በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

“አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

“አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

ሉርዴስ እየተንቀጠቀጡ ያሉትን ከንፈሮችዋን በጣቶቿ ሸፍና በአፓርታማዋ መስኮት በኩል ውጪውን ትኩር ብላ ትመለከታለች። የላቲን አሜሪካ ሴት ስትሆን ኃይለኛ የሆነው ባሏ አልፍሬዶ ለ20 ዓመታት ሲያሠቃያት ኖሯል። አልፍሬዶ ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳ ቢሆንም እንኳ ሉርዴስ ያሳለፈችውን አካላዊና ስሜታዊ ሥቃይ መናገሩ ቀላል ሆኖ አላገኘችውም።

“ችግር መፈጠር የጀመረው ገና በተጋባን በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው” አለች ሉርዴስ ዝግ ባለ አንደበት። “አንድ ጊዜ በቡጢ ሲለኝ ሁለት ጥርሶቼ ረገፉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሰነዘረብኝ ቡጢ ጎንበስ ብዬ ሳመልጥ ቁም ሳጥኑን ጠረመሰው። ይበልጥ የጎዱኝ ግን የሚናገራቸው መጥፎ ቃላት ናቸው። ‘የማትረቢ ቆሻሻ’ ይለኝ ነበር። ምንም የማይገባኝ ደደብ አድርጎ ነበር የሚመለከተኝ። ጥዬው እንዳልሄድ የሦስቱ ልጆቼ ነገር ሐሳብ ሆነብኝ።”

አልፍሬዶ የሉርዴስን ትከሻ እየደባበሰ “ትልቅ ቦታ ያለኝ ባለሙያ ሆኜ ሳለ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሲደርሰኝና ምንም ዓይነት በደል እንዳላደርስባት የሚያስጠነቅቅ ትእዛዝ ሲሰጠኝ በኃፍረት ተሸማቀቅኩ” ሲል ተናገረ። “ለመለወጥ ጥረት ባደርግም ብዙም ሳይቆይ ወደ ወትሮው ልማዴ ተመለስኩ።”

ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው? “በመንገዱ ዳር የሚገኘው ሱቅ ውስጥ ያለችው ሴት የይሖዋ ምሥክር ነች” ስትል ሉርዴስ ገለጸች፤ አሁን ዘና እንዳለች ፊቷ ላይ በግልጽ ይነበባል። “መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማወቅ እንድችል ልትረዳኝ ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸችልኝ። ይሖዋ አምላክ ሴቶችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ተገነዘብኩ። መጀመሪያ ላይ አልፍሬዶን ክፉኛ ቢያስቆጣውም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በመንግሥት አዳራሹ ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ለእኔ አዲስ ገጠመኝ ነበር። የራሴ የሆነ እምነት ሊኖረኝ እንደሚችል፣ የማምንባቸውን ነገሮች በነፃነት መግለጽና አልፎ ተርፎም ለሌሎች ማስተማር እንደምችል ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ። በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለኝ ተረዳሁ። ይህም ብርታት ሰጠኝ።

“መቼም ልረሳው የማልችል አንድ ትልቅ ለውጥ ተፈጠረ። አልፍሬዶ በየሳምንቱ እሁድ በካቶሊክ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ መገኘቱን ቀጥሎ ስለነበር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የጀመርኩትን ግንኙነት አጥብቆ ይቃወም ነበር። ትኩር ብዬ ዓይን ዓይኑን እያየሁ ትምክህት በተሞላበትና በረጋ መንፈስ ‘አልፍሬዶ፣ የአንተ አመለካከትና የእኔ አመለካከት የተለያየ ነው’ አልኩት። የሚገርመው ሊመታኝ አልቃጣም! ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቅኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ላለፉት አምስት ዓመታት ፈጽሞ መትቶኝ አያውቅም።”

ይሁን እንጂ ከዚህ የላቀ ለውጥ የሚፈጠርበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። አልፍሬዶ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሉርዴስ ከተጠመቀች ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ቤቱ ጋበዘኝና በጣም ደስ የሚሉ ሐሳቦችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አካፈለኝ። ለሚስቴ ሳልነግር ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ከሉርዴስ ጋር በስብሰባዎች መገኘት ጀመርኩ። እዚያ የምሰማቸው ብዙዎቹ ንግግሮች ከቤተሰብ ሕይወት ጋር የተያያዙ ስለነበሩ ብዙውን ጊዜ በኀፍረት እሸማቀቅ ነበር።”

አልፍሬዶ ከስብሰባ በኋላ ወንዶችን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ወለሉን ሲያጸዱ በመመልከቱ ልቡ በጣም ተነካ። ወደ ቤታቸው ሲሄድ ደግሞ ባሎች ሚስቶቻቸውን ዕቃ በማጠብ ሲረዷቸው ተመለከተ። እነዚህ እንደ ቀላል የሚታዩ ገጠመኞች አልፍሬዶ እውነተኛ ፍቅር እንዴት በተግባር እንደሚገለጽ እንዲያስተውል አደረጉት።

ብዙም ሳይቆይ አልፍሬዶ ተጠመቀ። አሁን እሱና ሚስቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። “ብዙውን ጊዜ ምግብ ከተበላ በኋላ ዕቃዎቹን በማነሳሳትና አልጋ በማንጠፍ ይረዳኛል” አለች ሉርዴስ። “ለሠራሁት ምግብ አድናቆቱን የሚገልጽልኝ ከመሆኑም በላይ ሙዚቃን ወይም ለቤታችን የምንገዛቸውን ነገሮች በመሳሰሉ ጉዳዮች የራሴን ምርጫ እንዳደርግ ይፈቅድልኛል። እነዚህ ነገሮች ቀደም ሲል አልፍሬዶ ፈጽሞ የማያደርጋቸው ነበሩ! በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ እቅፍ አበባ ገዛልኝ። አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለኝ ተረዳሁ። ይህም ብርታት ሰጠኝ”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባሎች ሚስቶቻቸውን ዕቃ በማጠብ ሲረዷቸው ተመለከተ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልፍሬዶ ከስብሰባ በኋላ ወንዶችን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ወለሉን ሲያጸዱ በመመልከቱ ልቡ በጣም ተነካ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ እቅፍ አበባ ገዛልኝ”