በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“ሸበቶ” ወንጀለኞች

የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ታይምስ “ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን ወንጀል የሚፈጽሙ ጡረተኛ አረጋውያን ለማስተናገድ ሲባል በብሪታንያ ወህኒ ቤት ውስጥ ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀ አንድ ሕንፃ አለ” ሲል ዘግቧል። በፖርትስማውዝ ወህኒ ቤት የሚገኘው የአረጋውያን እስረኞች ክፍል ወንበር የተገጠመለት አሳንሱር፣ ለአረጋውያን ተብለው የተዘጋጁ የጂምናዝየም መሣሪያዎችና በነርስነት ሙያ የሠለጠኑ ሠራተኞች አሉት። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ100,000 የሚበልጡ ጡረተኞች ከመንግሥት የሚያገኙት ድጎማና የጡረታ አበል ስለማይበቃቸው “ወንጀል መፈጸም ጀምረዋል።” አንዳንዶቹ አደንዛዥ ዕፆችን ያዘዋውራሉ፣ ከሱቅ ዕቃ ይሰርቃሉ፣ ሲጋራና አልኮል በኮንትሮባንድ ይነግዳሉ አልፎ ተርፎም ባንክ ይዘርፋሉ። በ1990 ወህኒ የወረዱት ጡረተኞች ቁጥር 355 ሲሆን በ2000 ግን ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር 1,138 ደርሷል። ስለ ወንጀልና ወንጀለኞች ጥናት የሚያካሂዱት ቢል ቱፕማን ብዙዎቹ ቀደም ሲል ምንም ዓይነት የወንጀል ሪኮርድ የነበራቸው ባይሆኑም “የኑሮው ጫና” ወንጀል ለመፈጸም እንደገፋፋቸው ተናግረዋል። “እነዚህ ጡረተኞች ያጡ የነጡ ድሆች ሳይሆኑ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ትጉ ሠራተኞችና ሕግ አክባሪ የነበሩ ሰዎች ናቸው።”

ሳሙና ሕይወት ይታደጋል

ለንደን በሚገኘው ስኩል ኦቭ ሃይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜዲስን ሌክቸረር የሆኑት ቫል ከርቲስ እንዳሉት ከሆነ እጅን በሳሙና መታጠብ ሰዎች በተቅማጥ በሽታ እንዳይያዙ ስለሚረዳ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይታደጋል። በኪዮቶ፣ ጃፓን በተካሄደው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የውኃ ፎረም ላይ ከርቲስ በሰው ዓይነ ምድር ውስጥ የሚገኙ በሽታ አምጪ ተሕዋሲያንን፣ “ቁጥር አንድ የሕዝብ ጠላት” ሲሉ መግለጻቸውን ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ ዘግቧል። “በአንዳንድ ማኅበረሰቦች” ይላል ጋዜጣው፣ “ሴቶች ሽንት ቤት ሄደው ሲመለሱ እጃቸውን ሳይታጠቡ ሕፃናት ልጆቻቸውን ያጥባሉ እንዲሁም ምግብ ይሠራሉ።” እጅን በሳሙና መታጠብ ገዳይ የሆኑ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች እንዳይዛመቱ ለመከላከል ይረዳል። ከርቲስ እንዳሉት ከሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የውኃውን ንጽሕና ከፍ በማድረግ የተቅማጥ በሽታን ለመከላከል ከመጣር ይልቅ እጅን በሳሙና መታጠብ በሦስት እጥፍ ገንዘብ ይቆጥባል።

ችግር ላይ የወደቁ ገበሬዎች

“በብዙ የዓለም ክፍሎች የግብርና ምርቶች በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩ ያደረገው አረንጓዴ አብዮት ያለ አንዳች ኪሣራ የተገኘ አይደለም። በአፍሪካ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎስቋላ ገበሬዎች ይበልጥ እንዲደኸዩ አድርጓል” በማለት ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት አንድ ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል። እንዴት? የዓለም ሕዝብ በመጨመሩ ምክንያት ይከሰታል ተብሎ የተሰጋውን ረሃብ ለመከላከል ሲባል ከ1950ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ጀምሮ ከፍተኛ ምርት የሚያስገኙ የስንዴና የሩዝ ዝርያዎች እንዲሰራጩ ተደርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ ከፍተኛ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ምርት እንዲትረፈረፍ በማድረጋቸው የእህል ዋጋ በእጅጉ ረከሰ። “እነዚህን አዳዲስ የእህል ዝርያዎች መዝራት የቻሉ ገበሬዎች ምርታቸውን በመጨመር የዋጋውን ማሽቆልቆል ማካካስ ሲችሉ እንደዚህ ማድረግ ያልቻሉት ገበሬዎች ግን ለኪሣራ ተዳርገዋል” ይላል ኒው ሳይንቲስት። በተጨማሪም አዳዲሶቹ የእህል ዝርያዎች የተሞከሩት በእስያና በላቲን አሜሪካ በመሆኑ አፍሪካ ውስጥ ጥሩ ምርት ማስገኘት አልቻሉም።

አደጋ! እንቅልፍ ለሚያሸልባቸው አሽከርካሪዎች

ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት “ድካም የተጫጫናቸው ወይም እንቅልፍ እንቅልፍ የሚላቸው አሽከርካሪዎች ጉዳይ በማኅበረሰባችን ውስጥ አሳሳቢ ችግር ሆኗል” ይላል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት “ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የመኪና አደጋ የሚደርሰው አሽከርካሪዎቹ በማሸለባቸው ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።” ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ ላይ የወጣው የጥናት ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ላለው አደጋ የሚዳረጉት በምሽት ወይም ‘እንቅልፍ በሚጫጫንበት’ የቀትር ሰዓት አካባቢ ብቻቸውን ሆነው በከፍተኛ ፍጥነት የሚያሽከረክሩ ሰዎች ናቸው። እንደሌሎቹ የመኪና አደጋዎች ሁሉ አሽከርካሪው በማሸለቡ ምክንያት የሚከሰቱ የመኪና አደጋዎችም በአብዛኛው የሚደርሱት ከ30 ዓመት በታች በሆኑ ወንዶች ላይ ነው።” መሪያቸውን እንደጨበጡ የማንቀላፋት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ የሆኑት ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ ዲስኦርደር የሚባል የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ሰዎች ናቸው። ይህ ዓይነቱ ችግር “በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወንዶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑትን” እንደሚያጠቃ መጽሔቱ ገልጿል። ይህ የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ሰዎች በሚያሽከረክሩበት ጊዜ ማሸለባቸው አይታወቃቸውም።

በመቅለጥ ላይ የሚገኙ የበረዶ ክምሮች

በሕንድ አገር በፑንጃብ ክፍለ ግዛት የሚገኙ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ኃይለኛው የዝናብ ወቅት በመዘግየቱ ምክንያት እየጎደሉ በሚገኙበት በአሁኑ ጊዜ በሰትለጅ ወንዝ ላይ የተሠራው የባክራ ግድብ ውኃ አምና ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የሰትለጅ ወንዝ ዋነኛ ገባር የሆነው ወንዝ የሚያልፈው 89 የበረዶ ክምሮች በሚገኙበት አካባቢ እንደሆነ ዳወን ቱ ኧርዝ የተባለው መጽሔት ይገልጻል። “የዝናቡ መስተጓጎል የበረዶው ክምር እየሟሟ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል። ደመና ባለመኖሩ የበረዶ ክምሮቹ ለከፍተኛ የፀሐይ ትኩሳት ተጋልጠዋል። በዚህ ላይ የአካባቢው ሙቀት በጣም ከፍተኛ መሆኑ ሲጨመር የበረዶ ክምሮቹ በፍጥነት እንዲቀልጡ አድርጓቸዋል” ሲሉ በጃዋሃርላል ኔህሩ ዩኒቨርሲቲ የበረዶ ክምር ተመራማሪ የሆኑት ሳይድ ኢክባል ሃስናን ገልጸዋል። ሊቃውንቱ የበረዶ ክምሮቹ መቅለጥ ሐይቆች ድንበራቸውን ጥሰው አካባቢውን እንዲያጥለቀልቁ ሊያደርግ ይችላል ብለው ያስባሉ። ከዚህም በላይ የበረዶ ክምሮች ሲመናመኑ የወደፊቱ የውኃ አቅርቦት ይቀንሳል። ይህ ደግሞ በግብርና ሥራና በኃይል አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

