በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

በፍጥረት እንደማምን በደንብ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

“በክፍል ውስጥ በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ስማረው የኖርኩትን ነገር ሁሉ አጠያያቂ አደረገብኝ። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውነት እንደሆነ ተደርጎ መቅረቡ ያሸማቅቀኝ ነበር።”—የ18 ዓመቱ ራየን

“የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዝግመተ ለውጥ አጥብቃ የምታምን አስተማሪ ነበረችኝ። እንዲያውም በመኪናዋ ላይ የዳርዊንን ምልክት ትለጥፋለች! ይህም በፈጣሪ እንደማምን በግልጽ ለመናገር እንድፈራ አድርጎኝ ነበር።”—የ19 ዓመቱ ታይለር

“የኅብረተሰብ ትምህርት መምህሬ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ የምንማረው ስለ ዝግመተ ለውጥ መሆኑን ስትናገር በጣም ፈርቼ ነበር። በዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ ረገድ አቋሜን በክፍል ውስጥ ማስረዳት እንደሚጠበቅብኝ አውቅ ነበር።”—የ14 ዓመቷ ራኬል

አንተም እንደ ራየን፣ ታይለርና ራኬል በክፍል ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ርዕስ ሲነሳ ትጨነቅ ይሆናል። አንተ የምታምነው ‘ሁሉን የፈጠረው’ አምላክ መሆኑን ነው። (ራእይ 4:11) በዙሪያህ የምትመለከተው ነገር ሁሉ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀበት ነው። ይሁን እንጂ የመማሪያ መጻሕፍቱና አስተማሪህም ጭምር ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው ይላሉ። ታዲያ አንተ ማን ሆነህ ነው እነዚህን ሁሉ “ሊቃውንት” የምትሟገተው? ደግሞስ ስለ አምላክ መናገር ብትጀምር የክፍል ጓደኞችህ ምን ይላሉ?

እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች የሚያስጨንቁህ ከሆነ አይዞህ! በፍጥረት የምታምነው አንተ ብቻ አይደለህም። እንዲያውም በርካታ የሳይንስ ሊቃውንትም ሳይቀር የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉትም። ብዙ መምህራንም ቢሆኑ በዝግመተ ለውጥ አያምኑም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር የመማሪያ መጻሕፍቱ ከሚያቀርቡት ሐሳብ በተቃራኒ ከ5 ተማሪዎች መካከል 4ቱ በፈጣሪ ያምናሉ።

ያም ቢሆን ‘በፍጥረት እንደማምን ማስረዳት ቢኖርብኝ ምን እላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ሁኔታው ቢያስፈራህም እንኳ በልበ ሙሉነት አቋምህን መግለጽ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ዝግጅት ይጠይቃል።

በመጀመሪያ እምነትህን ፈትሽ!

ወላጆችህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆኑ በፍጥረት የምታምነው እነርሱ ስላስተማሩህ ይሆናል። አሁን ግን እያደግህ ስትሄድ ለእምነትህ ጽኑ መሠረት ኖሮህ ‘በአእምሮህ’ ተጠቅመህ አምላክን ማምለክ ትፈልጋለህ። (ሮሜ 12:1) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች “ሁሉን ነገር ፈትኑ” በማለት አበረታቷቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) አንተስ ስለ ፍጥረት ባለህ እምነት ረገድ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ጳውሎስ ስለ አምላክ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል።” (ሮሜ 1:20) እነዚህን ቃላት በአእምሮህ ይዘህ የሰውን አካል፣ መሬትን፣ ሰፊ የሆነውን ጽንፈ ዓለምና የውቅያኖስን ጥልቆች መርምር። አስደናቂ ከሆነው የነፍሳት፣ የዕፅዋትና የእንስሳት ዓለም ውስጥ አንተን የሚማርክህን መስክ መርጠህ አሰላስል። ከዚያም ‘በአእምሮህ’ ተጠቅመህ ራስህን ‘ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳምነኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ጠይቅ።

