ተስፋ መከራን እንድቋቋም ኃይል ሰጥቶኛል

ተስፋ መከራን እንድቋቋም ኃይል ሰጥቶኛል

ተስፋ መከራን እንድቋቋም ኃይል ሰጥቶኛል

ሚቺኮ ኦጋዋ እንደተናገረችው

ሚያዝያ 29 ቀን 1969 ከፖሊስ ጣቢያ ስልክ ተደወለልኝ። ባለቤቴ ሴኪቺ የመኪና አደጋ ደርሶበት ሆስፒታል ገብቶ ነበር። ሁለቱን ትናንሽ ወንዶች ልጆቼን አንድ ጓደኛዬ ጋር ትቼ እየተጣደፍኩ ወደ ሆስፒታሉ ሄድኩ። ሴኪቺ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰውነቱን ማዘዝ አልቻለም፤ እስከዛሬም ድረስ ራሱን አያውቅም። ስለ ቤተሰባችንና የገጠመንን ችግር እንዴት ልንወጣ እንደቻልን ልንገራችሁ።

የተወለድሁት የካቲት 1940 በጃፓን ኮቤ አቅራቢያ በምትገኘው በሳንዳ ነው። ሴኪቺና እኔ የምንተዋወቀው መዋዕለ ሕፃናት አብረን ከተማርንበት ጊዜ አንስቶ ነው። በየካቲት 16, 1964 ተጋባን። ባለቤቴ ዝምታን የሚመርጥና ልጆች የሚወድ ሰው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሪዩሱኬ እና ኮሄይ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለድን።

ሴኪቺ ተቀጥሮ የሚሠራው ቶኪዮ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የግንባታ ድርጅት ስለነበር ከተጋባን በኋላ ከከተማው ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ መኖር ጀመርን። በጥቅምት 1967 አንዲት ወጣት መጥታ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ መሆኗን በመግለጽ አነጋገረችኝ። “አመሰግንሻለሁ፤ የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ አለኝ” አልኳት።

“መጽሐፍ ቅዱሱን ልታሳዪኝ ትችያለሽ?” ስትል ጠየቀችኝ።

ከመጽሐፍ መደርደሪያችን ውስጥ የሴኪቺን መጽሐፍ ቅዱስ ወስጄ አሳየኋት። እርሷም ይሖዋ የሚለውን ስም አውጥታ አሳየችኝ። ይህ የአምላክ ስም መሆኑን አላውቅም ነበር። ሴትየዋ ሁለቱን ትናንሽ ልጆቼን ስትመለከት “ልጅህን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” የሚለውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አነበበችልኝ። (ምሳሌ 22:6) በእርግጥም ደግሞ ልጆቼን በተሳካ መንገድ ማሳደግ የምችለው እንዴት ነው እያልኩ አስብ ነበር። በመሆኑም ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ፈለግሁ።

ሴትየዋ ወደ ቤት እንድትገባ ጋበዝኳትና “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” በሚለው ብሮሹር አማካኝነት ውይይት ጀመርን። ‘በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆነን አስደሳች ሕይወት መምራት ብንችል እንዴት ግሩም ነበር’ ብዬ አሰብሁ! ሴኪቺ ወደ ቤት ሲመለስ “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እፈልጋለሁ” አልኩት።

“ፍቅሬ፣ ያን ያህል እኮ የጠለቀ እውቀት ማግኘት አያስፈልግሽም። ማወቅ የምትፈልጊውን ነገር እኔ እነግርሻለሁ” አለኝ። የሆነ ሆኖ በየሳምንቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ወዲያውም በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመርኩ።

የመከራችን መጀመሪያ

ቀደም ሲል በጠቀስኩት በዚያ የሚያዝያ 1969 ምሽት ሆስፒታል ስደርስ ልጆቼን እንድትጠብቅልኝ አደራ ብያት የመጣሁት ሴት ባል የሆነው የሴኪቺ ጓደኛ አደጋው በደረሰበት ታክሲ ውስጥ አብሮ እንደነበር ሳውቅ በጣም ደነገጥሁ። የባሌ ጓደኛ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሞተ።

በዚያ ዕለት ምሽት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሴኪቺም በሕይወት የመቀጠል ተስፋ ስለሌለው ከመሞቱ በፊት ሊያዩት ይገባል የምላቸውን ሰዎች እንድጠራ ነገሩኝ። ከራስ ቅሉ ግርጌ ስንጥቅ የነበረው ሲሆን ሴሬብረም የሚባለው የአንጎሉ ክፍል ጉዳት ደርሶበት ነበር። በሚቀጥለው ቀን ዘመዶቹ ሁሉ ከኮቤ አካባቢ ተሯሩጠው መጡ።

