በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ድንቅ የፈጠራ ውጤት”

“ድንቅ የፈጠራ ውጤት”

ምሉዓን ሆናችሁና ጽኑ እምነት ኖሯችሁ ቁሙ

“ድንቅ የፈጠራ ውጤት”

የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዘመን እንቅስቃሴያቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለተናገረው ትንቢት ልዩ ትኩረት ሲሰጡ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 24:​14) ‘የመጨረሻው ቀን’ መጀመሪያ የሆነው 1914 ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ልበ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጽኑ እምነት በመያዝ ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፍ የትምህርት ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ምሥራቹን በምድር ዙሪያ የማወጅ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ አዲስ፣ ቀጥተኛና ውጤታማ ዘዴ ተጠቅመው ነበር። ስለዚህ ዘዴ የበለጠ ለማወቅ እስቲ ያለፈውን ጊዜ መለስ ብለን እንቃኝ።

ምሥራቹን ለማወጅ የተቀየሰ አዲስ ዘዴ

ጊዜው ጥር 1914 ነው። በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኝ አንድ ጨለማ አዳራሽ ውስጥ ከ5, 000 ሰዎች ጋር ተቀምጠሃል እንበል። ከፊት ለፊትህ የተንቀሳቃሽ ፊልም ማሳያ ትልቅ ስክሪን ተዘርግቷል። ካፖርት የለበሰ ሽበታም ሰው መታየት ጀመረ። ከዚያ ቀደም ያየሃቸው ፊልሞች ድምፅ የሌላቸው ነበሩ፤ ሰውዬው ግን ይናገራል፤ አንተም የሚናገረውን መስማት ትችላለህ። የተ​ገኘኸው አንድ አዲስ የፈጠራ ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ በቀረበበት ዝግጅት ላይ ሲሆን የምትሰማው መልእክትም በዓይነቱ ልዩ ነው። ተናጋሪው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል ሲሆን የፈጠራው ውጤት ደግሞ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ይባላል።

ሲ ቲ ራስል ተንቀሳቃሽ ፊልምን በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች ማሳየት እንደሚቻል ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም በ1912 “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የሚባለውን ፊልም ማዘጋጀት ጀመረ። በመጨረሻም ፊልሙ ስምንት ሰዓት የሚወስድ ባለ ቀለምና ድምፅ የፎቶግራፍ ስላይድ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ፊልም ለመሆን በቃ።

አራት ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ የተዘጋጀው “ፎቶ ድራማ” ተመልካቹን ከፍጥረት አንስቶ ይሖዋ አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያወጣው ዓላማ ፍጻሜውን እስከሚያገኝበት እስከ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ድረስ ይወስዳል። ሌሎች ሰዎች ይህን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል ዓመታት ፈጅቶባቸዋል። የሆነው ሆኖ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የሚባለውን ፊልም በነፃ ተመልክተዋል!

ይህን “ፎቶ ድራማ” ለማዘጋጀት አጃቢ ሙዚቃዎች የተመረጡ ሲሆን 96 ንግግሮች በሸክላ ተቀድተዋል። የዓለምን ታሪክ የሚያሳዩ ሥዕሎች በስላይድ ፊልም ተዘጋጁ። እንዲሁም በመቶ የሚቆጠሩ አዳዲስ ሥዕሎችንና ንድፎችን መሥራት አስፈልጎ ነበር። አንዳንዶቹ ባለ ቀለም ስላይዶችና ፊልሞች በከፍተኛ ጥንቃቄ በእጅ የተሣሉ ናቸው። አንድ ሥዕል በተደጋጋሚ ይሳል የነበረ ሲሆን እንዲያውም አራቱን ክፍሎች እያንዳንዳቸውን 20 ጊዜ ማዘ​ጋጀት አስፈልጓል። ይህ ደግሞ “ፎቶ ድራማው” በአንድ ቀን ውስጥ በ80 የተለያዩ ከተ​ማዎች ውስጥ ለማሳየት አስችሏል!

ከመድረክ በስተጀርባ

“ፎቶ ድራማው” ለሕዝብ ዕይታ በቀረበ ጊዜ ከመድረክ በስተጀርባ ምን ተከናውኖ ነበር? አሊስ ሆፍማን የምትባል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ድራማው የወንድም ራስልን ምስል በማሳየት ይጀምራል። ወንድም ራስል በስክሪኑ ላይ ታይቶ ከንፈሮቹ ሲንቀሳቀሱ ሸክላው መጫወት ይጀምራል። . . . እኛም ድምፁን እንሰማለን።”

ዞላ ሆፍማን የፎቶግራፍ ፊልሙን የማፍጠን ጥበብ በመጠቀም “ፎቶ ድራማ” ስለቀረበበት ሁኔታ ስትገልጽ “የፍጥረት ቀናትን የሚያሳየውን ክፍል ስንመለከት ዓይኖቼ በአድናቆት ፈጠጡ። አበቦች ቀስ በቀስ ሲፈኩ በግልጽ ይታዩ ነበር” ብላለች።

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባልና ሙዚቃ አፍቃሪው ካርል ኤፍ ክላይን “ፊልሙ በሚታይበት ጊዜ ናርሲሱስ እና ሁሞሬስኬ የሚባሉትን የመሳሰሉ ድንቅ የሙዚቃ ቅንብሮች በአጃቢነት ይሰሙ ነበር” ብሏል።

አንዳንድ የማይረሱ ትዝታዎችም ነበሩ። ክሌይተን ጄ ዉድዎርዝ ሁኔታውን አስታውሶ “አንዳንድ ጊዜ አስቂኝ ስህተቶች ይፈጸሙ ነበር። አንድ ጊዜ ሸክላው ‘እንደ እርግብ ወደ ተራራችሁ ሽሹ’ እያለ ሲጫወት ከጥፋት ውኃ በፊት ይኖር የነበረ ጊጋንቶሳውሩስ የሚባል ግዙፍ እንስሳ በስክሪኑ ላይ ይታይ ነበር!” በማለት ተናግሯል።

“የፍጥረት ፎቶ ድራማ” እየታየ “ዩሬካ ድራማ” ተዘጋጀ። (ሣጥኑን ተመልከት።) አንደኛው ‘የዩሬካ ድራማ’ የተዘጋጀው በሸክላ በተቀዱ ንግግሮችና በአጃቢ ሙዚቃዎች ሲሆን ሌላኛው ግን የንግግሮቹንና የሙዚቃውን ቅጂ ጨምሮ የስላይድ ፊልም ነበረው። “ዩሬካ ድራማ” ተንቀሳቃሽ ፊልም አይኑረው እንጂ ሕዝብ በማይበዛባቸው አካባቢዎች ታይቶ በጣም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

ውጤታማ የመመሥከሪያ መሣሪያ

“ፎቶ ድራማውን” በ1914 መገባደጃ ላይ በደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በአውስትራሊያ የሚኖሩ በድምሩ 9, 000, 000 የሚያክሉ ሰዎች አይተውታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም በዚህ አዲስ ዘዴ በመጠቀም ምሥራቹን በጽኑ እምነት ሰብከዋል። እነዚህን ድራማዎች ለማሳየት ሲሉ ምቹ አዳራሾች ለመከራየት የሚያስፈልገውን ወጪ በደስታ ሸፍነዋል። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ሰዎች የአምላክን ቃልና ዓላማ እንዲያውቁ በመርዳት በኩል ትልቅ ቁም ነገር አከናውኗል።

አንድ ሰው ለሲ ቲ ራስል በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ድራማውን ለመጀመሪያ ጊዜ መመልከቴ ሕይወቴን ለውጦልኛል፤ ወይም የነበረኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ሙሉ በሙሉ እንዲለወጥ አድርጓል ማለት እችላለሁ” በማለት ጠቅሷል። አንዲት ሴት ደግሞ “ባለፈው በጋ አምጥታችሁ ያሳያችሁን ‘የፍጥረት ፎቶ ድራማ’ ጨርሶ ሊጠፋ ተቃርቦ የነበረው እምነቴ እንደገና እንዲያንሰራራ አድርጎልኛል። . . . አሁን ዓለም ሊሰጠኝ የማይችለውንና በምንም ነገር የማልለውጠውን ሰላም አግኝቻለሁ” ብላለች።

በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የረጅም ጊዜ አባል የነበረው ድሜትሪየስ ፓፓጆርጅ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቁጥር አነስተኛና የገንዘብ አቅማቸውም ውስን መሆኑን ስንመለከት ‘የፍጥረት ፎቶ ድራማ’ ታላቅ የፈጠራ ውጤት ነበር። በእርግጥም ከዚህ ሥራ በስተጀርባ የይሖዋ መንፈስ አለ!”

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ዩሬካ ድራማ”

“ፎቶ ድራማ” ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ ከስምንት ወር በኋላ ማኅበሩ “ዩሬካ ድራማ” የሚባል ሌላ ዓይነት ድራማ የማዘጋጀቱን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። ሙሉው “ፎቶ ድራማ” በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ በመታየት ላይ እያለ ተመሳሳይ መልእክት ያዘለው “ዩሬካ ድራማ” በትናንሽ መንደሮችና በገጠር አካባቢዎች ይታይ ነበር። “የዩሬካ ድራማ” አንድ ክፍል “እህቶች ለመስበክ ልዩ አጋጣሚ” እንደፈጠረላቸው ተገልጿል። ለምን? ምክንያቱም የሸክላዎቹ ማኅደር የሚመዝነው 14 ኪሎ ግራም ብቻ ነበር። ድራማውን ለማሳየት ደግሞ የሸክላ ማጫወቻውን ይዞ መሄድ የግድ ነው።