አምሮ ለመታየት መፈለግ

የአውስትራሊያ ግዛት በሆነችው በኒው ሳውዝ ዌልስ “በየዓመቱ 2,850 ሰዎች በቆዳ ካንሰር ሲያዙ 340 ሰዎች ደግሞ በዚሁ በሽታ ምክንያት ይሞታሉ” ሲል ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ዘግቧል። በቪክቶሪያ ካንሰር ካውንስል የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከአውስትራሊያ ሕዝብ መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት መልካቸውን ለማሳመር ሲሉ ፀሐይ ላይ ይሰጣሉ፤ ይህም ቁጥሩ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 በመቶ ጨምሯል ማለት ነው። ጋዜጣው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “የተመራማሪዎቹ የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ከ60 በመቶ የሚበልጡ ወጣቶች ሆን ብለው ቆዳቸውን ለማጠየም ሲሉ ፀሐይ ላይ የሚሰጡ ከመሆኑም በላይ ከጠቅላላው ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ ፀሐይ ላይ ሲሰጡ ይበልጥ ጤነኛ እንደሆኑ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።” በገበያ አዳራሾች የሚሸጡ ቆዳን ለማጠየም የሚረዱ ቅባቶች ሽያጭ ባለፈው ዓመት ብቻ 18 በመቶ ሲጨመር የፀሐይ መከላከያ ቅባቶች ሽያጭ ግን አልጨመረም። የአውስትራሊያ የደርማቶሎጂ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሮቢን ማርክስ አንዳንድ ሰዎች ቀስ በቀስ ቆዳን ፀሐይ በማስመታት እንዲጠይም ማድረግ አደገኛ እንደማይመስላቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ “የቆዳ ካንሰር ሊቃውንት በማንኛውም መጠን ቆዳን ፀሐይ በማስመታት ማጠየም አደገኛ እንደሆነ ይናገራሉ” በማለት ጋዜጣው ይገልጻል። ዶክተር ማርክስ “የቆዳ መጠየም እንደ መጅ ነው፤ አንድ ችግር መኖሩን ያመለክታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በኢጣሊያ እንቅልፍ የማጣት ችግር

በ2002 በኢጣሊያ፣ እንቅልፍ የማጣት ችግርን አስመልክቶ ከ600 በላይ ዶክተሮችና ከ11,000 የሚበልጡ ሕመምተኞች የተካፈሉበት ሰፊ ጥናት ተካሂዶ ነበር። ጥናቱ ከ12 ሚሊዮን የሚበልጡ ጣሊያናውያን የእንቅልፍ ችግር እንዳለባቸው ማመልከቱን ላ ስታምፓ የተባለው ጋዜጣ ገልጿል። ጥናቱ ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት ጠዋት ጠዋት፣ 80 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቀኑ ውስጥ በአንድ የተወሰነ ሰዓት እንደሚጫጫናቸውና 46 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሥራቸው ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስቸግራቸው ተደርሶበታል። ጋዜጣው “22 በመቶ የሚሆኑት የመኪና አደጋዎች የሚያጋጥሙት አሽከርካሪው እንቅልፍ ሲጫጫነው በመሆኑ በዚህ ረገድ ለበለጠ ጉዳት የሚዳረጉት መኪና የሚያሽከረክሩት ናቸው” ይላል። በተጨማሪም ችግሩ ካለባቸው ሰዎች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት ስለችግራቸው ሐኪም አማክረው እንደማያውቁ ጥናቱ አመልክቷል። የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት ማርዮ ጆቫኒ ተርሳኖ “እንቅልፍ የማጣት ችግር ካለባቸው ሰዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት የችግራቸው መንስኤ በውል አይታወቅም” ብለዋል። ቢሆንም የሕክምና ምርመራ ቢደረግ ለችግራቸው ምክንያት የሚሆን አካላዊ ሕመም ሊገኝባቸው ይችል ይሆናል። ተርሳኖ እንደተናገሩት ለእንቅልፍ ማጣት ችግር መንስኤ ከሚሆኑት ሌሎች ነገሮች መካከል ስጋት (24 በመቶ)፣ አስጨናቂ ሁኔታዎች (23 በመቶ) እንዲሁም የአእምሮ መረበሽ (6 በመቶ) ይገኙበታል።