ይህን ጥያቄ ለመመለስ የ14 ዓመቱ ሳም የሰውን አካል በምሳሌነት ይጠቅሳል። “እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄ የተሠራ ከመሆኑም በላይ ውስብስብ ነው” ብሏል። አክሎም “ሁሉም የአካል ክፍሎች ግሩም በሆነ ሁኔታ ተቀናጅተው ይሠራሉ። የሰው አካል የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ሊሆን አይችልም!” ይላል። ሆሊ የተባለችው የ16 ዓመት ልጃገረድም ሳም በተናገረው ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ትላለች:- “የስኳር በሽታ እንዳለብኝ ከተነገረኝ ጊዜ ጀምሮ የሰው አካል እንዴት እንደሚሠራ ብዙ ተምሬያለሁ። በጣም አስገራሚ ነው። ለምሳሌ ጣፊያ፣ በጨጓራና በአንጀት አካባቢ የምትገኝ አንዲት ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ደምና ሌሎች የአካላችን ክፍሎች በትክክል መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ታበረክታለች።”

ሌሎች ወጣቶች ደግሞ በፈጣሪ የማመንን ጉዳይ የሚመለከቱት ከሌላ አቅጣጫ ነው። የ19 ዓመቱ ጄረድ እንዲህ ብሏል:- “ለእኔ ትልቁ ማስረጃ መንፈሳዊ ነገሮችን የምንፈልግ መሆናችን እንዲሁም ውበትን ማድነቃችንና የመማር ፍላጎት ያለን መሆኑ ነው። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሊያሳምነን እንደሚፈልገው እነዚህ ባሕርያት ለመኖር የሚያስፈልጉን አይደሉም። ሊያሳምነኝ የሚችለው ብቸኛው ማብራሪያ እነዚህ ባሕርያት ሊኖሩን የቻሉት በመኖር እንድንደሰት በሚፈልግ አካል ስለተፈጠርን መሆኑ ነው።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ታይለርም ከዚሁ ድምዳሜ ላይ ደርሷል። እሱም “ዕፅዋት ሕይወት እንዲቀጥል የሚጫወቱትን ሚና እንዲሁም አስደናቂ የሆነውን የአፈጣጠራቸውን ውስብስብነት ሳስብ ፈጣሪ እንዳለ እርግጠኛ እሆናለሁ” ብሏል።

ሁሉም ነገር የተገኘው አምላክ ፈጥሮት መሆኑን አስቀድመህ በጥንቃቄ ካሰብክበትና ይህንንም ከልብ ካመንክበት ይህን እምነትህን መግለጽ ቀላል ይሆንልሃል። ስለዚህ አንተም እንደ ሳም፣ ሆሊ፣ ጄረድና ታይለር የአምላክን ድንቅ የእጅ ሥራዎች ጊዜ ወስደህ አሰላስልባቸው። ከዚያም እነዚህ ፍጥረታት “የሚነግሩህን” ነገር ልብ ብለህ “አድምጥ።” እንዲህ ካደረግህ፣ አምላክ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ባሕርያቱንም ጭምር ‘ከፍጥረቱ በግልጽ ማየት’ እንደሚቻል በተናገረው በሐዋርያው ጳውሎስ አባባል አንተም እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። *

ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እወቅ

ስለ ፍጥረት በሚገባ ለማስረዳት አምላክ የሠራቸውን ነገሮች በጥልቀት ከመመልከትም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ሐሳብ በማይሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ መከራከር አያስፈልግህም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት:-

የሳይንስ መማሪያ መጽሐፌ መሬትና ሥርዓተ ፀሐይ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደኖሩ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሬትና ስለ ሥርዓተ ፀሐይ ዕድሜ አይናገርም። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ዘገባ፣ ጽንፈ ዓለም በአጠቃላይ የመጀመሪያው የፍጥረት “ቀን” ከመጀመሩ አስቀድሞ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደነበረ ሳይንስ ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ዘፍጥረት 1:1, 2

አስተማሪዬ፣ ምድር በስድስት ቀናት ውስጥ ልትፈጠር እንደማትችል ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስድስቱ የፍጥረት “ቀናት” እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝማኔ እንደነበራቸው አይገልጽም። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ መጽሔት ላይ ከገጽ 18-20 ተመልከት።

እንስሳትና ሰዎች በጊዜ ሂደት እንዴት እንደተለወጡ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች በክፍል ውስጥ ቀርበው ውይይት አድርገንባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች “እንደየወገናቸው” እንደፈጠረ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:20, 21) ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር እንደመጣ ወይም አምላክ በአንድ ሴል አማካኝነት የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንዳስጀመረ የሚገልጸውን ሐሳብ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም። ቢሆንም ከእያንዳንዱ ‘ወገን’ በርከት ያሉ ዓይነቶች ሊገኙ ይችላሉ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ‘ወገን’ ውስጥ ለውጥ እንደሚከሰት የሚገልጸውን ሐሳብ አይቃወምም።

ስለ እምነትህ እርግጠኛ ሁን!

