በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ቁጣ የልብ ሕመም ያስከትላል

“በቀላሉ የሚበሳጩ ወይም ቂም የሚይዙ ወንዶች ኤትሪያል ፊብሪሌሽን ለተባለ የልብ ሕመም ስለሚጋለጡ የልብ ምታቸው የተዛባ ይሆናል” ሲል የኒው ዮርኩ ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል። ቁጡ ወይም ትዕግሥት የለሽ የሆኑ፣ ሲበሳጩ አንደበታቸውን መቆጣጠር የሚሳናቸው ወይም ደግሞ ሌሎች ሲተቿቸው በጣም የሚናደዱ ወንዶች ለተዛባ የልብ ምት ችግር የሚጋለጡበት አጋጣሚ 30 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። የጥናት ቡድኑ ዳይሬክተር የሆኑት ኢሌን ኤከር እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “የቁጣን ስሜት ከማፈን ይልቅ አውጥቶ መግለጽ በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ለመከላከል ይረዳል ተብሎ ይታሰብ ነበር። . . . በዚህ ጥናት ላይ እንደታየው ግን ቁጡ የሆኑ ወንዶች ለኤትሪያል ፊብሪሌሽን ብቻ ሳይሆን ሞት ለሚያስከትሉ ሌሎች ችግሮችም የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ እንደሆነ በተጨባጭ ተረጋግጧል።”

ጋብቻና ፍቺ በብሪታንያ

በብሪታንያ “ጋብቻ ካልፈጸሙት ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አገባለሁ የሚል እምነት ‘ጨርሶ እንደሌላቸው’ ይናገራሉ” ሲል የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ሚንተል ኢንተርናሽናል ግሩፕ የተባለው ተቋም ተንታኝ የሆኑት ጄኒ ካትሊን “ይህ ሁኔታ ሰዎች ለጋብቻ ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ እንደመጣ በግልጽ ያሳያል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “በአሁኑ ጊዜ ከትዳር ጓደኛ ጋር በጋብቻ ሳይተሳሰሩ አብሮ መኖርና ልጆች መውለድ ተመራጭ ሆኗል” ብለዋል። ማግባት የሚፈልጉ ሰዎች ለሠርጋቸው የሚያወጡት ወጪ በአማካይ 28,600 ዶላር በመድረሱ ጋብቻን በሌላ አገር መፈጸም የተሻለ አማራጭ እየሆነ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆኑ የብሪታንያ እጮኛሞች ሠርጋቸውን በሌላ አገር መፈጸም ይመርጣሉ። በሠርጋቸው ላይ የሚታደሙት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሚሆንና ረከስ ባለ ዋጋ ድግስ ማዘጋጀት ስለሚቻል በአገራቸው ቢደግሱ ከሚያወጡት ወጪ አንድ ሦስተኛውን ብቻ በመጠቀም ወጪያቸውን መሸፈን ይችላሉ። የጋብቻ ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም የፍቺ ቁጥር ግን እያሻቀበ ነው። “ከትዳር ጓደኛቸው የተፋቱ በዕድሜ የገፉ ሴቶች ቁጥር ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አምስት እጥፍ ያደገ ሲሆን ይህ ቁጥር ወደፊትም እያሻቀበ ይሄዳል የሚል ስጋት አለ” ሲል ቴሌግራፍ ዘግቧል።