አእምሮ፣ ስሜትና ጤንነት

በአእምሮአችን ውስጥ የሚብላላው ነገር ከዚህ በፊት ይታመን ከነበረው ይበልጥ በአካላችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ቭፕሮስት በተባለው የፖላንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ ያመለክታል። በማከልም “የምናስበው ነገርና ስሜታችን ሁሉንም የአካል ብልቶች ማለትም የነርቭ፣ በሽታ ተከላካይ፣ ሆርሞን አመንጪ፣ የደም ዝውውርና የመራቢያ ሕዋሶችን በሙሉ ይነካል” ብሏል። ስለሆነም፣ በዋርሶ የሃይጂንና ኤፒዶሞሎጂ ሚሊተሪ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ማረክ ኮቫልቺክ “ውጥረት የበዛበት ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች በጉንፋንና በፍሉ የመያዝ ዕድላቸው ከሌሎች ሰዎች በእጥፍ ይበልጣል” ብለዋል። በተጨማሪም ጭንቀት ያለባቸው ሴቶች የማርገዝ አጋጣሚያቸው በግማሽ ይቀንሳል። ቭፕሮስት ጨምሮም ጭንቀት ካንሰር ባያመጣም “የካንሰርን ሂደት ሊያፋጥን ይችላል” ብሏል። ግልፍተኛና ጠበኛ የሆኑ ሰዎች በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ስለሚታመን ቁጣም ለጤንነት ጎጂ ሊሆን ይችላል።

ሕጋዊ የዝሆን ጥርስ ሽያጭ

ከ1979 እስከ 1989 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥር በግማሽ ቀንሷል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ከዝሆን ጥርስ የሚሠሩ ዕቃዎች ተፈላጊነት እየጨመረ መሄዱ ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ሕገ ወጥ አዳኞች አውቶማቲክ መሣሪያዎች በብዛት ማግኘታቸው ነው። በዚህ ምክንያት በ1989 ኮንቬንሽን ኦን ኢንተርናሽናል ትሬድ ኢን ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ የተባለው ስምምነት በዝሆን ጥርስ ንግድ ላይ ሙሉ እገዳ ጣለ። ይሁን እንጂ በቅርቡ ኮንቬንሽን ኦን ኢንተርናሽናል ትሬድ ኢን ኢንዴንጀርድ ስፒሽስ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና እና ናሚብያ ለአንድ ጊዜ ብቻ 600 ኩንታል የሚመዝን የዝሆን ጥርስ እንዲሸጡ መፍቀዱን አፍሪካን ዋይልድላይፍ የተባለው መጽሔት ዘግቧል። የዝሆን ጥርሶቹ ከሕገ ወጥ አዳኞቹ የተወረሱ ወይም በተፈጥሯዊ ምክንያት ከሞቱ ዝሆኖች የተወሰዱ ናቸው። ሌሎች ሁለት አገሮች “ሕገ ወጥ የዝሆን ጥርስ ግብይት እንዳይካሄድ ማገድ የሚችሉ ስለመሆናቸው በቂ መተማመኛ ባለመስጠታቸው” የዝሆን ጥርስ ክምችታቸውን እንዲሸጡ ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል።