በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርሜንያው ወርቃማ ፍሬ

የአርሜንያው ወርቃማ ፍሬ

የአርሜንያው ወርቃማ ፍሬ

● አፕሪኮት ለበርካታ ሺህ ዓመታት በእስያና በአውሮፓ ሲመረት ቆይቷል። አውሮፓውያን፣ አፕሪኮት መጀመሪያ የተገኘው በአርሜንያ እንደሆነ ያምኑ ስለነበር ፍሬውን የአርሜንያ ፖም በማለት መጥራት ጀመሩ።

በዛሬው ጊዜ 50 የሚያህሉ የአፕሪኮት ዝርያዎች በአርሜንያ ይበቅላሉ። የአፕሪኮት ዛፎች የሚያፈሩት ከሰኔ አጋማሽ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ከእሳተ ጎሞራ የተገኘውና በተለያዩ ማዕድናት የዳበረው የአርሜንያ አፈር እንዲሁም ፀሐያማ የሆነው የአገሪቱ የአየር ንብረት በዚያ የሚበቅሉት አፕሪኮቶች ልዩ የሆነ ጣዕም እንዲኖራቸው አድርገዋል፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች የአርሜንያ አፕሪኮቶችን በዓለም ላይ ከሚገኙት በጣም ጣፋጭ አፕሪኮቶች ተርታ ይመድቧቸዋል።

የተለመዱት የአፕሪኮት ዝርያዎች መጠናቸው ፕሪም ያህላል፤ ቀለማቸውም ፈዘዝ ያለ ወርቃማ ወይም ደማቅ ብርቱካንማ አሊያም በሁለቱ መካከል ሊሆን ይችላል። አፕሪኮት የላይኛው ሽፋኑ ለስላሳ ሲሆን ውስጡ ግን ጠንከር ያለ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ውኃ የለውም፤ ጣዕሙም ጣፋጭ ወይም ጎምዘዝ ያለ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች፣ በጣም የተለመዱት የአፕሪኮት ዝርያዎች በኮክና በፕሪም መካከል የሚገኝ ጣዕም እንዳላቸው ይናገራሉ።

የአፕሪኮት ገበሬዎች “ጥቁር” አፕሪኮት ማምረት የቻሉ ቢሆንም ይህ ግን እውነተኛ አፕሪኮት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አፕሪኮትንና ፕሪምን በማዳቀል የተገኘ ዝርያ ነው። ይህ ዝርያ ወደ ጥቁር የሚጠጋ ደማቅ ሐምራዊ ቀለም ያለው ሲሆን ቆዳው እንደ ኮክ ሆኖ ውስጡ ቢጫ ነው። ይህ ፍሬ ፕለዎት፣ ፕለምኮት ወይም አፕሪም የሚሉ የተለያዩ መጠሪያዎች የሚሰጡት ሲሆን እነዚህ ስሞች የተገኙት “የፕሪም” እና “የአፕሪኮትን” የእንግሊዝኛ ስያሜ በመቀላቀል ነው።

የአፕሪኮት ዛፎች የሚያብቡት ቅጠል ከማውጣታቸው በፊት ሲሆን ጥሩ መዓዛ ያላቸውና ዘሩ በራሱ እንዲዳቀል የሚያስችሉ ነጭ አበቦች ብቅ ይላሉ። አበቦቹ ከኮክ፣ ከፕሪም እንዲሁም ከቼሪ አበቦች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ዛፎቹ ለማበብና ጥሩ ፍሬ ለማፍራት መጠነኛ ቅዝቃዜ ስለሚያስፈልጋቸው ጥሩ የአፕሪኮት ምርት የሚገኘው ቀዝቃዛ የበጋ ወቅትና ሞቅ ያለ ክረምት ባላቸው አካባቢዎች ነው። በመሆኑም የአርሜንያ የአየር ንብረት ለእነዚህ ዛፎች በጣም ተስማሚ ነው።

አፕሪኮቶች ከዛፍ ላይ እንደተቆረጡ ከተበሉ ከጤና አንጻር ብዙ ጠቀሜታ አላቸው። ለምሳሌ በቤታ ካሮቲን እና በቫይታሚን ሲ የበለጸጉ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች የሚያውቁት የደረቁ አፕሪኮቶችን ነው። ይህም የሆነው አፕሪኮቶች ካልደረቁ ትሙክ ትሙክ የሚሉና በቀላሉ የሚበላሹ በመሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ይበልጥ የተለመዱት የደረቁ አፕሪኮቶች ናቸው። የሚያስደስተው ግን የደረቁ አፕሪኮቶችም በአሰርና በብረት ማዕድን የበለጸጉ በመሆናቸው ለሰውነት በጣም ይጠቅማሉ። ከዚህም ሌላ አፕሪኮቶች ብራንዲ የተባለውን መጠጥ፣ ዳቦ ላይ የሚቀባ ጣፋጭ ምግብ እንዲሁም ጭማቂ ለመሥራት ያገለግላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ከአፕሪኮት ዛፍ ግንድ የሚያማምሩ የእንጨት ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት ይቻላል፤ ዱዱክ የተባለው ተወዳጅ የሆነው የአርሜንያውያን የሙዚቃ መሣሪያ የሚሠራው ከዚህ ዛፍ ሲሆን መሣሪያው የአፕሪኮት ዋሽንት በመባልም ይጠራል። የአርሜንያ ዋና ከተማ የሆነችውን የረቫንን የሚጎበኙ ቱሪስቶች በከተማዋ በሚገኙ ሱቆችና የገበያ ስፍራዎች ውስጥ ሲዘዋወሩ ውብ የሆኑና ከአፕሪኮት ዛፍ የተሠሩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችንና ጌጣ ጌጦችን ማግኘት ይችላሉ።

በምትኖርበት አካባቢ የአፕሪኮት ፍሬ የሚገኝ ከሆነ ለምን አትቀምሰውም? የዚህን ወርቃማ ፍሬ ጣዕም በጣም እንደምትወደው ምንም ጥርጥር የለውም።