በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁጣን መቆጣጠር

ቁጣን መቆጣጠር

 ቁጣን መቆጣጠር

ከ2,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የግሪኩ ፈላስፋ አርስቶትል አሳዛኝ ተውኔቶችን ወይም ድራማዎችን ማየት የሚያስከትለውን ጭንቀት “ማስወጣትን” ለመግለጽ “ከታርሲስ” የሚል ቃል ተጠቅሞ ነበር። አርስቶትል መግለጽ የፈለገው ነገር፣ አንድ ሰው ያስጨነቀውን ስሜት ሲያወጣው ሥነ ልቦናዊ እረፍት ያገኛል የሚል ነው።

ባለፈው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢም፣ የነርቭ ሕክምና ባለሙያ የሆነው ኦስትሪያዊው ሲግመንድ ፍሮይድ ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። ሰዎች አሉታዊ ስሜቶቻቸውን አምቀው ከቆዩ፣ የኋላ ኋላ እነዚህ ስሜቶች እንደ አእምሮ መረበሽ ለመሳሰሉ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሊያጋልጧቸው እንደሚችሉ ፍሮይት ተናግሮ ነበር። በመሆኑም ፍሮይት ቁጣን በመግታት ፈንታ ልናወጣው እንደሚገባ ገልጿል።

በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ ዓመታት ውስጥ ግን ከታርሲስ በተባለው ንድፈ ሐሳብ ላይ ጥናት ያካሄዱ ተመራማሪዎች  ፍሮይድ ለተናገረው ነገር ድጋፍ የሚሆን ማስረጃ አላገኙም። ካሮል ታቭረስ የተባሉት የሥነ ልቦና ባለሙያ ተመራማሪዎቹ ካገኟቸው ውጤቶች በመነሳት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የከታርሲስን መላ ምት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልናስወግደው ይገባል። ዓመፅን መመልከት (ወይም ‘ስሜትን ማውጣት’) የጥላቻ ስሜትን ለማስወገድ ይረዳል የሚለው እምነት ፈጽሞ በጥናት የተደገፈ አይደለም ማለት ይቻላል።”

ጌሪ ሃንከንስ የተባሉ ሌላ የሥነ ልቦና ባለሙያ ደግሞ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “የከታርሲስ ንድፈ ሐሳብ እንደሚለው ንዴትህን በሙሉ ‘ማውጣት’ ብዙውን ጊዜ የባሰውን እንድትበሳጭ ከማድረግ በቀር እፎይታ አይሰጥህም።” እርግጥ ነው፣ በአእምሮ ጤንነት መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች በከታርሲስ ዙሪያ በሚደረገው ውዝግብ መቼም ቢሆን ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን ብዙ ሰዎች ከሌላ ምንጭ ይኸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙት ጥበብ ጠቅሟቸዋል።

‘ቍጣን ተወው’

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው መዝሙራዊው ዳዊት ቁጣን ለመቆጣጠር የሚረዳ ጥሩ ሐሳብ አስፍሯል፤ ዳዊት “ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ [“በንዴት አትብገን፣” NW]” ብሏል። (መዝሙር 37:8) በኋላ ላይ የምትቆጭበትን ነገር ከመናገር ወይም ከማድረግ ለመቆጠብ የሚረዳው አንዱ መንገድ መጀመሪያውኑ ‘በንዴት አለመብገን’ ነው። እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረጉ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ይቻላል! ቁጣህን ለመቆጣጠር የሚያስችሉህን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ከልክ በላይ አትቆጣ

ከልክ በላይ ላለመቆጣት፣ ረጋ ብለህ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ለማየት መሞከር ጠቃሚ ነው። መጀመሪያ ወደ አእምሮህ የመጣውን ነገር ላለመናገር ጥረት አድርግ። ደምህ እየፈላ እንደሆነና ራስህን መቆጣጠር የማትችልበት ደረጃ ላይ እንደደረስክ ከተሰማህ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርግ።​—ምሳሌ 17:14

ጃክ የሚባል አንድ ቁጡ የነበረ ሰው ይህን ባሕርዩን ለማሸነፍ የረዳው ይህ ምክር ነው። የጃክ አባት ሰካራምና ግልፍተኛ ነበር። ጃክም እያደገ ሲሄድ እንደ አባቱ ዓይነት ባሕርይ አዳበረ። እንዲህ ይላል፦ “ስናደድ ውስጤ በእሳት እንደተያያዘ ሆኖ ይሰማኛል። በቁጣ እደነፋለሁ፤ ይህም ሳይበቃኝ ቡጢ እስከ መሰንዘር እደርሳለሁ።”