በፍጥረት የምታምን በመሆንህ የምትሸማቀቅበት ወይም የምታፍርበት ምንም ምክንያት የለም። ማስረጃዎቹን ሁሉ ከመረመርን፣ ድንቅ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንደሠራን ማመን ፍጹም ምክንያታዊ አልፎ ተርፎም ከሳይንስ ጋር የሚስማማ ሆኖ እናገኘዋለን። ያላንዳች አሳማኝ ማስረጃ ከፍተኛ እምነት እንድናሳድርና ተአምር ሠሪ ሳይኖር በተፈጸመ ተአምር እንድናምን የሚጠይቅብን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንጂ በፈጣሪ ማመን አይደለም። እንዲያውም በዚህ ንቁ! መጽሔት ላይ የቀረቡትን ሌሎች ርዕሰ ትምህርቶችም ከመረመርክ በኋላ ማስረጃው የሚደግፈው ሁሉም ነገር የተገኘው አምላክ ስለፈጠረው ነው የሚለውን እምነት መሆኑን እርግጠኛ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም። ደግሞም በማሰብ ኃይልህ ተጠቅመህ ጉዳዩን በጥንቃቄ ካጤንከው በክፍል ውስጥ ለዚህ እምነትህ ጥብቅና ለመቆም ድፍረት ይኖርሃል።

ቀደም ሲል የጠቀስናት ራኬል የተገነዘበችው ይህንን ነው። “እምነቴን ሸሽጌ ዝም ማለት እንደሌለብኝ ለመገንዘብ ጥቂት ቀናት ወስዶብኛል” ትላለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “ለአስተማሪዬ፣ ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ ላይ በተለይ እንድትመለከታቸው የምፈልጋቸውን ክፍሎች አስምሬ ሰጠኋት። ከዚያ በኋላ መጽሐፉ የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ከተለየ አቅጣጫ እንድትመለከተው እንደረዳትና ለወደፊቱ ስለ ዝግመተ ለውጥ ስታስተምር ከዚህ መጽሐፍ ያገኘችውን እውቀት ግምት ውስጥ እንደምታስገባ ነገረችኝ!”

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ብዙ ወጣቶች ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? እና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? በተሰኙት የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ውስጥ የሠፈሩትን መረጃዎች በመመርመር ተጠቅመዋል። ሁለቱም መጻሕፍት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ስለ ፍጥረት ያለህን እምነት በትምህርት ቤት ሳትሸማቀቅ ለመናገር የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

▪ ሁሉንም ነገሮች ለፈጠረው አምላክ ያለህን አድናቆት እንዴት ልታሳይ ትችላለህ?—የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ማስረጃ ሞልቷል”

“ወላጆቹ በፈጣሪ እንዲያምን ላስተማሩትና በትምህርት ቤት ግን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ እየተማረ ላለ ወጣት ምን ትይዋለሽ?” ይህ ጥያቄ ማይክሮባዮሎጂስት ለሆነች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቀርቦላት ነበር። መልሷ ምን ነበር? “በአምላክ መኖር የምታምነው ወላጆችህ ስላስተማሩህ ብቻ ሳይሆን አንተው ራስህ ማስረጃውን መርምረህ ወደዚህ መደምደሚያ ስለደረስህ መሆኑን ለራስህ ለማረጋገጥ እንደሚያስችልህ አጋጣሚ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። አንዳንድ ጊዜ መምህራን የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ‘እንዲያረጋግጡ’ ሲጠየቁ ይህን ማድረግ እንደማይችሉና ይህን ጽንሰ ሐሳብ የተቀበሉት ስለተማሩት ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንተም በፈጣሪ ላይ ባለህ እምነት ረገድ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊገጥምህ ይችላል። በእርግጥ አምላክ መኖሩን ለራስህ ማረጋገጥህ ጠቃሚ የሚሆነው ለዚህ ነው። ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሞልቷል። ይህን በተመለከተ ማስረጃ ማግኘት አዳጋች አይደለም” ብላለች።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንተን የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

ፈጣሪ መኖሩን አንተ እንድታምን ያደረጉህን ሦስት ነገሮች ከዚህ በታች ዘርዝር:-

1. ......

2. ......

3. ......