በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸውን?

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸውን?

“የመላው አጽናፈ ዓለም አምላክ በአንድ ሃይማኖታዊ መንገድ ብቻ እንዲመለክ ይፈልጋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው” በማለት ማርኩስ ቦርግ የተባሉ ደራሲ ጽፈዋል። የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ዴስሞንድ ቱቱ ሁሉንም የእምነት “ምሥጢር አውቃለሁ ብሎ ሊናገር የሚችል አንድም ሃይማኖት የለም” በማለት ተናግረዋል። የሂንዱ እምነት ተከታዮች “ጆቶ ሞዝ፣ ቶቶ ፖዝ” የሚል የታወቀ አባባል አላቸው። ይህም ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ ግብ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው እንደማለት ነው። ቡዲስቶችም ይህን አባባል ይጋራሉ። አዎን፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸው የሚል እምነት አላቸው።

ጄፍሬ ፓሪንደር የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “ሁሉም ሃይማኖቶች ግባቸው አንድ ነው ወይም ወደ እውነት የሚያደርሱ ተመሳሳይ መንገዶች ናቸው ወይም ሁሉም የሚያስተምሩት አንድ ዓይነት መሠረተ ትምህርቶችን ነው እየተባለ ይነገራል።” በእርግጥም ደግሞ በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት፣ የሚካሄደው የአምልኮ ሥርዓትና የሚመለኩት ነገሮች ተመሳሳይ ናቸው። ብዙዎቹ ሃይማኖቶች ስለ ፍቅር ይናገራሉ እንዲሁም መግደል፣ መስረቅና መዋሸት ስህተት እንደሆኑ ያስተምራሉ። በብዙ የሃይማኖት ቡድኖች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋሉ። ታዲያ አንድ ሰው በቅንነት እስካመለከና ጥሩ ሰው ሆኖ ለመኖር ጥረት እስካደረገ ድረስ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን ለውጥ ያመጣልን? ወይስ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ብቻ ናቸው?

ቅንነት ብቻውን በቂ ነውን?

ክርስቲያን ሐዋርያ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመባል የሚታወቀው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረውን ሳውል የተባለውን አይሁዳዊ ሰው ሁኔታ ተመልከት። ለአይሁድ እምነት ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ሲሆን ይህም የተሳሳተ ሃይማኖት እንደሆነ አድርጎ የቆጠረውን የክርስቶስ ተከታዮች ይከተሉት የነበረውን ሃይማኖት ለማጥፋት እንዲነሳሳ አደረገው። (ሥራ 8:​1-3፤ 9:​1, 2) ይሁን እንጂ ሳውል አምላክ ካሳየው ምሕረት እንደ እርሱ ያሉ ሃይማኖተኛ ሰዎች ለአምላክ ቅንዓት ሊኖራቸው ቢችልም የተሟላ እውቀት ስለሚጎድላቸው ሊሳሳቱ እንደሚችሉ ተገንዝቧል። (ሮሜ 10:​2) ሳውል ስለ አምላክ ፈቃድና ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ተጨማሪ እውቀት እያገኘ ሲሄድ ለውጥ አደረገና ቀድሞ ያሳድዳቸው ከነበሩት ከኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ጋር ሆኖ ማምለክ ጀመረ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​12-16

መጽሐፍ ቅዱስ በመቶዎች የሚቆጠሩ እምነቶች እንዳሉና ከእነዚህ እምነቶች መካከል የትኛውንም ብንመርጥ አምላክ እንደሚቀበለው ይናገራል? ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያው ጳውሎስ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ መመሪያ ሰጥቶታል። ኢየሱስ “ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን [ይ]ከፍት ዘንድ” ወደ አሕዛብ ልኮታል። (ሥራ 26:​17, 18) በግልጽ ለማየት እንደምንችለው የምንመርጠው ሃይማኖት ልዩነት ያመጣል። ጳውሎስ በተላከበት አገር ይኖሩ የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች የራሳቸው ሃይማኖት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ‘በጨለማ’ ውስጥ ነበሩ። በእርግጥ፣ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሱና የአምላክን ሞገስ የሚያስገኙ የተለያዩ መንገዶች ብቻ ቢሆኑ ኖሮ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሠሩት ለሰጣቸው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ማሠልጠን አያስፈልገውም ነበር።​—⁠ማቴዎስ 28:​19, 20

ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:​13, 14) መጽሐፍ ቅዱስ ምንም በማያሻማ ሁኔታ “አንድ ሃይማኖት” ብቻ እንዳለ ይናገራል። (ኤፌሶን 4:​5) “ሰፊ” በሆነው መንገድ ላይ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ሃይማኖት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሆኖም የሚከተሉት እዚህ ላይ የተገለጸውን “አንድ ሃይማኖት” አይደለም። ያለው እውነተኛ አምልኮ አንድ ብቻ እስከሆነ ድረስ ይህንን እውነተኛ እምነት ለማግኘት መፈለግ አለባቸው።

እውነተኛውን አምላክ ፈልግ

የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አምላክ ከሰው ልጆች ምን እንደሚፈልግ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​15-17፤ 4:​3-5) እሱ ያወጣቸው መስፈርቶች ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍረዋል። ይህም ተቀባይነት ያለውን አምልኮና ተቀባይነት የሌለውን አምልኮ ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል። (ማቴዎስ 15:​3-9) አንዳንዶች ሃይማኖታቸውን በውርስ የተቀበሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በሚኖሩበት አካባቢ ብዙሃኑ የሚከተለውን ሃይማኖት ይይዛሉ። ለብዙዎች ሃይማኖት ማለት በተወለዱበት ጊዜና አካባቢ የሚወሰን ነገር ነው። ይሁን እንጂ የሃይማኖት ምርጫህን አጋጣሚ እንዲወስንልህ ወይም ሌሎች ሰዎች እንዲመርጡልህ ማድረግ ይኖርብሃልን?

የሃይማኖት ምርጫህ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከመረመርክ በኋላ በምታገኘው እውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ዝም ብሎ ከመቀበል የበለጠ ነገር አድርገዋል። “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን መረመሩ።” (ሥራ 17:​11፤ 1 ዮሐንስ 4:​1) አንተም ልክ እንደዚሁ ለምን አታደርግም?

መጽሐፍ ቅዱስ የአጽናፈ ዓለሙ አምላክ እርሱን በእውነት የሚያመልኩትን ሰዎች እንደሚፈልግ ይገልጻል። በ⁠ዮሐንስ 4:​23, 24 ላይ እንደተመዘገበው ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ‘ንጹሕ የሆነና ነውር የሌለበት አምልኮ’ ነው። (ያዕቆብ 1:​27) አምላክ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሕይወት የሚወስደውን ቀጭን መንገድ ለማግኘት ያደረጉትን ፍለጋ ባርኮላቸዋል። አምላክ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ግድ የለሽ ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን እርሱ ያዘጋጀውን ጠባብ መንገድ ለማግኘትና መንገዱንም ተከትለው ለመጓዝ ከፍተኛ ጥረት ለሚያደርጉት ነው።​—⁠ሚልክያስ 3:​18