ሃይማኖት የሰውን ዘር አንድ ማድረግ ያልቻለው ለምንድን ነው?

ሃይማኖት የሰውን ዘር አንድ ማድረግ ያልቻለው ለምንድን ነው?

ሃይማኖት የሰውን ዘር አንድ ማድረግ ያልቻለው ለምንድን ነው?

ሃይማኖት ለግጭቶች ሁሉ ዋነኛ መንስኤ ነው ብሎ መናገር ሃይማኖት ባይኖር ኖሮ የጦርነቶች ቁጥር በጣም ይቀንስ ነበር ብሎ እንደ መናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ የመከራከሪያ ነጥብ ምክንያታዊ ነው? ሃይማኖትን በማጥፋት ጦርነትን ማስቀረት ይቻላል? የአንተ መልስ ምንም ይሁን ምን፣ አንድ የማይታበል ሐቅ አለ፦ ሃይማኖት የሰውን ዘር አንድ ማድረግ አልቻለም። እንዲህ እንድንል የሚያደርጉንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

በሃይማኖት መከፋፈል

ሰብዓዊው ኅብረተሰብ በሃይማኖት የተከፋፈለ ሲሆን ዋና ዋና የሚባሉ ሃይማኖቶች እርስ በርስ ተቀናቃኞች ሆነዋል። ታዲያ ቡድሂስቶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሂንዱዎች፣ አይሁዶችና ሙስሊሞች በሰላም አብረው ይኖራሉ ብሎ ለማመን የሚያበቃ አንዳች ምክንያት ይኖራል?

ሌላው አሳዛኝ እውነታ ደግሞ እነዚህ ዋና ዋና ሃይማኖታዊ ቡድኖች በውስጣቸው እየተከፋፈሉ መምጣታቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ግምት እንደሚያሳየው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ተከፋፍለው ከ30,000 በላይ ቡድኖች ተፈጥረዋል። እስልምናም ቢሆን እርስ በርስ በሚጋጩ እምነቶች ምክንያት ከመከፋፈል አላመለጠም። አንድ የመካከለኛው ምሥራቅ የዜና ወኪል እንደዘገበው በቅርቡ ሞሲን ሆጃት የሚባሉ አንድ ሙስሊም ሃይማኖታዊ ምሑር “በሙስሊሙ ዓለም ለተፈጠሩት ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ሙስሊሞች መከፋፈላቸው ነው” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። እንደ ቡድሂዝም፣ ሂንዱይዝም እንዲሁም የአይሁድ እምነት ያሉ ሌሎች ዋና ዋና ሃይማኖቶችም እርስ በርስ በሚጋጩ ኑፋቄዎች ተከፋፍለዋል።

ሃይማኖት ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ

ሃይማኖት ከመንፈሳዊ ሕይወት ውጪ ባለው የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ማለት ይቻላል። ዚ ኤኮኖሚስት የተሰኘው የዜና መጽሔት “ሃይማኖተኛ ሰዎች፣ የንግዱን ዓለም ጨምሮ በሁሉም ዓይነት መስኮች ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው። ሃይማኖት በኢኮኖሚው ውስጥም ጭምር ሥር እየሰደደ ነው” በማለት የታዘበውን ገልጿል። ይህ ደግሞ ሰዎችን አንድ ከማድረግ ይልቅ እንዲከፋፈሉ እያደረጋቸው ነው። ይሁን እንጂ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው ታሪክ እንደሚያሳየው ይበልጥ ጎጂ የሚሆነው ሃይማኖት በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ነው።

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ በተጠቀሰው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ላይ አንድ የታሪክ ተመራማሪዎች ቡድን “ሃይማኖትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ኅብረት ሲፈጥሩ ወይም እርስ በርስ ሲቆራኙ ሃይማኖት የጦርነት መንስኤ መሆኑ የማይቀር ነው” በማለት ገልጿል። እዚህ ላይም አንድ የማይታበል ሐቅ አለ፦ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሃይማኖት ከፖለቲካዊና ከወታደራዊ አካላት ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው።

አደገኛ ውሕደት

በብዙ አገሮች ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ሃይማኖቶች የአገር ፍቅርና የዘር ማንነት መገለጫዎች እየሆኑ ነው። በዚህም የተነሳ በብሔር፣ በዘርና በጎሣ ምክንያት የሚቀሰቀሰውን ጥላቻ በሃይማኖት ምክንያት ከሚመጣው ጥላቻ መለየት አስቸጋሪ እየሆነ ነው። ይህ አደገኛ ውሕደት ዓለምን ብትንትኗን ለማውጣት የሚያስችሉ ወሳኝ ቅመሞችን ይዟል።

ከዚህ ሁሉ ደግሞ በጣም ግራ የሚያጋባው ነገር አብዛኛው ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን ፈጣሪ እወክላለሁ ማለቱ ነው። ሁሉን ቻይ፣ አፍቃሪና በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ፈጣሪ የሰውን ዘር ከሚከፋፍሉና በደም ዕዳ ተጠያቂ ከሆኑ ሃይማኖቶች ጋር ግንኙነት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋም በመያዛቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገው ነበር