በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ስም አለው!

አምላክ ስም አለው!

 አምላክ ስም አለው!

የአምላክ ስም ማን ነው? ሰዎች ሁሉ የግል መጠሪያ ስም አላቸው። እንዲያውም ብዙ ሰዎች ለውሾቻቸውና ለድመቶቻቸው እንኳ ሳይቀር ስም ያወጣሉ! ታዲያ አምላክ የራሱ የሆነ ስም ሊኖረው አይገባም? የግል መጠሪያ ስም መኖርና በስም መጠራት ለሰዎች የእርስ በርስ ዝምድናና ግንኙነት የግድ አስፈላጊ ነው። ታዲያ ከአምላክ ጋር ለሚኖረን ዝምድና ሁኔታው ከዚህ የተለየ መሆን አለበት? የሚያስገርመው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው እውነተኛ አምላክ እናምናለን የሚሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተጸውኦ ስሙ አይጠሩትም። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ከታወቀ ብዙ ምዕተ ዓመታት አልፈዋል። የሚከተሉትን ተከታታይ ርዕሶች በምታነብበት ጊዜ በአንድ ወቅት የአምላክ ስም በሰፊው ይሠራበት እንደነበረ ትረዳለህ። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በስም ስለማወቅ ምን እንደሚል ትማራለህ።

በ17ኛው መቶ ዘመን በርካታ የአውሮፓ አገሮች በሳንቲሞቻቸው ላይ የአምላክን ስም ይቀርጹ ነበር። በ1634 በተቀረጸ የጀርመን ሳንቲም ላይ ይሖዋ የሚለው ስም በጉልህ ይታያል። እነዚህ ሳንቲሞች የይሖዋ ገንዘቦች ወይም የይሖዋ ሳንቲሞች ተብለው ይጠሩ የነበረ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ለግብይት አገልግለዋል።

ይሖዋ * ለበርካታ መቶ ዘመናት ተቀባይነት አግኝቶ የቆየ የአምላክ ስም አጠራር ነው። ከቀኝ ወደ ግራ በሚነበበው የዕብራይስጥ ቋንቋ ይህ ስም በአራት ተነባቢ ፊደላት (יהוה) ተጽፎ ይገኛል። እነዚህ የሐወሐ የሚል ድምጽ ያላቸው አራት የዕብራይስጥ ሆሄያት ቴትራግራማተን ተብለው ይጠራሉ። በዚህ ዓይነት የሚጻፈው የአምላክ ስም ለአሥርተ ዓመታት በአውሮፓውያን ሳንቲሞች ላይ ተቀርጾ ቆይቷል።

በተጨማሪም የአምላክን ስም በሕንፃዎች፣ በሐውልቶች፣ በሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ እንዲሁም በብዙ የአብያተ ክርስቲያናት ዝማሬዎች ውስጥ ማግኘት ይቻላል። ብሮክሃውስ የተባለው በጀርመንኛ የተዘጋጀ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚለው ከሆነ በአንድ ዘመን የፕሮቴስታንት መሳፍንቶች ቴትራግራማተንና የተሸለመ ፀሐይ የተቀረጸበት ኒሻን ማድረጋቸው የተለመደ ሆኖ ነበር። ይህ በባንዲራዎችና በሳንቲሞች ላይ ጭምር ይደረግ የነበረው ንድፍ ይሖዋ-ፀሐይ ኒሻን ተብሎ ይጠራ ነበር። በጣም ሃይማኖተኛ የነበሩት የ17ኛውና የ18ኛው መቶ ዘመን አውሮፓውያን ሁሉን የሚችለው አምላክ ስም እንዳለው ያውቁ እንደነበረ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ስሙን ይጠሩ ነበር።

በቅኝ ተገዥዋ በአሜሪካም ቢሆን የአምላክ ስም ምሥጢር አልነበረም። ለምሳሌ ኤተን አለን የሚባለውን የአሜሪካ አብዮታዊ ወታደር እንውሰድ። በማስታወሻው ላይ እንዳሰፈረው በ1775 ጠላቶቹ እጃቸውን እንዲሰጡ “በታላቁ ይሖዋ ስም” ጠይቋል። ቆየት ብሎም አብርሃም ሊንከን ፕሬዚዳንት በነበሩበት ዘመን አብዛኞቹ አማካሪዎቻቸው በጻፉላቸው ደብዳቤዎች ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም ብዙ ጊዜ ጠቅሰዋል። የአምላክ ስም የሚገኝባቸው ሌሎች የአሜሪካ ታሪካዊ ሰነዶች በብዙ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ለሕዝብ ይታያሉ። እነዚህ የአምላክ ስም ለበርካታ መቶ ዘመናት እንዴት ይሠራበት እንደነበረ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው።

ዛሬስ? የአምላክ ስም ተረስቷል? በፍጹም! የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን የግል ስም በብዙ  ቁጥሮች ላይ አስፍረዋል። ቤተ መጻሕፍት ሄደህ ጥቂት መጻሕፍት ብትመለከት ወይም የራስህን መዝገበ ቃላት ገለጥ ገለጥ ብታደርግ ይሖዋ ወይም በእንግሊዝኛ ጀሆቫ የሚለው ስም የቴትራግራማተን አቻ መሆኑን መረዳት ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢንተርናሽናል ይሖዋ የሚለው ስም “በዕብራይስጥ ቅዱስ የሆነው የአምላክ ስም” እንደሆነ በቀጥታ ይገልጻል። የኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ የቅርብ እትም ይሖዋ “ለአምላክ የተሰጠ አይሁዳዊና ክርስቲያናዊ ስም” እንደሆነ ያመለክታል።

‘ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ዛሬ የምንኖረውን ሰዎች ሊያሳስብ የሚገባ ነገር ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የአምላክ ስም ዛሬም ቢሆን በተለያየ መልኩ በብዙ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችና አደባባዮች ይታያል። ለምሳሌ በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኝ አንድ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ተቀርጾ ይገኛል። በዚሁ ከተማ በአንድ የምድር ውስጥ ባቡር ጣቢያም ስሙ በዕብራይስጥ ተጽፎ ይታያል። ይሁን እንጂ በእነዚህ ቦታዎች ከሚተላለፉት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል እነዚህን ቅርጾች ሥራዬ ብለው የተመለከቱት ብዙዎች አይደሉም ለማለት ይቻላል።

በአካባቢህ የሚኖሩ ሰዎችስ ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ? ወይስ አብዛኞቹ ሰዎች ፈጣሪን የሚጠሩት በማዕረግ ስሙ “አምላክ” እያሉ ብቻ ነው? ብዙ ሰዎች አምላክ ስም ኖረው አልኖረው ምንም ደንታ እንደማይሰጣቸው አስተውለህ ይሆናል። አንተስ? አምላክን ይሖዋ በተባለው የግል ስሙ መጥራት ይከብድሃል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ከ95 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚሠራባቸውን ይሖዋ የሚለውን ስም 39 በሚያህሉ የአጠራር ዓይነቶች አስፍረዋል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የይሖዋን ስም ያሳወቀ ንጉሥ

በ1852 አንድ የሚስዮናውያን ቡድን ከሐዋይ ተነስቶ ወደ ማይክሮኔዥያ ደሴቶች ተጓዘ። እነዚህ ሚስዮናውያን በዘመኑ የሐዋይ ደሴት ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ከሜሃሜሃ ሳልሳዊ ማህተም ያረፈበት ሸኚ ደብዳቤ ይዘው ነበር። ይህ በሐዋይ ቋንቋ የተጻፈ ደብዳቤ ለፓስፊክ ደሴቶች የተለያዩ ገዥዎች የተላከ ሲሆን በከፊል እንዲህ ይላል:- “ጥቂት የልዑል አምላክ የይሖዋ አስተማሪዎች የዘላለም መዳን እንድታገኙ ቃሉን ሊያሳውቋችሁ ወደ እናንተ ለመምጣት ተነስተዋል። . . . እነዚህን ጥሩ አስተማሪዎች በወዳጅነትና በክብር እንድትቀበሉ እንዲሁም እንድታዳምጧቸው አደራ እላችኋለሁ። . . . ጣዖቶቻችሁን ጥላችሁ ጌታ ይሖዋን አምላካችሁ አድርጋችሁ እንድትቀበሉት፣ እንድታመልኩትና እንድትወዱት እመክራችኋለሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ይባርካችኋል፣ ያድናችኋል።”

[ሥዕል]

ንጉሥ ከሜሃሜሃ ሳልሳዊ

[ምንጭ]

Hawaii State Archives

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴትራግራማተን “አራት ፊደላት” ማለት ሲሆን የአምላክ ስም የዕብራይስጥ አጻጻፍ ነው