በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

የኖኅ መርከብ እና የመርከብ ምህንድስና (ጥር 2007) የኖኅ መርከብ በሚያስደንቅ አኳኋን እንደተሠራ እርግጠኛ ነበርኩ፤ ሆኖም ስለ አሠራሩ በትክክል የማውቀው ነገር አልነበረም። ይህ ርዕሰ ትምህርት የመርከቡ ርዝመት፣ ወርድና ቁመት ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ መሠራቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ ተስማሚ እንዲሆን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ቀለል ባለ መንገድ ያብራራል። ርዕሱን ካነበብኩ በኋላ በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በመጽሔቱ ላይ የሚገኘውን ንድፍ በመከተል የመርከቡን ሞዴል ለመሥራት ወሰንኩ። በወረቀት የተለያዩ እንስሳትን ከሠራን በኋላ መርከቡ ውስጥ አስቀመጥናቸው፤ ከዚያም የኖኅንና የቤተሰቡን ሥዕል ሠራን። ራሳችንን በባለ ታሪኮቹ ቦታ በማስቀመጥ ስለ ኖኅ መርከብ አሠራር ይበልጥ ለማወቅ ችለናል። በጣም እናመሰግናለን።

ቲ. ኤ.፣ ጃፓን

የስድስት ዓመቱ ልጄ የተለያዩ ነገሮችን አስመስሎ መሥራት ይወዳል። በዚህ ርዕሰ ትምህርት መጨረሻ ላይ የኖኅን መርከብ የሚመስል ሞዴል እንዴት መሥራት እንደሚቻል የሚያሳይ መመሪያ መኖሩን ስንመለከት እኔም ሆንኩ ልጄ በጣም ተደሰትን። ግሩም በሆነው ርዕሰ ትምህርት ታግዘን ሞዴሉን በመሥራት ከሰዓት በኋላ አስደሳች ጊዜ አሳለፍን! አመሰግናችኋለሁ። ሩጫ በሚበዛበትና ልጆቻችን ከሳምንት እስከ ሳምንት በትምህርት ቤት የሚደረግባቸው ግፊት እያየለ በመጣበት በዚህ ዘመን ወላጆች ልጆቻቸውን በይሖዋ መንገድ ለማሳደግ የሚያግዝ እንደ ንቁ! መጽሔት ያለ መሣሪያ ማግኘታቸው እንዴት ያለ በረከት ነው!

ኤም. ኤፍ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የወጣቶች ጥያቄ . . . ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው? (ኅዳር 2006) ይህን ርዕሰ ትምህርት አንብቤ ይሖዋ ምን ያህል ስለ እኛ እንደሚያስብና ችግሮቻችንን እንድንፈታ እንደሚረዳን ሳውቅ ልቤ በጣም ተነካ። ምንም እንኳ መጥፎ ልማድ እያገረሸ ቢያስቸግረንም ይሖዋ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ የሆነ አምላክ ነው። (መዝሙር 86:5) እኛ ወጣቶች ይህን ማወቃችን ‘ከወጣትነት ክፉ ምኞት እንድንሸሽ’ ይረዳናል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

ቪ. ኤፍ. ኤፍ.፣ ብራዚል

የወጣቶች ጥያቄ . . . ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው? (ታኅሣሥ 2006) ለስድስት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠና ቆይቻለሁ። ምንም እንኳ ወላጆቼ በጣም ጥብቅ ቢሆኑብንም ስለ እኔ ከልብ እንደሚያስቡ አውቃለሁ። ይህን ርዕሰ ትምህርት ማንበቤ ወላጆቼ ያለባቸውን ጭንቀት እንድረዳና ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያስብልኝ መሆኑን እንድገነዘብ አድርጎኛል።

ኬ. ቲ.፣ ታይላንድ

ኮብላይ ልጅ ነበርኩ (ታኅሣሥ 2006) ስለ ይሖዋ መማር የጀመርኩት ከ1992 አንስቶ ነው። ይሁን እንጂ ሌላ የሕይወት ጎዳና ለመከተል የመረጥኩበት ጊዜ ነበር። ልክ እንደ ሜሮስ ሰንዴይ እኔም ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ፤ ከይሖዋ ከኮበለልኩ ከሦስት ዓመታት በኋላ እሱ እንዲረዳኝ መጠየቅ ጀመርኩ። አሁን እንደገና ወደ “ቤቱ” ተመልሻለሁ! ለምታከናውኑት ሥራ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

ዲ. ኬ.፣ ዩክሬን

የወጣቶች ጥያቄ . . . ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር የምችለው መቼ ነው? (ጥር 2007) ዕድሜዬ 15 ነው። አክስቴንና ባለቤቷን ለመጠየቅ ሄጄ በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንድ የ17 ዓመት ልጅ ጋር ተዋወቅሁ። ከዚያም አልፎ አልፎ በኢንተርኔት አማካኝነት ማውራት ጀመርን። ሳናውቀው በየቀኑ ማውራት ጀመርንና ሁለታችንም ፍቅር ያዘን። በኋላም ይህን ርዕሰ ትምህርት ሳነብ በእርግጥም ምንም ዓይነት የጋብቻ ሐሳብ ሳይኖረን የፍቅር ጓደኝነት መሥርተን እንደነበር ተገነዘብኩ። በወላጆቼና በንቁ! መጽሔት እርዳታ ከልጁ ጋር የነበረኝን ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት በማቋረጥ ግሩም ውሳኔ አደረግሁ። አሁን ከልጁ ጋር ንጹሕ ጓደኛሞች ስንሆን ከይሖዋ ጋር ላለኝ ግንኙነት ቅድሚያ እሰጣለሁ። ይህ ርዕሰ ትምህርት እውነታውን እንዳስተውል ስለረዳኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ዲ. ዲ.፣ ካናዳ