በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ያለፈ ጉብኝት

የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ያለፈ ጉብኝት

የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ያለፈ ጉብኝት

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

መጋቢት 15, 2003 በሜክሲኮ ከተማ ዳርቻ በዚህ ገጽ ላይ ፎቶግራፋቸው የሚታየው አዳዲስ ሕንፃዎች ሲወሰኑ ከ40 አገሮች የመጡ ልዑካን ተገኝተው ነበር። እነዚህ የመኖሪያና የማተሚያ ሕንፃዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሜክሲኮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በቅርቡ የሠሯቸው ተጨማሪ ሕንፃዎች ናቸው።

በዚህ ሥፍራ የተሠሩት የቅርንጫፍ ቢሮው የመጀመሪያ ሕንፃዎች የተወሰኑት በ1974 ሲሆን በዚያን ጊዜ በሜክሲኮ 65,000 አስፋፊዎች ነበሩ። በሜክሲኮ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ያድግ ስለነበር በ1985 እና በ1989 ተጨማሪ ሕንፃዎች ተወስነዋል። በቅርቡ የተገነቡት ከደርዘን የሚበልጡ አዳዲስ ሕንፃዎች ትልቅ ማተሚያና 1,300 ለሚሆኑ ሠራተኞች የሚበቃ መኖሪያ ያላቸው ናቸው።

አዳዲሶቹ ሕንፃዎች ከተወሰኑ ከሁለት ሳምንት በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች የጉብኝት ፕሮግራም ተዘጋጀ። ቅርንጫፍ ቢሮውን እንዲጎበኙ የጽሑፍ መጋበዣ ከተላከላቸው መካከል የአካባቢው ባለ ሥልጣናት እንዲሁም ከቅርንጫፍ ቢሮው ማዶ በሚገኘው አዲስ የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ይገኙበት ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮው ያሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጥሪውን ምን ያህል ሰዎች ይቀበሉ ይሆን ብለው በማሰብ የሚሆነውን ለማየት በጉጉት ሲጠባበቁ ነበር።

የሚያስደስት ምላሽ

ተማሪዎችን እንዲሁም የመንግሥትና የማዘጋጃ ቤት ሹማምንትን ጨምሮ በድምሩ 272 ሰዎች ለጥሪው ምላሽ ሰጥተዋል። ጎብኚዎቹ የሕንፃዎቹን ውበትና ንጽሕና በማድነቅ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ጥሪውን ተቀብለው ከመጡት ሰዎች አንዷ “ድርጅታችሁን ስጎበኝ የመጀመሪያዬ ነው። በጣም ማራኪ ነው። በፊትም አደንቃችሁና አከብራችሁ የነበረ ቢሆንም ይህ ጉብኝት ይበልጥ እንዳደንቃችሁና እንዳከብራችሁ ገፋፍቶኛል” በማለት በጎብኚዎች መዝገብ ላይ አስተያየቷን አስፍራለች።

አንድ ሌላ ጎብኚ ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “እዚህ ቦታ ስለሚሠራው ነገር የተሳሳተ ግምት ነበረን። ስለ እናንተ ብዙ የሐሰት ወሬ ተናፍሷል። . . . አሁን ያየሁት ነገር ግን በእናንተ ላይ እምነት እንዲያድርብኝ አድርጎኛል። ጠቃሚ ነገር እያከናወናችሁ እንዳላችሁ ስለተገነዘብኩ ከእንግዲህ ቤቴ ስትመጡ በደስታ እቀበላችኋለሁ።”

እናቷ የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት የዩኒቨርሲቲው አስተማሪ የሁለት ክፍል ተማሪዎችን ይዛ መጥታ ነበር። እንዲህ አለች:- “ወጣቶቹን ይዣቸው የመጣሁት የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም ምን በመሥራት ላይ እንዳሉ እንዲያውቁ ስለፈለግሁ ነው። ደግሞም ይህን ቦታ በመጎብኘት ሊማሩት የሚችሉት ብዙ ነገር አለ።” ተማሪዎቹ ምን ተሰማቸው?

ከተማሪዎቹ መካከል አንዷ “ላደረጋችሁልን አቀባበል አመሰግናችኋለሁ። የዛሬው ቀን ለእኔና ለክፍል ጓደኞቼ የማይረሳ ቀን ነው” ስትል ጽፋለች። ሌላዋ ደግሞ ምሥክሮቹን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ፈጽሞ እንደማያውቁ ተናግራለች። “አእምሯችንን ማስፋትና ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ነገሮችም ለመስማትና ለማሰብ ፈቃደኞች መሆን አለብን” በማለት አስተያየቷን ደምድማለች። በአካባቢው የሚኖር አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ከዚህ ጉብኝት በፊት ስለ ምሥክሮቹ የነበረኝ አመለካከት የተለየ ነበር። አሁን ግን ምን ያህል እርስ በርስ እንደምትረዳዱ መመልከት ችያለሁ። እንደ ጉንዳን ታታሪዎች ናችሁ።”

አራት ፖሊሶችም ለጉብኝት መጥተው ነበር። ከእነሱ አንዷ የሚከተለውን ተናግራለች:- “በጣም አስደናቂ ነው። እዚህ ምንም ዓይነት አድልዎ የለም። የሚያጸዳውም፣ አትክልተኛውም፣ ሁሉም ሰው እኩል ነው። . . . ይህ ግሩም ነገር ነው።”

በአካባቢው የሚኖሩ ዘጠኝና አሥር ዓመት የሞላቸው ሁለት ልጆች ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “በጣም ያምራል፤ ትልቅ ሕንፃ ነው።” “ከሁሉም የወደድኩት ማሽኖቹን ነው። በጣም ፈጣኖች ናቸው። በተለይ ደግሞ ወረቀት የሚቆርጡትን ማሽኖች ወድጃቸዋለሁ።”

የከባድ ጉዳትና የቁስለኞች ሐኪም የሆነ አንድ ሰውና ባለቤቱ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነች ሴት ልጃቸው ለመጎብኘት መጥተው ነበር። በጉብኝቱ ወቅት የሐኪሙ ባለቤት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ጠየቀች። የማወቅ ፍላጎቷ የተቀሰቀሰው ምሥክሮቹ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አባል የነበሩትን አባቷን ሊያነጋግሩ በመጡበት ጊዜ እንደነበረ ተናገረች። አባቷ ሲቆጡ ምሥክሮቹ ግን ምንም ሳይረበሹ ተረጋግተው ይናገሩ ነበር። “አሁን ምክንያቱ ገብቶኛል” አለች።

ሐኪሙና ቤተሰቡ ይህ ጉብኝት ስለ ምሥክሮቹ የነበራቸውን አመለካከት እንደለወጠው ተናገሩ። ሆሴ የሚባለው አስጎብኚያቸውም ፍላጎታቸውን በማየት በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ የጋበዛቸው ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ሐሳብ አቀረበላቸው። ለዚህም ቀና ምላሽ በመስጠት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እየመጡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ።

እነዚህ ሰዎች በቀጣዩ ሳምንት የመጡ ሲሆን ሆሴና ባለቤቱ ቤትሪስ ወደ ክፍላቸው ወስደው በሚገባ አስተናገዷቸው። ብዙ ጥያቄዎች ስለነበሯቸው የመጀመሪያው ጥናት ሦስት ሰዓት ተኩል የፈጀ ነበር! ከዚህ በፊት ምሥክሮቹ ሲያነጋግሯቸው ይቆጡ የነበሩትን የሚስትየዋን አባት ጨምሮ ሁሉም ሚያዝያ 16 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ተገኙ!

ከሁሉ በላይ አስደሳች የነበረው ነገር ጎብኚዎቹ 500 የሚያህሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን፣ በተለይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሶችን ወደ ቤታቸው ይዘው መሄዳቸው ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ኖሯቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል።

በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ የምትኖር አንዲት ሴት በጽሑፍ ማደያ ዴስኩ ላይ ለተመደበው አርማንዶ ለተባለው ወንድም “[ሃይማኖታችሁ] እውነት እንደሆነ ስላወቅሁ ከዛሬ ጀምሮ ከእናንተ ጋር አብሬ እሰበሰባለሁ” ብላ ነግራው ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አርማንዶ ይህችን ሴት በመንግሥት አዳራሹ ሲያያት በጣም ተደሰተ። “በጉብኝቱ ወቅት የወሰደችውን መጽሐፍ ይዛ ነበር። ሰላም ስላት ‘እንደምታየኝ አደርጋለሁ ብዬ ቃል የገባሁትን ነገር እያደረግሁ ነው’ አለችኝ” ሲል ተናግሯል።

ሦስቱ የጉብኝት ቀናት ወዲያውኑ አለፉ። ይሁን እንጂ በጣም የሚያንጹ ነበሩ። ጎብኚዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በቦታው ተገኝተው ቅርንጫፍ ቢሮውን ካዩ በኋላ የሰጡት አስተያየት በዚያ የሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች ያገኙትን መብት ከፍ አድርገው እንዲመለከቱና ይበልጥ እንዲያደንቁ ረድቷቸዋል።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

1. ጋራዥ፣ 2. የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ፣ 3. የጥገና ሕንፃ፣ 4. የመኖሪያ ሕንፃ፣ 5. ማተሚያ፣ 6. አዳራሽ፣ 7. የእንግዳ ማረፊያ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ተማሪዎችንና የአካባቢውን ፓሊሶች ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጥተው እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለዋል