በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተለያዩ ነገሮችን የመሰበሰብ ልማድ ሚዛናዊ መሆን ይጠይቃል

የተለያዩ ነገሮችን የመሰበሰብ ልማድ ሚዛናዊ መሆን ይጠይቃል

 የተለያዩ ነገሮችን የመሰበሰብ ልማድ ሚዛናዊ መሆን ይጠይቃል

በአውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“አንድ ቀን” ይጠቅመኝ ይሆናል እያልክ እቃ የማከማቸት ልማድ አለህ? እቃዎቹ ምንም ተግባራዊ ጠቀሜታ እንደሌላቸው በምትገነዘብበት ጊዜ ትጥላቸው ይሆናል። የሚገርመው ነገር ብዙዎች ምንም ተግባራዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን እቃዎች መሰብሰብ ያስደስታቸዋል። እንዲህ የሚያደርጉት በትርፍ ጊዜያቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች የመሰብሰብ ልማድ ያላቸው ሰዎች ናቸው።

አንዳንዶች የሚሰበስቡት በጣም የተለመዱ ይኸውም ድንጋይ፣ ቴምብር፣ የድሮ ሳንቲሞችና የመሳሰሉ ነገሮችን ነው። ሌሎች ደግሞ የሰውና የእንስሳት አሻንጉሊቶችን፣ ማንኪያዎችን፣ ሜዳልያዎችን፣ ፖስት ካርዶችን፣ ጥንታዊ ቁሳቁሶችን፣ የተቀዱ ዘፈኖችን ወይም ያሳለፉትን የእረፍት ጊዜ የሚያስታውሱ ነገሮችን መሰብሰብ ያስደስታቸዋል። ሰዎች መሰበሰብ የሚፈልጓቸው ነገሮች ስፍር ቁጥር የላቸውም! ለምሳሌ አንድ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ጠበቃ ወደ 200,000 የሚጠጉ የባቡር ሐዲድ ምስማሮች ሰብስበዋል! እኚህ ሰው፣ በአናታቸው ላይ ቀን የተጻፈባቸው ያረጁ የባቡር ሐዲድ ምስማሮችን ለማግኘት ገጠር ከሚያስሱ በመቶዎች ከሚቆጠሩት የመሰብሰብ ልማድ ካላቸው ሰዎች አንዱ ናቸው።

ሃርፐርስ ማገዚን እንዲህ ሲል ጠቅሷል:- “ሰዎች ከሚሰበስቧቸው በጣም የሚያስገርሙ ነገሮች መካከል ጥርሶች፣ ሰው ሠራሽ ፀጉሮች፣ የራስ ቅሎች፣ የብስኩት ማስቀመጫዎች፣ የድሮ የመጓጓዣ መኪና ትኬቶች፣ ፀጉር፣ የፊት ማራገቢያዎች፣ ወላንዶዎች፣ ጉጠቶች፣ ውሾች፣ ሳንቲሞች፣ ከዘራዎች፣ የካናሪ ወፎች፣ ጫማዎች፣ . . . አዝራሮች፣ አጥንቶች፣ የባርኔጣ  ማያያዣ መርፌ ቁልፎች፣ የሐሰት ፊርማዎች፣ የጽሑፎች የመጀመሪያ እትሞችና የመርዝ ጋዝ መከላከያ ጭምብሎች ይገኙባቸዋል።”

ከተለመዱት ለየት ያሉ ነገሮችን የመሰብሰብ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም አሉ። አንዲት የሩሲያ ባለ ሥልጣን ሚስት ሀብታምና ታዋቂ የነበሩ ሰዎችን ፖፖ ሰብስበዋል። አንድ ጃፓናዊ እንደራሴ ደግሞ 5,000 ውሾችን ሰብስበው በጣም ያጌጡ የውሻ ቤቶች አዘጋጅተው አስቀምጠዋቸዋል። ሃርፐርስ ማገዚን እንደዘገበው የመሰብሰብ ልማድ ያላቸው አንድ ሀብታም ሰው በሺዎች የሚቆጠሩ ቁንጫዎችን “በአልኮል አድርቀው ለየብቻ በተለያየ እቃ ውስጥ አስቀምጠዋቸዋል፤ በየእቃው ላይ የተገኙበትን ቦታና ያገኙበትን ሰው ወይም እንስሳ ስም አስፍረዋል።”

ለየት ያሉ ነገሮችን በመሰብሰብ በኩል የሚጠቀሱ ሰዎች ቢኖሩም ይህ ልማድ በዘመናችን የተፈጠረ አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል መጻሕፍትንና የብራና ጽሑፎችን በመሰብሰብ ማከማቸት ጥንትም ቢሆን የነበረ ልማድ ነው። ላይት ፍሮም ዚ ኤንሸንት ፓስት የተባለው መጽሐፍ የአሦር ንጉሥ የነበረው አሽርባኒፓል (ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው መቶ ዘመን) ቀደም ብለው የተጻፉ ታሪኮችንና ሰነዶችን ገልብጠው በነነዌ ወደሚገኘው ቤተ መጻሕፍቱ እንዲያመጡለት እንዴት አድርጎ ጸሐፊዎቹን በየቦታው እንደላካቸው ይናገራል። ይህንን አስደናቂ ቤተ መጻሕፍት የያዘው የአሽርባኒፓል ቤተ መንግሥት በ1853 በቁፋሮ ተገኝቷል።

የግሪክና የሮም መኳንንትም እንዲሁ የሥነ ጥበብ ውጤቶችን በመሰብሰብ ልማዳቸው ይታወቁ ነበር። ኮሌክቲንግ—አን አንሩሊ ፓሽን (የተለያዩ ነገሮችን መሰብሰብልጓም ያልተበጀለት አመል) የተባለው መጽሐፍ “በሲሴሮና በቄሳር ዘመን ሮም ገንና የምትታይ የድል አድራጊዎች ግዛትና የተገኘውን ጥሩ ነገር ሁሉ የምትሰበስብ ከተማ ነበረች። . . . የሥነ ጥበብ ውጤት አሻሻጮች በከተማዋ ማዕዘን ሁሉ ይገኙ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ሀብታም የአገሪቱ ነዋሪዎች የግል ቤተ መዘክር ነበራቸው” በማለት ዘግቧል።

አንዳንድ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን መሰብሰብ የሚወዱት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን የመሰብሰብ ልማድ ያዳበሩት ለምንድን ነው? ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና “ሰዎች በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ቢሆንም ተቀዳሚ ግባቸው ደስታ ማግኘት ነው። የትርፍ ጊዜ ሥራዎች መንፈስን የሚያድሱ ከመሆናቸውም በላይ ከተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለየት ያለ ነገር ለማድረግ ያስችላሉ” ሲል ገልጿል። አዎን፤ ብዙዎች የሰበሰቧቸውን በጣም የሚወዷቸው ነገሮች በጥንቃቄ በመመልከት ጊዜ ማሳለፉ ብቻ እንኳ ያስደስታቸዋል።

ካንቤራ ታይምስ በተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጥ ልማዱ ባላቸው ሰዎች የተሰበሰቡ ነገሮች “ፈጽሞ የተረሱ ቦታዎችንና ሰዎችን ለማስታወስ ይረዳሉ። የተሰበሰበው ጥንታዊ ነገር ከሆነ የቀድሞው ትውልድ የነበረውን ጥበብና ራእይ እንድንገነዘብ እንዲሁም የአሁኑ ትውልድ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ እንድናደንቅ ይረዳናል” ብሏል። በእርግጥም፣ የአንዳንድ ነገሮች መሰብሰብ ትምህርት ሰጪ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሬክስ ናን ኪቬል የተባሉ የተለያዩ ነገሮችን በመሰብሰብ ልማዳቸው የሚታወቁ በአውስትራሊያ የሚኖሩ ሰው ነበሩ። እኚህ ሰው ከአውስትራሊያና ከኒው ዚላንድ የጥንት ታሪክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን 15,000 የሚያክሉ እቃዎች ሰብስበዋል።

ይህ ልማድ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የተሰበሰቡት ነገሮች የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት መኖሩ ብቻ ሊሆን ይችላል። ዩትኔ ሪደር “በትርኢቱ ላይ ያልተገኙ ሰዎች  ‘በ1969 በዉድስቶክ ተደርጎ የነበረውን [የሮክ ሙዚቃ ትርኢት] የመግቢያ ትኬቶች’ ከትክክለኛነታቸው ማረጋገጫ ደብዳቤ ጋር በ80 ዶላር የመግዛታቸው ምስጢር ምን ሊሆን ይችላል? . . . በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ ከሆነ ባሕል ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቁሳቁሶች መሰብሰብ አትራፊ ንግድ እየሆነ መጥቷል” በማለት ዘግቧል።

ነገር ግን ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል። ዘ ካንቤራ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “እቃዎችን መሰብሰብ ደስታ የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን ስውር ወጥመዶችም አሉት። ሁሉም ሻጮች እውነተኞች ናቸው ማለት ያስቸግራል፤ ብዙ ነገሮች ዋጋማ ቢመስሉም ሥርዓት የለሾችና ግብረ ገብነት የጎደላቸው ሰዎች አስመስለው የሠሯቸው የሐሰት እቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ።” አንድ ሰው “የገዛው እቃ” ዋጋ የሌለው የሐሰት ሥራ መሆኑን ሲረዳ ምን ያህል ያዝን ይሆን! ስለዚህ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” የሚሉት የምሳሌ 14:15 ቃላት አንዳንድ ነገሮችን በሚሰበስቡ ሰዎችም ላይ ይሠራል።

ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል

በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮችን መሰብሰብ በጣም ብዙ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ይጠይቃል። እቃዎችን የምትሰበስብ አንዲት ሴት ይህ ልማዷ “ከልክ በላይ እረፍት እንደነሳት” ተናግራለች። ዕድሜ ልካቸውን እቃ ሲሰበስቡ የኖሩ አለስታር ማርቲን የተባሉ ሰው የመሰብሰብ ልማድ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች “ባሕርያቸው ሁሉ ከሰው እንደማይገጥም” አምነው ተቀብለዋል።

ቬርነር ምዌንስተርቤርገር የተባሉ ሰው ኮሌክቲንግ—አን አንሩሊ ፓሽን በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “አንድ ሰው የተለያዩ ነገሮችን የመሰብሰብ ልማድ ያላቸውን ሰዎች ሥራዬ ብሎ ቢከታተል ብዙም ሳይቆይ የሚፈልጉትን ነገር የማግኘት ፋታ የማይሰጥ ፍላጎትና ረሃብ እንዳላቸው መገንዘቡ አይቀርም። . . . የሚያስገርመው ሰዎቹ እንዲያው ለየት ያለ የመሰብሰብ ልማድ ያላቸው መሆኑ ሳይሆን ብዙዎቹ በግልጽ የሚያንጸባርቁት እንግዳ የሆነው ባሕርያቸው፣ እቃዎችን ለማግኘት ያላቸው ቁርጠኝነት፣ የሚፈልጉትን ሲያገኙ የሚታይባቸው ደስታ ወይም ሲያጡ የሚነበብባቸው ሐዘን እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚያሳዩት ከሰው የማይገጥም አስተሳሰብና ጠባይ ነው” በማለት ጽፈዋል።

አንድ ክርስቲያን በትርፍ ጊዜው መሥራት የሚያስደስተው ማንኛውም ልማድ ጥበብ ወደ ጎደለው ወይም አሳፋሪ ወደ ሆነ ጽንፍ እንዲመራው ሊፈቅድለት ይገባል? በፍጹም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ራሳችሁን ግዙ’ በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ጴጥሮስ 1:13) የትርፍ ጊዜ ሥራ አስደሳች ቢሆንም አምላካዊ አክብሮት ያለውን ሰው ከሚያሳስቡት ‘ከሁሉ የሚሻሉ’ ነገሮች መካከል አንዱ አይደለም። (ፊልጵስዩስ 1:10) በዚህ ጉዳይ ላይ ከንጉሥ ሰሎሞን ትምህርት መቅሰም እንችላለን። ያለውን በርካታ ሀብት በመጠቀም አስደናቂ የሆኑ ቤቶችን፣ የወይን አትክልት ቦታዎችን፣ ዛፎችና ከብቶችን አከማችቶ ነበር። ሰሎሞን “ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም” በማለት ገልጿል። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት መድከሙ እውነተኛ እርካታ አምጥቶለታል? ሰሎሞን መልስ ሲሰጥ “እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር” ብሏል።—መክብብ 2:3-11

አንዳንድ ነገሮችን ለመሰብሰብ ያለህ ፍላጎት ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች መስጠት ያለብህን ትኩረት እንዳይሰርቅብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ‘ለዚህ ልማዴ ወይም ጊዜ ማሳለፊያዬ ማጥፋት የምችለው ምን ያህል ጊዜ ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ጊዜህ የሚጠፋው ለማግኘት ያሰብካቸውን ነገሮች በመፈለግ ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ይገባሃል። የሰበሰብካቸውን ነገሮች ለመንከባከብ፣ አዘውትረህ ለማጽዳት፣ ለመደርደር፣ እየተመለከትህ ለማድነቅና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመጠበቅ ጊዜ ያስፈልግሃል። ገንዘብንስ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? ይህ ልማድህ ቤተሰብህን ልትንከባከብበት የሚገባውን ሀብትህን ያሟጥጥብህ ይሆን? (1 ጢሞቴዎስ 5:8) አቅምህ የማይፈቅደውን ነገር እንድትገዛ በምትጠየቅበት ጊዜ ራስህን ተቆጣጥረህ እንደማትችል ትገልጻለህ? መዘንጋት የማይኖርብህ፣ ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲህ በቀላሉ መሰብሰብ አትችልም። ሰሎሞን “ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል” በማለት ስለ መጻሕፍት የተናገራቸው ቃላት ለሚሰበሰቡ ነገሮችም ይሠራል። (መክብብ 12:12) ስለዚህ ክርስቲያናዊ መመሪያዎችን በመከተል ሚዛንን መጠበቅ ያስፈልጋል።

ከላይ እንደተጠቀሰው አንዳንድ ነገሮችን የመሰብሰብ ልማድ “ልጓም ያልተበጀለት አመል” ተብሏል። ነገር ግን እንዲህ ሊሆን አይገባውም። ለዚህ ልማድ ሚዛናዊ አመለካከት ኖሮን በመጠኑ ካከናወንነው መንፈስን የሚያድስ፣ የሚያስደስትና ምናልባትም ትምህርት የምንቀስምበት ጊዜ ማሳለፊያ ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማንኛውም የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ የሚጠይቀውን ጊዜና ወጪ አስቀድመን ማስላታችን ተገቢ ነው