ይሁን እንጂ ጃክ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። ጃክ በአምላክ እርዳታ መለወጥና ቁጣውን መቆጣጠርን መማር እንደሚችል ተገነዘበ። ደግሞም ተለወጠ! ጃክ አንድ የሥራ ባልደረባው በንዴት ባንባረቀበትና በሰደበው ጊዜ ምን ምላሽ እንደሰጠ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቁጣ ሰውነቴን ሲወረው ተሰማኝ። በወቅቱ ግለሰቡን አንስቼ ባፈርጠው ደስ ይለኝ ነበር።”

ታዲያ ጃክን እንዲረጋጋ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “‘ይሖዋ እባክህ እንድረጋጋ እርዳኝ!’ ብዬ እንደጸለይኩ ትዝ ይለኛል። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጤ ሰላም ሲሰፍን ተሰማኝ፤ ሰውየውንም ትቼው መሄድ ቻልኩ።” ጃክ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱን ቀጠለ። ደጋግሞ ይጸልይ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በ⁠ምሳሌ 26:20 ላይ እንደሚገኘው “ዕንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል” እንደሚለው ባሉ ጥቅሶች ላይ ያሰላስል ነበር። ውሎ አድሮ ጃክ ቁጣውን መቆጣጠር ችሏል።

መረጋጋትን ተማር

“ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል።” (ምሳሌ 14:30) አንድ ሰው ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተሉ ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነቱን ሊያሻሽልለት ይችላል። የቁጣ ስሜትን ለማብረድና መንፈስን  ዘና ለማድረግ የሚረዱ ቀላል ዘዴዎችን ለመማር ሞክር። ቀጥሎ የቀረቡት ዘዴዎች በውጥረት ምክንያት የሚመጣን ቁጣ ለማሸነፍ ውጤታማ መሆናቸው ታይቷል።

● ንዴትን ለማብረድ ከሚረዱ እጅግ ውጤታማና ፈጣን ዘዴዎች አንዱ በረጅሙ መተንፈስ ነው።

● በረጅሙ በምትተነፍስበት ጊዜ “ተረጋጋ፣” “ተወው ይሁን” ወይም “ምንም አይደል” እንደሚሉት ያሉ ሊያረጋጉህ የሚችሉ ቃላትን ለራስህ እየደጋገምክ ተናገር።

● የምትወደውን ነገር በማድረግ ለምሳሌ በማንበብ፣ ሙዚቃ በማዳመጥ፣ አትክልት በመንከባከብ ወይም ሌላ የሚያረጋጋህ ነገር በመሥራት ራስህን አስጠምድ።

● አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ፤ እንዲሁም ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ተመገብ።

በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን

እንድትቆጣ ሊያደርጉህ ከሚችሉ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ጨርሶ መራቅ ባትችልም የሚያናድድ ነገር ሲያጋጥምህ የምትሰጠውን ምላሽ ግን መቆጣጠር ትችላለህ። ይህም የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል።

ከሌሎች ብዙ የሚጠብቁ ሰዎች የመቆጣት አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው። ለምን? ምክንያቱም አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር እነሱ የጠበቁት የላቀ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ሲቀር ለሐዘንና ለብስጭት ይዳረጋሉ። እንዲህ ያለውን ፍጽምና የመጠበቅ አዝማሚያ ለማሸነፍ “ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድም እንኳ የለም፤ . . . ሁሉም መንገድ ስተዋል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። (ሮም 3:10, 12) በመሆኑም እኛም ሆንን ሌሎች ፍጹም መሆን እንደምንችል የምናስብ ከሆነ ብስጭት ላይ የመውደቅ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል።

ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ብዙ አለመጠበቅ ብልህነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ . . . ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2) አዎን፣ “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።” (መክብብ 7:20) ስለዚህ ያልሆንነውን ለመሆን በሌላ አባባል ፍጹም ለመምሰል የምንጥር ከሆነ የምናተርፈው ነገር ቢኖር ሕይወታችን በብስጭትና በንዴት የተሞላ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ነው።

ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደ መሆናችን መጠን ሁላችንም አልፎ አልፎ ቁጣችንን መቆጣጠር ያቅተናል። ቁጣችንን የምንገልጽበትን መንገድ ግን መቆጣጠር እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ኤፌሶን 4:26) አዎን፣ ቁጣችንን በመቆጣጠር ስሜታችንን በተሻለ ይኸውም ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በማይጎዳ መንገድ መግለጽ እንችላለን።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

መረጋጋትን ተማር

በረጅሙ መተንፈስን ተለማመድ

የምትወደውን ነገር በመሥራት ራስህን አስጠምድ

አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