በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጀርሞች በማንም ላይ ጉዳት የማያደርሱበት ጊዜ

ጀርሞች በማንም ላይ ጉዳት የማያደርሱበት ጊዜ

ጀርሞች በማንም ላይ ጉዳት የማያደርሱበት ጊዜ

ጀርሞች ወይም ረቂቅ ሕዋሳት ለሕይወት አስፈላጊ ናቸው። በምድር አፈር ውስጥም ሆነ በገዛ አካላችን ውስጥ የማይናቅ ድርሻ አላቸው። በገጽ 7 ላይ የሚገኘው “የጀርም ዓይነቶች” የሚለው ሣጥን እንዳመለከተው “በሰውነታችን ውስጥ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ።” ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ጠቃሚዎች፣ እንዲያውም ለጤንነታችን እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። በሽታ አምጪ የሆኑት ባክቴሪያዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂቶች ቢሆኑም አንድም ጀርም በማንም ላይ ጉዳት የማያደርስበት ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ጀርሞች የሚያስከትሉት ጎጂ ውጤት የሚወገድበትን መንገድ ከመመርመራችን በፊት በሽታ አምጪ የሆኑ ጀርሞችን ለመዋጋት ምን ጥረት እየተደረገ እንዳለ እንመልከት። ከዚህ ርዕስ ጋር አባሪ የሆነውን “ምን ልታደርግ ትችላለህ?” የሚለውን ሣጥን መርምር፤ እንዲሁም የጤና ባለሞያዎች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩ ጀርሞችን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት ተመልከት።

ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ

የቀድሞዋ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ግሮ ሀርለም ብሩንትላንድ በመደረግ ላይ ያለውን ጥረት ገልጸዋል። ሪፖርት ኦን ኢንፌክሽየስ ዲዝዝስ 2000 በሚል ባቀረቡት ዘገባ ላይ “የተሕዋሳት መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚያስፈልግ” ጠቁመዋል። በተጨማሪም “ሁሉንም የጤና ባለሞያዎች የሚያሳትፍ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል” ካሉ በኋላ “በኢንፌክሽን በሽታዎች ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ማካሄድ” አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በ2001 የዓለም ጤና ድርጅት “የተሕዋሳት መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ” ነድፏል። ይህ ሰነድ የጤና አጠባበቅ ባለሞያዎችም ሆኑ ሰዎች በአጠቃላይ “ምን ማድረግና እንዴት ማድረግ እንደሚገባቸው” የሚገልጽ ፕላን ይዟል። ይህ ስትራቴጂ ሰዎች ጤንነታቸውን እንዴት ሊጠብቁ እንደሚችሉ ማስተማርንና በኢንፌክሽን በሽታዎች በሚታመሙበት ጊዜ ደግሞ እንዴት አንቲባዮቲክና ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶችን እንደሚጠቀሙ የሚያስረዳ መመሪያ አካትቶ የያዘ ነው።

በተጨማሪም የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች ማለትም በሆስፒታሎችና በማስታመሚያ ቤቶች የሚሠሩ ዶክተሮች፣ ነርሶችና ሌሎች ሠራተኞች በሽታ እንዳይዛመት ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተመክረዋል። የሚያሳዝነው ግን በርካታ የጤና ባለሞያዎች አሁንም ቢሆን ከአንዱ በሽተኛ ወደሌላው በሚዘዋወሩበት ጊዜ እጃቸውን ለመታጠብ ወይም ጓንታቸውን ለመቀየር ቸልተኞች እንደሆኑ ጥናቶች አመልክተዋል።

በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዶክተሮች ሳያስፈልግ ጭምር አንቲባዮቲኮችን ያዛሉ። ይህን ከሚያደርጉባቸው ምክንያቶች አንዱ በሽተኞች ቶሎ ለመዳን ሲሉ አንቲባዮቲክ እንዲታዘዝላቸው ሐኪሞቻቸውን ስለሚጫኑ ነው። ስለሆነም ዶክተሮች በሽተኞቻቸውን አስደስተው ለመሸኘት ሲሉ ብቻ እሺ ይሏቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ዶክተሮች በቂ ጊዜ ወስደው በሽተኞቻቸውን አያስተምሩም ወይም ለበሽታው መንስኤ የሆነው ጀርም ምን ዓይነት እንደሆነ ለመለየት የሚያስችል ምርመራ የሚያደርጉበት መንገድ የላቸውም። በተጨማሪም አዲስና ብዙ ጀርሞችን የማጥቃት ኃይል ያለው ውድ አንቲባዮቲክ መድኃኒት ያዝዙ ይሆናል። ይህም ጀርሞች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ እንዲያዳብሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ ካነጣጠረባቸው ሌሎች ክፍሎች መካከል ሆስፒታሎች፣ ብሔራዊ የጤና አጠባበቅ ዘዴዎች፣ ምግብ አምራቾች፣ የመድኃኒት ኩባንያዎችና ሕግ አውጪዎች ይገኙበታል። ሪፖርቱ መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች በመላው ዓለም ላይ የሚያካሂዱትን ጥቃት ለመቋቋም እነዚህ ሁሉ ክፍሎች ትብብር እንዲያደርጉ ተማጽኗል። ይሁን እንጂ ይህ ስትራቴጂ ግቡን ይመታ ይሆን?

የተጋረጡ እንቅፋቶች

የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ የጤና ችግሮችን መቋቋም እንዳይቻል የሚያደርግ አንድ ዋነኛ እንቅፋት እንዳለ አመልክቷል። እርሱም ትርፍ፣ ማለትም ገንዘብ የማግኘት ፍላጎት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9,10) የዓለም ጤና ድርጅት “የሽያጭ ወኪሎች ከሕክምና ባለሞያዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ላይ ቁጥጥር ማድረግንና የመድኃኒት ኢንዱስትሪዎች ለሕክምና ባለሞያዎች በሚያዘጋጁት የትምህርት ፕሮግራም ላይ ክትትል ማድረግን ጨምሮ የመድኃኒት ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ መከታተል ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው” ሲል አሳስቧል።

የመድኃኒት ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በከፍተኛ ትጋት ለዶክተሮች ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች አማካኝነት በቀጥታ ለሸማቹ ሕዝብ ማስተዋወቅ ጀምረዋል። ይህም ከአግባብ ውጭ ለሆነ የመድኃኒት አጠቃቀም አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች እንዲባዙ ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ ለምግብነት ለሚያገለግሉ እንስሳት ስለሚሰጡ ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች በሚገልጸው ምዕራፉ ላይ “በአንዳንድ አገሮች የእንስሳት ሐኪሞች 40 በመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን የሚያገኙት ከመድኃኒት ሽያጭ ነው። ስለዚህ ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች በብዛት አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ አይገፋፉም።” በበቂ መረጃዎች ሊረጋገጥ እንደቻለው መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች ሊፈጠሩና ሊባዙ የቻሉት አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች አላግባብ በመወሰዳቸው ነው።

የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ምርት ብዛት በእርግጥም በጣም የሚያስደንቅ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በዓመት 20 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ይመረታሉ። ከመላው ዓለም ምርት ውስጥ ለሰዎች ፍጆታ የሚውለው ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው። የቀረው በአዝርእት ላይ ይረጫል ወይም ለእንስሳት ይሰጣል። አብዛኛውን ጊዜ የእርድ ከብቶችን እድገት ለማፋጠን ሲባል ከመኗቸው ጋር አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ተደባልቀው ይሰጧቸዋል።

የመንግሥታት የሥራ ድርሻ

የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ በማጠቃለያው ላይ “ስትራቴጂውን ሥራ ላይ የማዋሉ ኃላፊነት በአብዛኛው የሚወድቀው በእያንዳንዱ አገር ላይ ነው። መንግሥታት ወሳኝ የሆነ የሥራ ድርሻ ይኖራቸዋል” ይላል።

በእርግጥም በርካታ መንግሥታት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ለሚደረግ ትብብር ልዩ ትኩረት በመስጠት መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸውን ተሕዋሳት መስፋፋት የሚቆጣጠሩበት ፕሮግራም ነድፈዋል። እነዚህ ፕሮግራሞች በፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች አጠቃቀምና መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ባላቸው ተሕዋሳት ላይ ቁጥጥር ማድረግን፣ ኢንፌክሽንን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከርን፣ ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶችን ለሕክምናና ለግብርና ተገቢ በሆነ መንገድ መጠቀምን፣ ተሕዋሳት መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ የሚያዳብሩበትን መንገድ ለመረዳት የሚያስችል ምርምር ማካሄድንና አዳዲስ መድኃኒቶች መሥራትን ያካትታል። የዓለም ጤና ድርጅት የኢንፌክሽን በሽታዎችን አስመልክቶ ያቀረበው የ2000 ሪፖርት ተስፋ ሰጪ አይደለም። ለምን?

ለዚህ አንዱ ምክንያት “ለሕዝብ ጤና ቅድሚያ የማይሰጡ መንግሥታት በዚህ ረገድ ቆራጥ እርምጃ የማይወስዱ መሆናቸው ነው” ሲል ሪፖርቱ ጠቁሟል። በተጨማሪም “በሽታና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ የሚስፋፋው ብጥብጥ፣ ድህነት፣ የሕዝብ ፍልሰትና የአካባቢ ጉስቁልና ባለበት እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለኢንፌክሽን በሽታዎች በሚጋለጡበት ሁኔታ ነው” ብሏል። ሰብዓዊ መንግሥታት ደግሞ እነዚህን ችግሮች ማስወገድ አልሆነላቸውም።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለተለያዩ በሽታዎች መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑትን ችግሮች ብቻ ሳይሆን በሽታዎችን ከነአካቴው ስለሚያጠፋ መንግሥት ይናገራል። አንዳንድ ጀርሞች ምንጊዜም ችግር ማምጣታቸው አይቀርም ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ የወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ በጣም የተሻለ እንደሚሆን የምናምንበት በቂ ምክንያት አለን።

ጀርሞች ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትሉበት ጊዜ

ኢሳይያስ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢይ ከብዙ ዘመን በፊት ከሰብዓዊ መንግሥታት ስለሚበልጥ አንድ መንግሥት ከመተንበዩም በተጨማሪ የዚህ መንግሥት አስተዳዳሪ ማን እንደሚሆን ተናግሯል። ይህ ትንቢት በኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት ምን እንደሚል ልብ በል:- ‘ሕፃን ተወልዶልናል፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል። መንግሥትም በትከሻው ላይ ይሆናል። ስሙም ድንቅ፣ መካሪ፣ ኃያል አምላክ፣ ዘላለማዊ አባት፣ የሰላም መስፍን ተብሎ ይጠራል።’—ኢሳይያስ 9:6

ይህ ሕፃን፣ ይህ የገዥነት ሥልጣን የሚሰጠው መስፍን ማነው? የዚህ ሕፃን ማንነት ገና ከመወለዱ በፊት እንዴት እንደታወቀ ልብ በል። መልአኩ ገብርኤል ማርያም ለምትባል ድንግል “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል . . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ሲል ነግሯታል።—ሉቃስ 1:31-33

ኢየሱስ ለአቅመ አዳም በደረሰ ጊዜ በእርግጥ የአምላክ ንጉሣዊ መንግሥት ገዥ እርሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አሳይቷል። ኢየሱስ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ “የመንግሥቱን ምሥራች” ከማወጁም በላይ ማንኛውንም በሽታና ሕማም የማስወገድ ኃይል እንዳለው በተግባር አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ይተርካል:- “ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፣ ዕውሮችንም፣ ዲዳዎችንም፣ ጉንድሾችንም፣ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፣ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጕንድሾችም ሲድኑ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።”—ማቴዎስ 9:35፤ 15:30, 31

አዎን፣ ኢየሱስ ማንኛውም በሽታ ወይም እክል ያለበትን ሰው ፈውሷል። እንዲያውም ሞተው የነበሩ ሰዎችን አስነስቷል። (ሉቃስ 7:11-17፤ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:38-44) እርግጥ ኢየሱስ የፈወሳቸውም ሆኑ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ተመልሰው መሞታቸው አልቀረም። ቢሆንም የኢየሱስ ተአምራት ወደፊት በመንግሥቱ ግዛት ሥር በዚህች ምድር ለሚኖሩ ሰዎች ምን እንደሚያደርግላቸው አሳይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜያለሁ አይልም” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4

ሁላችንም እንደምናውቀው ዛሬ ማንኛውም ሰው የበሽታና የሞት ተገዥ ነው። ጀርሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሳምማሉ፣ ከዚያም አልፈው ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋሉ። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ አካል አፈጣጠር በጣም አስደናቂ በመሆኑ አንዳንዶች እንዲህ ያለው አካል የሚታመምበት ምክንያት ይደንቃቸዋል። የሕክምና ዶክተር የሆኑት ሉዊስ ቶማስ ባክቴሪያዎች ስለሚሰጡት ጠቃሚ አገልግሎት ከገለጹ በኋላ በሽታ የሚመጣው “እንደ ድንገተኛ አደጋ ነው” ብለዋል። “ይህም የሚሆነው የሕመምተኛው በሽታ የመከላከል ችሎታ በአንድ ልዩ መንገድ እክል ሲያጋጥመው ሳይሆን አይቀርም” በማለት አክለዋል።

በእርግጥም ጠንካራ የሆነ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በባክቴሪያዎች አይጠቁም። ቢሆንም ይዋል ይደር እንጂ ሰዎች ለእርጅናና ለሞት እጃቸውን መስጠታቸው አይቀርም። ለበሽታና ለሞት ምክንያቱ ፍጹም ከነበረው ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረስነው ኃጢአት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሲል ይገልጻል።—ሮሜ 5:12

ይሁን እንጂ አምላክ ልጁ ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ ከፍሎ የሰው ልጆችን ኃጢአት ከሚያስከትለው ውጤት እንዲዋጅ ወደ ምድር ልኮታል። (ማቴዎስ 20:28) መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል። (ሮሜ 6:23፤ 1 ዮሐንስ 5:11) በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የመፈወስ ኃይል ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ይውላል። በዚያ ጊዜ ሁሉም ጀርሞች፣ ባሁኑ ጊዜ በሽታ የሚያመጡት ጀርሞች ጭምር ማንንም የማይጎዱ ይሆናሉ።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ይመጣል ስለሚለውና ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔ ስለሚያስገኘው ስለዚህ መንግሥት ይበልጥ ለማወቅ መፈለግ ተገቢ አይሆንም? የይሖዋ ምሥክሮች ተጨማሪ እውቀት እንድታገኝ በደስታ ይረዱሃል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምን ልታደርግ ትችላለህ?

መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ጀርሞች የሚያስከትሉትን አደጋ ለመቀነስ ምን ልታደርግ ትችላለህ? የዓለም ጤና ድርጅት አንዳንድ መመሪያዎች ሰጥቷል። በመጀመሪያ በሽታን እንዲሁም የኢንፌክሽኖችን መዛመት ለመቀነስ ልንወስድ የምንችላቸውን እርምጃዎች ዘርዝሯል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሰዎች የፀረ ተሕዋሳት መድኃኒት አወሳሰዳቸውን እንዴት ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ ገልጿል።

በሽታዎችንና የበሽታዎችን መዛመት ለመቀነስ ከሁሉ የሚሻለው መንገድ ጤነኛ ሆኖ ለመኖር የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረግ ነው። ጤነኛ ሆነህ ለመኖር ምን ልታደርግ ትችላለህ?

ራስን ከበሽታ ለመጠበቅ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች

1. የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች ለማግኘት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። የተመጣጠነ ምግብ፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴና በቂ እረፍት።

2. የግል ንጽሕና መጠበቅ። የጤና ባለሞያዎች ራስን ከበሽታ ለመጠበቅም ሆነ ለሌሎች በሽታ ላለማስተላለፍ እጅ መታጠብን የመሰለ ጠቃሚ ነገር እንደሌለ አበክረው ይመክራሉ።

3. አንተም ሆንክ ቤተሰብህ የምትመገቡት ምግብ ጤናማ መሆኑን አረጋግጥ። በተለይ ምግቦቻችሁ የሚዘጋጁበት አካባቢና እጆቻችሁ ንጹሕ መሆናቸውን በጥብቅ ተከታተል። በተጨማሪም እጃችሁን ለመታጠብና ምግባችሁን ለማጠብ የምትጠቀሙበት ውኃ ንጹሕ መሆኑን አረጋግጥ። ጀርሞች የሚራቡት በምግብ ውስጥ በመሆኑ ሥጋ ከመመገባችሁ በፊት በደንብ አብስሉት። ምግቦች በቀዝቃዛ ቦታ እንዲቀመጡ አድርጉ።

4. በበራሪ ነፍሳት አማካኝነት ከባድ በሽታ በሚተላለፍባቸው አገሮች እነዚህ ነፍሳት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት በምሽት ወይም ንጋት ላይ ከቤት ውጭ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በእጅጉ ቀንስ። ሁልጊዜ አጎበር ተጠቀም።

5. ክትባቶች በሽታ ተከላካይ ሕዋሳትህን በአካባቢህ በብዛት የሚገኙ ጀርሞችን እንዲዋጉ ሊያሰለጥኑልህ ይችላሉ።

የፀረ ተሕዋሳት መድኃኒቶች አጠቃቀም

1. ማንኛውንም አንቲባዮቲክ ወይም ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒት ከመግዛትህ ወይም ከመውሰድህ በፊት የሕክምና ባለሞያ አማክር። መድኃኒቶችን ለማሻሻጥ ሲባል የሚሰጡ ሥጦታዎች ወይም ቅናሾች የሚጠቅሙት ከሸማቹ ይበልጥ ሻጩን ነው።

2. ሐኪምህ አንቲባዮቲክ መድኃኒት እንዲያዝልህ ግፊት አታድርግ። እንዲህ ካደረግህ ወደ ሌላ ሐኪም እንዳትሄድበት ሲል ብቻ ሊያዝልህ ይችላል። ለምሳሌ ጉንፋን የሚመጣው በቫይረሶች ምክንያት ነው። አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ጉንፋን አያድኑም። ያሳመመህ ቫይረስ ሆኖ ሳለ አንቲባዮቲክ ብትወስድ ጠቃሚዎቹን ባክቴሪያዎች ሊጫናቸውና መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ባክቴሪያዎች በሰውነትህ ውስጥ እንዲራቡ ሊያደርግ ይችላል።

3. አዲስ የተገኘ መድኃኒት ካልታዘዘልኝ ብለህ አትጠይቅ። ላንተ የሚሻለው መድኃኒት እርሱ ላይሆን ወይም የማያስፈልግ ወጪ ሊያስወጣህ ይችላል።

4. ስለ ማንኛውም መድኃኒት አስተማማኝ ከሆነ ምንጭ መረጃ ለማግኘት ሞክር። አገልግሎቱ ምንድን ነው? ምን ተጓዳኝ ጉዳት ይኖረዋል? መድኃኒቱ በሚወሰድበት ጊዜ በሰውነት ውስጥ የሚሠራው እንዴት ነው? ምን ዓይነት አደጋስ ሊያስከትል ይችላል?

5. አንቲባዮቲክ መድኃኒቱ በእርግጥ ተገቢና አስፈላጊ ከሆነ መድኃኒቱን ከመጨረስህ በፊት በሽታው ቢሻልህም እንኳን የታዘዘልህን በሙሉ ጨርሰህ ብትወስድ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ይሆናል። የመድኃኒቱ የመጨረሻ ክፍል ኢንፌክሽኑ ሙሉ በሙሉ መወገዱን ያረጋግጥልሃል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የሰው ልጆች በሽታ አምጪ ከሆኑ ጀርሞች ነፃ ሆነው በደስታ ይኖራሉ