በሆስፒታሉ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ “የሴኪቺ ኦጋዋ ዘመዶች ቶሎ ገብታችሁ እዩት” የሚል ድምፅ ተሰማ። ወዲያው ለበሽተኞች ለየት ያለ ክትትል ወደሚደረግበት ክፍል እየተሯሯጥን ሄደን በየተራ ተሰናበትነው። ይሁን እንጂ እንደዚያ በመሰለው አስጊ ሁኔታ አንድ ወር ቆየ። መጨረሻ ላይ በተደረገለት ምርመራ ደግሞ በዚሁ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል ይችላል ተባለ።

በመሆኑም ሴኪቺ ከቶኪዮ 650 ኪሎ ሜትር በአምቡላንስ ተጉዞ ወደ ኮቤ እንዲዛወር ተደረገ። እኔ እርሱን ሸኝቼ ሕይወቱ እንዲተርፍ እየጸለይኩ በፈጣን የመንገደኞች ባቡር ወደ ቤቴ ተመለስኩ። በዚያው ዕለት ምሽት በኮቤ ሆስፒታል በሕይወት ሳገኘው ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። ከዚያም በለሆሳስ ድምፅ “ፍቅሬ በሕይወት አለህ!” አልኩት።

ከወላጆቼ ጋር መኖር

ሳንዳ ወደሚገኘው የወላጆቼ ቤት ተመልሼ ልጆቹን መዋዕለ ሕፃናት አስገባኋቸው። አርባ ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኮቤ ለመመላለስ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ቲኬት ገዛሁና እኔና አማቴ በቀጣዩ ዓመት በየተራ ወደ ሆስፒታል ስንመላለስ ከረምን። ‘ሴኪቺ ዛሬ ነቅቶ አገኘው ይሆን? መጀመሪያ የሚነግረኝ ነገር ምን ይሆን? እኔስ ምን ልበለው?’ እያልኩ አስብ ነበር። በተለይ ደስተኛ የሚመስል ቤተሰብ ስመለከት ‘ሴኪቺ ደህና ቢሆን ኖሮ ልጆቻችን ደስ የሚል ጊዜ ያሳልፉ ነበር’ እያልኩ አስብና ዓይኖቼ ወዲያው እንባ ያቀርራሉ።

በእነዚያ የመጀመሪያ ዓመታት አንድ ሰው ጥቂት ወራት ነፍሱን ሳያውቅ ቆይቶ እንደነቃ ጋዜጣ ላይ ሳነብብ ሴኪቺም ሊነቃ ይችላል ብዬ አሰብሁ። ከዚያም ለአማቼ “በሰሜን ምሥራቅ ሆንሹ ወደሚገኘው ሆስፒታል ልወስደው እፈልጋለሁ” አልኩት። እርሱ ግን ምንም መፍትሔ የሌለው ነገር ስለሆነ ያለኝን ገንዘብ ለቤተሰቤ እንድጠቀምበት መከረኝ።

ኮቤ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በአንዱ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል የአንድ ወንድም ቤት ሆስፒታሉ አጠገብ ይገኝ ስለነበር ሴኪቺን ለመጠየቅ ከመሄዴ በፊት ወደ እነርሱ ጎራ እላለሁ። ሚስቱ በሳምንት አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ነበር። ሁለት ልጆቻቸው ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎቻቸው ላይ የተቀዱ የቴፕ ክሮች ሆስፒታሉ ክፍል ድረስ ያመጡልን ነበር። ከዚህ ቤተሰብ ከፍተኛ ማበረታቻና ማጽናኛ አግኝቻለሁ።

በተስፋ መጽናት

አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆስፒታል ድረስ መጥቶ ጎበኘንና ሮሜ 8:​18-25ን አነበበልኝ። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። . . . ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። . . . የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።”

ኢየሱስ ቃል ከገባው ከመጪው የምድራዊ ገነት ሕይወት ደስታ ጋር ሲወዳደር ዛሬ የሚደርስብን መከራ ጥቂት መሆኑን ስለ ክርስቲያናዊ ተስፋችን ካደረግነው ውይይት መረዳት ችያለሁ። (ሉቃስ 23:​43) ይህ ውይይት ዛሬ ያለውን እውነታ በተስፋ እንድጋፈጠውና በአዲሱ ዓለም እውን በሚሆኑት በረከቶች ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​17, 18፤ ራእይ 21:​3, 4

ሴኪቺ በሰኔ 1970 ወላጆቼና እኔ በምንኖርባት በሳንዳ ወደሚገኘው ሆስፒታል ተዛወረ። በቀጣዩ ጥር ወር ጠበቃችን ባለቤቴ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ለሥራ ብቁ እንዳልሆነ የሚገልጽ ውሳኔ የሰፈረበት ሰነድ አምጥቶ ሲሰጠኝ ወሽመጤ ቁርጥ አለ። እንባዬንም መቆጣጠር አልቻልኩም። አማቴ ብዙ ጊዜ “ሚቺኮ በእኔ ልጅ ምክንያት ስለተሸከምሽው መከራ በጣም አዝናለሁ” ትለኝ ነበር። እንዲሁም “በሴኪቺ ፋንታ እኔን ባደረገኝ ኖሮ” ትልና ተያይዘን እናለቅሳለን።

