታጋራ ነበር። ጃናየስ ከወንድ ልጆቹ ይልቅ የመንግሥቱ አልጋ ወራሽ እንድትሆን የመረጠው እሷን ነበር። ሰሎሜ ብሔሩ በሃስሞናውያን አገዛዝ ሥር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሰላም የሰፈነበት ወቅት (76-67 ከዘአበ) እንዲያገኝ በማድረግ ብቃት ያላት መሪ መሆኗን አስመሰከረች። ፈሪሳውያን እንደገና ሥልጣን እንዲይዙ ተደረገ፤ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ድንጋጌያቸው ላይ የወጣው ሕግ ተሻረ።

ሰሎሜ ስትሞት ሊቀ ካህን ሆኖ ያገለግል የነበረው ልጅዋ ዳግማዊ ሂርካነስ እና ዳግማዊ አሪስቶቡለስ ሥልጣን ለመጨበጥ ሽኩቻ ጀመሩ። ሁለቱም አባቶቻቸው የነበራቸው ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ማስተዋል ይጎድላቸው ነበር። ደግሞም የሰሉሲድ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከወደቀ በኋላ በአካባቢው እየጨመረ የመጣው የሮማውያን እንቅስቃሴ ምን ትርጉም እንዳለው ሙሉ በሙሉ የተረዱ አይመስልም። በ63 ከዘአበ ሮማዊው ገዥ ፖምፔ በደማስቆ እያለ ሁለቱ ወንድማማቾች እሱ ዘንድ ቀርበው በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት እንዲሸመግል ጠየቁት። በዚያው ዓመት ፖምፔ እና ወታደሮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ገስግሰው ከተማዋን ተቆጣጠሩ። ይህ የሃስሞናውያን መንግሥት ማብቂያ መጀመሪያ ነበር። በ37 ከዘአበ የሮማ ሴኔት “የሮማ ሕዝብ አጋርና ወዳጅ” “የይሁዳ ንጉሥ” ሲል ሥልጣኑን ያጸደቀለት ኤዶማዊው ንጉሥ ታላቁ ሄሮድስ ኢየሩሳሌምን ተቆጣጠረ። ከዚህ በኋላ የሃስሞናውያን መንግሥት አከተመ።

የሃስሞናውያን ቅርስ

ከጁዳ መቃብ አንስቶ እስከ ዳግማዊ አሪስቶቡለስ ድረስ የነበረው የሃስሞናውያን ዘመን ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለተከሰተው ሃይማኖታዊ መከፋፈል መሠረት ጥሏል። ሃስሞናውያን ለአምላክ አምልኮ ቅንአት ይዘው ቢነሱም በኋላ ላይ ቅንአታቸው ተገቢ ወዳልሆነ የራስን ጥቅም ወደማስጠበቅ አመራ። የአምላክን ሕግ እንዲታዘዙ በማድረግ ሕዝቡን የማስተባበር አጋጣሚ የነበራቸው ካህናት ብሔሩን መራራ ወደሆነ የፖለቲካ ትግል አዘቅት ውስጥ ጨመሩት። በዚህ ሁኔታ መከፋፈል የሚፈጥሩ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ተስፋፉ። ሃስሞናውያን አክትሞላቸዋል፤ ይሁን እንጂ በሰዱቃውያን፣ በፈሪሳውያንና በሌሎችም መካከል ሃይማኖታዊ የበላይነት ለመቀዳጀት የሚደረገው ሽኩቻ በሄሮድስና በሮም ሥር ያለችውን ብሔር ለይቶ የሚያሳውቃት ገጽታ ሆኗል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የኅዳር 15, 1998 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መቃብያን እነማን ነበሩ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b የሙት ባሕር ጥቅልል የሆነው “በናሆም መጽሐፍ ላይ የተሰጠ ማብራሪያ” “ሰዎችን ከነሕይወታቸው ስለ ሰቀለው” “ቁጡ አንበሳ” ይጠቅሳል። ይህም ከላይ የተጠቀሰውን ድርጊት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሃስሞናውያን ሥርወ መንግሥት

ጁዳ መቃብ

ጆናታን መቃብ

ሳይመን መቃብ

ጆን ሂርካነስ

↓ ↓

አሪስቶቡለስ

ሰሎሜ አሌክሳንድራ–ባልዋ–አሌክሳንደር ጃናየስ

↓ ↓

ዳግማዊ ሂርካነስ

ዳግማዊ አሪስቶቡለስ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጁዳ መቃብ አይሁዳውያንን ነፃ ለማውጣት ፍላጎት ነበረው

[ምንጭ]

The Doré Bible Illustrations/​Dover Publications, Inc.

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃስሞናውያን የአይሁድ ባልሆኑ ከተሞች ላይ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ተዋግተዋል

[ምንጭ]

The Doré Bible Illustrations/​Dover Publications, Inc.