በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንጀል ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል?

ወንጀል ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል?

ወንጀል ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል?

▪ እስከ አፍንጫው ድረስ መሣሪያ የታጠቀ አንድ የአእምሮ ሕመምተኛ አብረውት የሚማሩትን ተማሪዎችና መምህራኑን ፈጃቸው።

▪ አንዲት ትንሽ ልጅ ታፍና ስለተወሰደች ወላጆቿ ከፍተኛ ሐዘን ላይ ወድቀዋል።

▪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት መግደል ደስታ እንደሚያስገኝ ስለተሰማው ብቻ ሰው ገድሎ አስከሬኑን ለጓደኞቹ እንዳሳያቸው አምኗል፤ ጓደኞቹም ጉዳዩን ለሳምንታት በምሥጢር ይዘውለት ነበር።

▪ ሕፃናትን በጾታ የሚያስነውር አንድ ሰው ልጆችን ማጥመድ ስለሚቻልበት መንገድ እንደ እሱ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ሐሳብ ይለዋወጣል።

እነዚህ ዘገባዎች በዛሬው ጊዜ በዜና ከምንሰማቸው ዘግናኝ ወንጀሎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በምትኖርበት አካባቢ፣ በተለይ ምሽት ላይ ወደ ውጭ ስትወጣ ፍርሃት አይሰማህም? አንተ ወይም ደግሞ ቤተሰብህ ወንጀል ተፈጽሞባችሁ ያውቃል? በአንድ ወቅት በአንፃራዊ ሁኔታ ከወንጀል ነፃ እንደሆኑ ይቆጠሩ በነበሩ አገሮች የሚኖሩትን ጨምሮ በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ወንጀልና ጥቃት ይፈጸምብናል ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል። እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ከተለያዩ አገሮች የተገኙ አጫጭር ዘገባዎች እንመልከት።

ጃፓን:- ኤዥያ ታይምስ እንዲህ ብሏል:- “በአንድ ወቅት ጃፓን በዓለም ላይ ወንጀል ብዙም እንደማያሰጋቸው ከሚነገርላቸው አገሮች አንዷ ነበረች። . . . አሁን ግን ሰዎች እንደቀድሞው ከስጋት ነፃ የሆነ ሕይወት መምራት አልቻሉም፤ እንዲሁም አገራቸው ከስጋት ነፃ እንደሆነች የነበራቸው ስሜት ወንጀልና ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ባስከተሉት ከፍተኛ ጭንቀት ተተክቷል።”

ላቲን አሜሪካ:- በብራዚል ያሉ እውቅ ሰዎች በሳኦ ፓውሎ ከተማ ውስጥ የደፈጣ ውጊያ እንደሚነሳ መተንበያቸውን በ2006 የወጣ አንድ የዜና ዘገባ ይናገራል። አልፎ አልፎ በሚከሰትና ለሳምንታት በሚዘልቅ ዓመጽ የተነሳ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የጦር ሠራዊቱ በአስቸኳይ በከተማዋ ውስጥ እንዲሠማራ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። በማዕከላዊ አሜሪካና በሜክሲኮ “በወንበዴ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 50,000 ያህል ታዳጊ ወጣቶች መኖራቸው በእነዚህ ቦታዎች ያሉት ባለ ሥልጣናት ሁኔታዎችን በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተሉ አድርጓቸዋል” በማለት ትየምፖስ ዴል ሙንዶ በተሰኘ ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ ይናገራል። ጋዜጣው ሐተታውን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በ2005 ብቻ በኤል ሳልቫዶር፣ በሆንዱራስና በጓቲማላ 15,000 የሚያህሉ ሰዎች በወንበዴ ቡድኖች ውስጥ በሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ተገድለዋል።”

ካናዳ:- “ከወንጀል ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያጠኑ ባለሙያዎች የወንበዴ ቡድኖች ቁጥር መጨመር አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል” በማለት ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በ2006 እትሙ ላይ ዘግቦ ነበር። “ፖሊስ . . . በቶሮንቶ ጎዳናዎች ላይ 73 የወንበዴ ቡድኖች እንደሚንቀሳቀሱ ማወቅ ችሏል።” ይኸው ምንጭ እንደገለጸው ከሆነ በከተሞች ውስጥ እያሻቀበ ያለውን የወንበዴ ቡድኖች ቁጥር ለመቀነስ የሚያስችል መፍትሔ ማግኘት ቀላል አለመሆኑን የቶሮንቶ ፖሊስ አዛዥ በግልጽ ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ:- ከወንጀል ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያጠኑት ፓትሪክ በርትን ፋይናንሻል ሜይል በሚል ርዕስ ኢንተርኔት ላይ ባወጡት ሐተታ እንደገለጹት “የወንጀል ፍርሃት የወጣት ደቡብ አፍሪካውያንን አጠቃላይ ሕይወት ተቆጣጥሮታል።” “በመሣሪያ በማስፈራራት የሚፈጸም ዝርፊያ፣ የአውሮፕላን ጠለፋና የባንክ ዝርፊያ የመሳሰሉት ከባድ ወንጀሎች” ሰዎች ስጋት እንዲያድርባቸው ከሚያደርጉት የወንጀል ድርጊቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ፈረንሳይ:- በርካታ የቁጠባ ቤቶች ነዋሪዎች “[ወንጀለኞች ሆን ብለው] በሰባበሯቸው ደረጃዎች ሲጠቀሙ፣ አደገኛ በሆኑ የመኪና ማቆሚያዎች መኪናቸውን ሲያቆሙ እንዲሁም ከመሸ በኋላ ለአደጋ በሚያጋልጡ የሕዝብ መጓጓዣዎች ሲገለገሉ” በየዕለቱ ስጋት ያድርባቸዋል።—ጋርዲያን ዊክሊ

ዩናይትድ ስቴትስ:- የተደራጁ የወንበዴ ቡድኖች ወንጀል እንዲበዛ አድርገዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ በወጣ አንድ ዘገባ መሠረት በአንድ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት የተካሄደ የፖሊስ ጥናት እንዳመለከተው 700 በሚያህሉት የወንበዴ ቡድኖች ውስጥ ወደ 17,000 የሚጠጉ ወንድና ሴት ወጣቶች ይገኛሉ። ይህም በአራት ዓመታት ውስጥ የአባላቱ ቁጥር በ10,000 መጨመሩን ያሳያል።

ብሪታንያ:- የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ወንጀል በልጆች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ ስላወጣው ዘገባ ዘ ታይምስ የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ እንዲህ ብሏል:- “ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ የብሪታንያ ወጣቶች በሽጉጥ እየተገደሉ ነው። . . . የገዳዮቹም ሆነ የወንጀሉ ሰለባዎች ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።” በእንግሊዝና በዌልስ ያለው የእስረኞች ቁጥር ወደ 80,000 ተቃርቧል።

ኬንያ:- መኪና በሚበዛበት አውራ ጎዳና አቅራቢያ አንዲት እናትና ሴት ልጇ ከመኪናቸው ውስጥ በፍጥነት ባለመውጣታቸው በመኪና ጠላፊዎች እንደተተኮሰባቸው አንድ የዜና ዘገባ ይናገራል። የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የመኪና ጠለፋን፣ ማጅራት መቺነትንና ሰዎችን ቤታቸው ገብቶ ማጥቃትን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ወንጀል የሚፈጸምባት በመሆን የታወቀች ሆናለች።

ወንጀል ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው? የወንጀል ዋነኛ መንስኤ ምንድን ነው? ሰዎች እውነተኛ ሰላምና ጸጥታ አግኝተው የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት ይኖር ይሆን? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራሉ።