በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪካዊው ወህኒ ቤት የተገኙ የእምነት ተሞክሮዎች

ከታሪካዊው ወህኒ ቤት የተገኙ የእምነት ተሞክሮዎች

ከታሪካዊው ወህኒ ቤት የተገኙ የእምነት ተሞክሮዎች

በዓለም ዙሪያ ፈቃደኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አምላክ ለመቅረብ ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን እስረኞች ለመርዳት ወደተለያዩ ወህኒ ቤቶች ይሄዳሉ። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በአትላንታ ጆርጂያ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ ስናካሂድ ቆይተናል። ወህኒ ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ተፈታታኝ ነው። ፈቃደኛ አገልጋዮች ሆነን ስንሠራ በባንክ ዘረፋ፣ በነፍስ ግድያ፣ ዕፅ በማዘዋወር፣ በማጭበርበር እና አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ያጋጥሙናል። እንደ እነዚህ ዓይነት ግለሰቦችን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

ቅድሚያ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን ወህኒ ቤት የረገጡት መቼና እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጉ ይሆናል። ጊዜው ሐምሌ 4, 1918 ነበር። ስምንት የታወቁ ክርስቲያን አገልጋዮች በጥቁር ድንጋይ የተሠሩትን የዚህን የፌዴራል ወህኒ ቤት 15 ደረጃዎች በጠባቂዎች ታጅበው ወጡ። በጊዜው የተለመደው አሠራር ተግባራዊ ሆኖ ከነበረ ወደ ወህኒ ቤቱ የመጡት ካቴናቸው በወገባቸው ዙሪያ ከታሰረ ሰንሰለት ጋር ተጠፍሮና እግሮቻቸው በእግረ ሙቅ ተከርችመው መሆን አለበት። እነዚህ አዲስ እስረኞች በወቅቱ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው በሚታወቁት በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ በአመራር ቦታ ላይ የነበሩ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች ሲሆኑ የተበየነባቸው ፍርድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢ-ፍትሐዊ መሆኑ ይረጋገጣል ብለው አላሰቡም ነበር። ሆኖም መጋቢት 1919 ስምንቱ ምሥክሮች ከእስር ተፈትተው በእነዚያው ደረጃዎች ተመልሰው ወረዱ። ከጊዜ በኋላ ባለሥልጣናቱ ክሱን ለማንሳት ሲወስኑ ከወንጀል ነጻ እንደሆኑ ተፈረደላቸው። *

እነዚህ ክርስቲያኖች በአትላንታ ወህኒ ቤት በቆዩበት ጊዜ እስረኞችን ሰብስበው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምሩ ነበር። ከስምንቱ እስረኞች መካከል አንዱ የነበረው ኤ ኤች ማክሚላን ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው የወህኒ ቤቱ ምክትል ሹም መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ግን “[ለእስረኞቹ] የምታስተምሯቸው ትምህርቶች ግሩም ናቸው!” በማለት አድናቆቱን ለመግለጽ ተገፋፍቷል።

ዛሬ ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላም በዚሁ ወህኒ ቤት ውስጥ የሚሰጡት ውጤታማ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በእስረኞች ሕይወት ላይ ዘላቂ የሆነ ስሜት ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። በተለያዩ ጊዜያት የወህኒ ቤቱ ባለሥልጣናት እየተመላለሱ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስጠኑት የቡድናችን አባላት መካከል አንዳንዶቹን መርጠው ልዩ የምሥክር ወረቀትና የክብር ሽልማት ሰጥተዋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ፕሮግራም ውጤታማነት በዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ቢሮ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በሚያሳትመው ቮለንቲር ቱዴይ በተባለው የዜና መጽሔትም ላይ ወጥቷል።

ከእስረኞቹ ጋር የሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራም ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ተማሪዎቹ የሚያስደንቅ የጠባይ መሻሻል ማድረጋቸው ነው። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች የተፈረደባቸውን ጊዜ ሳይጨርሱ ሊፈቱ ችለዋል። ይህን የታዘቡ አንዳንድ ተጠራጣሪ ሰዎች እስረኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር የሚያጠኑት ለዚህ ሲሉ ብቻ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። እንዲህ የሚያደርግ ከስንት አንድ ሊኖር ቢችልም አብዛኛው ተሞክሮ የሚያሳየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ከእስር ከተለቀቁ ከብዙ ዓመታት በኋላም መልካም ክርስቲያናዊ ጠባያቸውን እስከ አሁን እንደጠበቁ መሆናቸውን ስንሰማ እንደሰታለን። በዚህ ታሪካዊ ወህኒ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ካገኘናቸው አስደሳች ተሞክሮዎች መካከል ጥቂቶቹን እነሆ።

ስደተኛ እስረኞች ተስፋ ፈነጠቀላቸው

በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአትላንታ ወህኒ ቤት ውስጥ ስንሰብክ ብዙ ስደተኛ እስረኞችን የመርዳት መብት አግኝተን ነበር። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አስደናቂ የሆነ የባሕርይ ለውጥ አድርገዋል።

ራውል * በጣም አደገኛ እስረኛ ነበር። እሱና ጓደኛው በነፍስ ግድያ የታሰሩ የታወቁ ወንጀለኞች ሲሆኑ ለምን ተነካን የሚሉ ጠበኛ ሰዎች እንደነበሩ ሲረዷቸው የነበሩት ሽማግሌዎች ተናግረዋል። ራውል በነፍስ የሚሹት ጠላቶች ነበሩት። አንድ ሰው ራውልን ለመግደል ምሎ የነበረ ሲሆን ራውልም ሰውዬውን ለመግደል ምሎ ነበር። ራውል ቀንደኛ ጠላቱ ወደ አትላንታ ወህኒ ቤት መዛወሩን ሲሰማ ፍርሃት አደረበት። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እነዚህ የረጅም ጊዜ ጠላቶች ግቢ ውስጥ፣ በካፊቴሪያው አሊያም በአንዱ የእስር ቤቱ ሕንፃ ውስጥ መገናኘታቸው የማይቀር ነበር። ይሁን እንጂ ራውል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ በአስተሳሰብ፣ በባህርይና በአለባበስ አስገራሚ ለውጥ አደረገ። ሁለቱ ሰዎች በመጨረሻ በግቢው ውስጥ ሲገናኙ ያ በጥብቅ ይፈልገው የነበረው ጠላቱ ራውልን መለየት እንኳ አልቻለም። ደም ማፋሰሱ እንደማይቀር ተፈርቶ የነበረው ጠብ ሳይከሰት ቀረ።

ራውል ለአምላክ ራሱን መወሰኑን በጥምቀት ለማሳየት ሲወስን ለዚህ ተስማሚ የሆነ የውኃ ገንዳ አስፈለገ። የወህኒ ቤቱ ቄስ እንደ መጠመቂያ ገንዳ የሚያገለግል ጥቁር የሬሳ ሳጥን በመስጠት ተባበረን። የሬሳ ሳጥኑ እስከ አፉ በውኃ ተሞላ። ነገር ግን ራውል ከሬሳ ሳጥኑም የሚተልቅ ይመስል ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሠረት ራውልን ሙሉ በሙሉ ውኃው ውስጥ ለማጥለቅ ሁለት ሽማግሌዎች መተጋገዝ አስፈልጓቸው ነበር። (ሉቃስ 3:21 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በአሁኑ ወቅት ራውል ከእስር የተለቀቀ ሲሆን ቀናተኛ ክርስቲያን ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

በ1987 አብዛኞቹን ስደተኛ እስረኞች ከአገር ለማባረር የተደረገው ውሳኔ ዓለም አቀፍ የዜና ሽፋን የተሰጠውን በንብረት ላይ ውድመት ያደረሰና ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ብጥብጥ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ከማስከተሉም በላይ የታገቱ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ በዚህ አደገኛ በሆነና ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ በሚችል ዓመፅ አንካፈልም ብለው በሕይወታቸው የቆረጡ ደፋር ስደተኛ እስረኞች ነበሩ። እነዚህም ከእኛ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ናቸው። እነዚህ በአንድ ወቅት እስከ ሞት እንኳ ከመፋለም የማይመለሱ የነበሩ ሰዎች አሁን በዓመፁና በንብረት ማጥፋቱ እጃቸውን ባለማስገባት ገለልተኝነታቸውን ጠብቀዋል። መጽሐፍ ቅዱስ አረመኔ ወንጀለኞችን እንኳን ሰላም ወዳድ ክርስቲያኖች አድርጎ በመለወጥ ረገድ ያለውን ኃይል የሚያሳይ እንዴት ያለ ሕያው ማስረጃ ነው!​—⁠ዕብራውያን 4:12

ምህረት ማግኘት

ሌላው የማይረሳው ተሞክሮ የጄምስ ነው። ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክር የነበረ ቢሆንም በመንፈሳዊ በመድከሙ በፈተና የተሸነፈ ሲሆን የባንክ ማጭበርበር ወንጀል ፈጸመ። ጄምስ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ፤ ከዚያም በአትላንታ የፌዴራል ወህኒ ቤት ታሰረ። ከጊዜ በኋላ “በሕይወቴ ያሳለፍኩት የመጨረሻ መሪር ወቅት ነበር” በማለት ነግሮናል።

የወህኒ ቤት ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። ጄምስ “ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ያሰቃየኝ ነበር” በማለት ያስታውሳል። ይሁን እንጂ በተጨናነቀች የእስር ቤቱ ክፍል ውስጥ መታጎሩ ራሱን በጥልቅ እንዲመረምር አደረገው። እንዲህ ብሎ ገልጾታል:- “እስር ቤት እያለሁ በጣም ይሰማኝ የነበረው የእኔ ምቾት ማጣት ሳይሆን ሰማያዊ አባቴን ማሳዘኔ ነበር።” ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከፈቃደኛ ምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና የነበረ አንድ እስረኛ ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥበት ክፍል አብሮት እንዲገኝ ጋበዘው። ጄምስ መጀመሪያ ላይ እፍረት ስለተሰማው እምቢ አለ። ሆኖም ወጣቱ እስረኛ በጣም ስለጨቀጨቀው አንድ እሁድ ቀን በስብሰባው ላይ ተገኘ።

ትምህርቱን የሚሰጡት ምሥክሮች ለተማሪዎቻቸው የሚያሳዩትን ፍቅራዊ አሳቢነት ሲመለከት ጄምስ በጥልቅ ተነካ። በኋላ ሌላም የነካው ነገር ነበር። ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው በመነሳት ሁሉም ሃይማኖታዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለእስረኞች ለሚሰጡት አገልግሎት ዳጎስ ያለ ክፍያ ያገኛሉ ብሎ አስቦ ነበር። ነገር ግን ምሥክሮቹ ለሚሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ በማቅረብ የወጪ መሸፈኛ እንደማይጠይቁና ምንም ገንዘብ እንደማይከፈላቸው ሲያውቅ በጣም ተደነቀ።​—⁠ማቴዎስ 10:8

ጄምስ ስብሰባዎቹን በጉጉት መጠባበቅ ጀመረ። ስብሰባዎቹን የሚመሩትን ወንድሞች ርኅሩኅና የሚያበረታቱ ሆነው አገኛቸው። በተለይ ለአንድ ሽማግሌ ልዩ አክብሮት ነበረው። ጄምስ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ሊጎበኘኝ የሚመጣበትን ቀን በጉጉት እጠባበቅ ነበር። ምክንያቱም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ሕያው አድርጎልኛል፤ የሚጋባ መንፈስ ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ እያጤኑ ማንበብ የመልእክቱን እውነተኛ መንፈስ ለመረዳት ማለትም ሙሉ በሙሉ ከራሴ ጋር ለማዋሃድ ከሁሉም በላይ ደግሞ የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማዳበር አስፈላጊ መሆኑን እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

ጄምስ ኃጢአቱን አምላክ ይቅር ሊለው እንደሚችል ማመን ከብዶት ነበር። ታዲያ የረዳው ምን ነበር? “ታማኝ የሆኑና ራስን ለሌሎች የመሠዋት መንፈስ ያላቸው ሰዎች ያደረጉልን እንክብካቤ የአምላክን ይቅር ባይነት ያንጸባርቅ ነበር። * የፈጸምኩት ኃጢአት ከባድ ቢሆንም ይረዳኝ የነበረው ወንድም ይሖዋ ፈጽሞ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል እንዲሰማኝ አድርጎ እንደማያውቅ አስተዋልኩ። ይሖዋ ፈጽሞ አይተወኝም። ከልብ ንስሐ እንደገባሁና ይህንን ከንቱ የሆነ የአጭበርባሪነት ሕይወት እርግፍ አድርጌ እንደተውኩ በማየት አብዝቶ ባርኮኛል።” ጄምስ ውገዳው ተነስቶለት ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተመልሷል። ከእስር ከተለቀቀበት ከዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በትጋትና በቅንዓት ማገልገሉን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት የጉባኤ አገልጋይነት መብት አግኝቶ በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር መስጠት መቻሉ ሚስቱንና ቤተሰቦቹን እጅግ አስደስቷቸዋል።

ወደ እውነት መመለስ

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከጆኒ ጋር ተገናኘን። ቤተሰቦቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም ጆኒ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ መመሪያ ያስፈልገው በነበረበት በለጋ ዕድሜው አንዳቸውም በመንፈሳዊ ጠንካሮች አልነበሩም። ጆኒ ቀስ በቀስ ወደ ወንጀል ሕይወት ገባ። ከአትላንታ ወህኒ ቤት አጠገብ በሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ካምፕ ውስጥ እንዲታሰር ተፈረደበት። በካምፑ ውስጥ ታስሮ እያለ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራማችን ሰማና ለመገኘት ወሰነ።

በመጀመሪያ አካባቢ ጆኒ የንባብ ችሎታው በጣም ዝቅተኛ ነበር። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በደንብ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው የንባብ ችሎታውን ለማሻሻል ቆረጠ። (ዮሐንስ 17:3) የምንሰጠው ትምህርት በዚህ ረገድ በተለይም አንብቦ የመረዳት ችሎታንና ሕዝባዊ ንባብን በተመለከተ እስረኞችን ይረዳል። ጆኒ በትምህርቱ ጠንክሮ በመሥራት ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዴት መሆን እንዳለበት አርአያ ስለሆናቸው አብረውት በሚማሩት ዘንድ አክብሮትን አተረፈ።

ከወራት በኋላ ጆኒ አደገኛ ዕፅን አስመልክቶ በሚሰጠው ትምህርታዊ ፕሮግራም ላይ እንዲገኝ በአላባማ ታላዴጋ ወደሚገኘው የፌዴራል ሕንጻ ተዛወረ። እዚያ እንደደረሰ ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረ ሲሆን ከእስር እስከተፈታበት ጊዜ ድረስ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። በተፈታበት ቀን ወዲያውኑ በትውልድ ከተማው ውስጥ ካሉት ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። እዚያም ወዳጃዊ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን ቀጠለ።

ጆኒ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረው ፍቅርና አድናቆት እናቱም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች የበለጠ ተሳትፎ እንድታደርግ ያበረታታት ሲሆን ከፍተኛ የብርታትና የድጋፍ ምንጭ ሆኖላታል። በቅርቡ ራሱን ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን በጥምቀት በማሳየት በክርስቲያናዊ አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

የተትረፈረፈ መከር

ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በአትላንታ ወህኒ ቤት የሚገኙ ከ40 በላይ የሚሆኑ እስረኞች የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ እርዳታ የተደረገላቸው ሲሆን ከ90 በላይ የሚሆኑ ሌሎች እስረኞችም ከሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጠቃሚ ሆነዋል። ከእስር ከተለቀቁ ወይም ወደ ሌላ ወህኒ ቤት ከተዛወሩ በኋላ የተጠመቁ እስረኞችም አሉ።

ወደዚህ ታሪካዊ ወህኒ ቤት በየሳምንቱ እየሄድን በፈጸሙት ጥፋት ከልብ የተጸጸቱ እስረኞችን በመርዳት በዚህ ልዩ የሆነ ክርስቲያናዊ አገልግሎት መሳተፍ በመቻላችን አመስጋኝ ነን። (ሥራ 3:19፤ 2 ቆሮንቶስ 7:8-13) የጥበቃ ማማዎች፣ ዘቦች፣ ባለ ቆንጥር ሽቦ አጥሮች እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚከፈቱና የሚዘጉ በሮች ባሉበት በዚህ አስፈሪ ስፍራ አደገኛ ወንጀለኞች በአኗኗራቸው ለውጥ አድርገው ሐቀኛ ዜጎች ሲሆኑና አምላክን በታማኝነት ሲያመልኩ ስንመለከት በደስታና በአድናቆት ስሜት እንዋጣለን።​—1 ቆሮንቶስ 6:9-11​—⁠ተጽፎ የተላከልን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ይህን ክስ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ከገጽ 647-​56 ተመልከት።

^ አን.9 የእስረኞቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.17 የሚያዝያ 15, 1991 መጠበቂያ ግንብ ሽማግሌዎች ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገዱ ሰዎችን ሄደው እንዲጎበኙ አበረታቶ ነበር። የጉብኝቱ ዓላማ ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ማበረታታት ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 2:​6-8

[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

‘የተወሰኑ የቅርብ ወዳጆቼን አስተናግዳችኋል’

በወቅቱ በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ውስጥ ያገለግል የነበረው ፍሬደሪክ ደብሊው ፍራንዝ ሚያዝያ 1983 በአትላንታ የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትስ ወህኒ ቤት ጎብኝቶ ነበር። ይህን ወህኒ ቤት ለመጎብኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ወደ ሕንጻው ሲገባ በእንግዳ መቆያ ክፍል ውስጥ ባለው ዴስክ አጠገብ ተቀምጦ ለነበረው ዘብ ድምፁን ጮክ አድርጎ እንዲህ አለው:- “እዚህ ወህኒ ቤት የተወሰኑ የቅርብ ወዳጆቼን አስተናግዳችሁ እንደነበር እንድታውቅ እፈልጋለሁ!” ዘቡ ግራ ስለተጋባ ፈዝዞ ቀረ። ፍራንዝ የተናገረው ስለ ምን ነበር?

ከ64 ዓመታት በፊት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድና ሰባት ተባባሪዎቹ ሕዝብን በማሳደም ወንጀል በሐሰት ተፈርዶባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ራዘርፎርድና ፍራንዝ የቅርብ ወዳጆችና የሥራ ባልደረባዎች ሆነዋል። ራዘርፎርድ ከሞተ ከ40 ዓመት በኋላ ፍራንዝ በ90 ዓመት ዕድሜው ወዳጁ ታስሮ የነበረበትን ስፍራ መጎብኘት መቻሉ አስደስቶታል። ራዘርፎርድና ተባባሪዎቹ በዚህ ወህኒ ቤት ውስጥ ስላከናወኑት ሥራ እንዳስታወሰ ምንም ጥርጥር የለውም። ያከናወኑት ሥራ ምን ነበር?

ራዘርፎርድና ተባባሪዎቹ ከመጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የወህኒ ቤቱ ምክትል ሹም “አንዳንድ የምትሠሩት ሥራ ልንሰጣችሁ ነው። ምን መሥራት ትችላላችሁ?” አላቸው።

ከስምንቱ አንዱ የነበረው ኤ ኤች ማክሚላን እንዲህ ብሎ መለሰ:- “ምክትል ሹም፣ ከመስበክ በስተቀር በሕይወቴ አንድም ሥራ ሠርቼ አላውቅም። እንደዚያ ዓይነት ሥራ እዚህ አላችሁ?”

“ጌታዬ እዚህ ለመታሰር የበቃኸው በመስበክህ ነው! እዚህ አንዲት ቃል መስበክ እንደማትችል ከአሁኑ ቁርጥህን እወቅ።”

በርካታ ሳምንታት አለፉ። እስረኞቹ ሁሉ እሁድ ዕለት በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ቀጥሎ ላለው የሰንበት ትምህርት ደግሞ የፈለገ ሁሉ መቆየት ይችላል። ስምንቱ ሰዎች በየተራ የሚመሩት የራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ለማቋቋም ወሰኑ። ከጊዜ በኋላ ራዘርፎርድ “አንዳንድ የማወቅ ጉጉት ያደረባቸው ሰዎች መገኘት የጀመሩ ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ሰዎች ይመጡ ነበር” በማለት ተናግሯል። ብዙም ሳይቆይ በስምንት ሰዎች የተጀመረው ቡድን ወደ 90 አደገ!

እስረኞቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራሙ የሰጡት ምላሽ ምን ይመስል ነበር? አንድ እስረኛ እንዲህ ብሏል:- “የ72 ዓመት ሰው ነኝ፤ እውነትን ለመስማት የቻልኩት እስር ቤት በመግባቴ ነው። ስለዚህ ወህኒ ቤት በመላኬ ደስተኛ ነኝ።” ሌላም እስረኛ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “የእስር ጊዜዬ ወደ ማለቁ ነው፤ ከዚህ በመውጣቴ አዝናለሁ . . . ስወጣ እንደ እናንተ ዓይነት ሰዎችን የት ማግኘት እንደምችል ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?”

ስምንቱ ሰዎች ከእስር ከመለቀቃቸው በፊት በነበረው ምሽት በመጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ፕሮግራሙ ሲካፈል ከነበረ አንድ ወጣት ልብ የሚነካ ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር:- “ምንም እንኳን የማልረባ፣ ርካሽና በዓለም የጎደፍኩ ሰው ብሆንም የተሻልኩና የተከበርኩ ሰው የመሆን ፍላጎት በውስጤ እንደተከላችሁ እንድታውቁ እፈልጋለሁ። . . . ደካማ ነኝ፣ በጣም ደካማ፤ ይህን ከእኔ ይበልጥ ማንም አያውቅም፣ ቢሆንም ከራሴ አልፌ በአካባቢዬ ያሉትን በመርዳት የተከላችሁት ዘር በሚገባ አፍርቶ ማየት እችል ዘንድ ጥረት አደርጋለሁ፣ አስፈላጊ ከሆነም ከራሴ ጋር እታገላለሁ። እንደ እኔ ካለው ሰው ይህን መስማት ሊያስገርም ይችላል፤ ነገር ግን የምናገረው ሁሉ ከልቤ ነው።”

ዛሬም ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ በአትላንታ ማረሚያ ቤትም ሆነ በሌሎች ወህኒ ቤቶች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘር በመዘራት ላይ ይገኛል።​—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7