የእንግሊዝ ጨው የእርጉዝ ሴቶችን ሕይወት ይታደጋል

የእንግሊዝ ጨው በመጠቀም የሚገኘው ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ሕክምና ለሞት ሊዳርግ የሚችል ከእርግዝና ጋር የተያያዘ ችግር የመከሰቱን አጋጣሚ በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ገልጿል። የጡንቻ መኮማተር የሚያስከትለው ኢክላምፕስያ የሚባል አደገኛ የሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 50,000 የሚያህሉ ሴቶችንና ማህፀናቸው ውስጥ ያለውን ሽል ለሞት ይዳርጋል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የእንግሊዝ ጨው ያለበት ጠብታ ወይም መርፌ ችግሩ ተባብሶ ኢክላምፕስያ የሚባለው ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት በሽታውን ለማከም ለበርካታ ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ቢሆንም ይህ ሕክምና በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ በሰፊው ሳይሠራበት ቆይቷል። በመሆኑም በእንግሊዝ፣ ኦክስፎርድ በሚገኘው የጤና ሳይንስ ተቋም የሚገኝ አንድ ዓለም አቀፍ የዶክተሮች ቡድን “የእንግሊዝ ጨው የሚያስገኘውን ጥቅም ለማየት በ33 አገሮች ውስጥ በ10,000 ሴቶች ላይ ጥናት ለማካሄድ ወሰነ” ሲል ዘ ታይምስ ዘግቧል። “ከሦስት ዓመት በኋላ . . . የእንግሊዝ ጨው በመጠቀም የሚሰጠው ሕክምና ውጤታማ መሆኑ በግልጽ በመታወቁ ጥናቱ ከታሰበለት ጊዜ በፊት እንዲቆም ተደረገ። በሽታው ያሰጋቸው የነበሩ ሴቶች ሕመሙ ኢክላምፕስያ የሚባለው ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የእንግሊዝ ጨው መጠቀማቸው የጡንቻ መኮማተር አደጋን 58 በመቶ ለመቀነስ አስችሏል። ለሕልፈተ ሕይወት የመዳረጋቸው አደጋ ደግሞ 45 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል።” ሕክምናው “የሚጠይቀው ወጪ ለአንዲት ሴት 38 ብር ገደማ ብቻ መሆኑ . . . በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ሴቶችም ከዝግጅቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።”

ልጆችን የማስነወር ድርጊት በሜክሲኮ

ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው ጋዜጣ የሜክሲኮ ሲቲን የፍትሕ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት በመጥቀስ እንደዘገበው “በሜክሲኮ ሲቲ ከ8 ልጃገረዶች መካከል አንዷ እንዲሁም ከ10 ወንዶች ልጆች መካከል አንዱ የማስነወር ድርጊት ይፈጸምባቸዋል።” የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ወላጆችን በልጆቻቸው ላይ ሊፈጸም ስለሚችለው የማስነወር ድርጊት የሚያስጠነቅቁና በልጆቻቸው ላይ ይህ ድርጊት ቢፈጸም ሊወስዱት የሚገባውን እርምጃ የሚጠቁሙ በራሪ ወረቀቶች እያሰራጨ ነው። በበራሪ ወረቀቶቹ ላይ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- (1) ልጆቻችሁ እንደተነወሩ ሲገልጹላችሁ አምናችሁ ተቀበሏቸው እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ አድርጉላቸው። (2) ለተፈጸመባቸው ድርጊት ጥፋተኞቹ እነሱ አለመሆናቸውን ግለጹላቸው። (3) የተፈጸመው ነገር ሕገወጥ መሆኑንና ዳግመኛ እንዲህ ያለ ነገር እንዳይከሰት ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑን ንገሯቸው።

ንቅሳትን ማስለቀቅ

“አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ንቅሳት ካላቸው ሰዎች መካከል ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት በሆነ ወቅት ላይ ንቅሳታቸውን ማስለቀቅ መፈለጋቸው አይቀርም” ይላል የካናዳው ቫንኩቨር ሰን። “የሚነቀሱ ሰዎች ቁጥር በጣም በመጨመሩ ንቅሳታቸውን ለማስለቀቅ የሚፈልጉ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ ሄዷል” ሲሉ አንድ የቆዳ ሐኪም ተናግረዋል። ክንዱ ላይ ተነቅሶት የነበረውን ደማቅ አረንጓዴ አርማ ያስለቀቀው የ27 ዓመቱ ዳን ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። “ንቅሳቱ አሁን ካለኝ እምነትና አቋም ጋር አይሄድም” ሲል ተናግሯል። ይሁንና ዘመናዊ የሆነ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በጨረር አማካኝነት ንቅሳትን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረትም እንኳ ሕመም የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና ጊዜ የሚወስድ ነው። “አነስተኛ የሆነን ንቅሳት ለማስለቀቅ እንኳ ከ8,400 ብር በላይ ሊጠይቅ ይችላል” ይላል ጋዜጣው። “ብዙ ቀለማት ያላቸው ዘመናዊ ንቅሳቶች በተለይ ትልልቅ ከሆኑ ለማስለቀቅ አዳጋች ናቸው” ሲል አክሎ ገልጿል።

ቀሳፊ ጭስ

“በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ምግብ ለማብሰል ሲባል በቤት ውስጥ ከሚቀጣጠለው እሳት የሚወጣው ጭስ በየ20 ሴኮንዱ አንድ ሰው ይገድላል” ሲል በሕንድ፣ ኒው ዴልሂ ውስጥ እየታተመ የሚወጣው ዳውን ቱ ኧርዝ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። “ይህ አኃዝ በወባ በሽታ ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ የሚበልጥ ሲሆን ለመጠጥነት ተስማሚ ባልሆነ ውኃና በንጽሕና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ጋር ይተካከላል።” ንጹሕ አየር በበቂ ሁኔታ በማያገኙ ክፍሎች ውስጥ ከሰልና ኩበት ለማገዶነት መጠቀም በካይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ጉዳት ከማያስከትሉበት መጠን 100 ጊዜ እጥፍ እንዲጨምሩ ስለሚያደርግ በቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ። እነዚህ በካይ ንጥረ ነገሮች ለሳንባ ካንሰር፣ ለአስም፣ ለሳንባ ነቀርሳና ለከባድ የብሮንካይተስ በሽታ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ኢንተርሚዲየት ቴክኖሎጂ ዴቨለፕመንት ግሩፕ የተባለ የምርምር ተቋም ባልደረቦች የሆኑ ጠበብት ብዙም ጭስ የማያስከትሉ ማንደጃዎችን የመጠቀም ኢኮኖሚያዊ አቅም የሌላቸው ሰዎች በጥሩ ሁኔታ የተሠሩ ጭስ ማውጫዎች ያሏቸውን ማንደጃዎች በመጠቀም አደገኛ ለሆነ ጭስ የሚጋለጡበትን አጋጣሚ 80 በመቶ መቀነስ እንደሚችሉ ይናገራሉ። በቤት ውስጥ በሚከሰት የአየር ብከለት ሳቢያ በየዓመቱ ከሚሞቱት 1.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ልጆች ናቸው።

በአጫሾች የተሞላች አህጉር

የአውሮፓ ኅብረት አባላት በሆኑ አገሮች ውስጥ ካለው ሕዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው ሲጋራ አጫሽ ነው ሲል ኤል ፓይስ የተሰኘው የስፔይን ጋዜጣ ዘግቧል። ከአውሮፓ አገሮች መካከል በአጫሾች ቁጥር የመጀመሪያውን ሥፍራ የያዘችው ግሪክ ስትሆን ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ያጨሳሉ። ግሪክ በትንባሆ ምርትም ከአውሮፓ ግንባር ቀደም ስትሆን በየዓመቱ 40,000 ቶን ትንባሆ ታመርታለች። ከአውሮፓ አገሮች መካከል አልፎ አልፎ የሚያጨሱ ሰዎችን ጨምሮ አነስተኛ የአጫሾች ቁጥር የሚገኝባት አገር ፖርቱጋል ስትሆን በዚህች አገር ያሉት አጫሾች ቁጥር ከ29 በመቶ ብዙም አይበልጥም። ይሁንና ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መካከል ትንባሆ በርካሽ ዋጋ የሚሸጥባት አገር ፖርቱጋል ናት። የአጫሾቹ ቁጥር አነስተኛ ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ከ1982 አንስቶ የትንባሆ ማስታወቂያዎች መጠቀምም ሆነ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ማጨስ በሕግ በመታገዱ እንደሆነ ይገመታል።

በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘ መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ አሁንም ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። በዓለማችን ላይ 6,500 ቋንቋዎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል በ2,355 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በ665 የአፍሪካ፣ በ585 የእስያ፣ በ414 የፓስፊክ ውቅያኖስ አገሮችና ደሴቶች፣ በ404 የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን ደሴቶች፣ በ209 የአውሮፓና በ75 የሰሜን አሜሪካ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ኅብረት 600 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች በመካሄድ ላይ ላሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረገ ነው።