አባቴ የሙሉ ቀን ሥራ ተቀጥሬ እንድሠራ ይወተውተኝ ነበር። እኔ ግን ሴኪቺን መንከባከብ አለብኝ የሚል ቁርጥ ውሳኔ ነበረኝ። ሴኪቺ ነፍሱን የማያውቅ ቢመስልም ሙቀትና ቅዝቃዜ ሲሆን እንዲሁም የሚደረግለት እንክብካቤ ጥሩ ካልሆነ ይሰማዋል። አባቴ ሌላ ሰው እንዳገባ ይፈልግ ነበር። እኔ ግን ባሌ ገና በሕይወት ስለነበር ሌላ ሰው ማግባቴ ተገቢ እንደማይሆን ተገንዝቤአለሁ። (ሮሜ 7:​2) ከዚያ አባቴ ጠጥቶ ሲመጣ “እኔ ስሞት ሴኪቺን ይዤ ነው የምሄደው” ይል ነበር።

በ1971 ሳንዳ ውስጥ ጉባኤ ሲቋቋም በጣም ደስ አለኝ። ከዚያም ሐምሌ 28 ቀን 1973 ለይሖዋ ራሴን መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ይህ የሆነው በኦሳካ የኤክስፖ ማዕከል በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ነበር።

በ1973 ልጄ ኮሄይ ከባድ የኩላሊት በሽታ ይዞት አምስት ወር ሆስፒታል ተኛ። አባቴም በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ ነበር። በዚህ ምክንያት ጥር 1 ቀን 1974 አባቴን፣ ባሌንና ልጄን ወደ ሦስት የተለያዩ ሆስፒታሎች እየሄድኩ ስጠይቅ ዋልኩ። እሁድ እሁድ ከትልቁ ልጄ ከሪዩሱኬ ጋር ኮሄይን ለመጠየቅ ስንሄድ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባለውን መጽሐፍ አስጠናቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ሪዩሱኬና እኔ በኮቤ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝተን ደስ ብሎን ወደ ቤት እንመለሳለን።

ሴኪቺን በመንከባከብ ይረዱኝ ለነበሩት ሁሉ ሁልጊዜም አመስጋኝ ነኝ። ለእነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማካፈሉን ሥራዬ ብዬ ተያይዤው ነበር። አንዲት ታካሚዎችን የምትንከባከብ ሴት በእሳት አደጋ እህቷ ሞታባት በነበረበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ታላቅ የትንሣኤ ተስፋ ስነግራት ጥሩ ምላሽ አሳየች። (ኢዮብ 14:​13-15፤ ዮሐንስ 5:​28, 29) እዚያው ሆስፒታል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናት ጀመር። ከዚያም በ1978 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቀች።

ልጆቼ የደስታ ምንጭ ሆነውልኛል

ያለ ባለቤቴ እገዛ ብቻዬን ልጆቼን ማሳደግ ፈታኝ ነገር ሆኖብኝ ነበር። ይሁን እንጂ በእጅጉ ተክሼበታለሁ! ተገቢ ምግባር ማሳየትንና ለሌሎች ሰዎች ስሜት ማሰብን አስተምሬያቸዋለሁ። ሪዩሱኬ ገና የሦስት ዓመት ልጅ እያለ ጥፋት ሲያጠፋ “እማማ ይቅርታ” ይለኝ ነበር። ኮሄይ ግን ትንሽ ዓመፀኛ ነበር። አንዳንድ ጊዜም ልቀጣው ስሞክር ያኮርፍ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ነገር እንዲገዛለት ስለፈለገ ሱቁ ፊት ለፊት ወድቆ አልቅሷል። ይሁን እንጂ በፍቅርና በትዕግሥት ቀስ ብዬ ላስረዳው እሞክር ነበር። ከጊዜ በኋላ ታዛዥና ጥሩ ልጅ ሆኗል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የአምላክ ቃል መሆኑን እንዳምን አድርጎኛል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​15-17

ሪዩሱኬ ወደ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ ለመምህራኑ የካራቴ ትምህርት ለምን እንደማይማር አስረዳቸው። (ኢሳይያስ 2:​4) አንድ ቀን በርከት ያሉ አስተማሪዎች ተሰብስበው ያቀረቡለትን ጥያቄዎች መመለስ በመቻሉ ከትምህርት ቤት ሲመለስ በደስታ ፍልቅልቅ ብሎ ነበር።

በጉባኤ ውስጥ ያለው ጤናማ ወዳጅነት ልጆቼን በጣም ጠቅሟቸዋል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች ብዙውን ጊዜ እቤታቸው ምሳ ይጋብዟቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ በቤተሰብ ጥናታቸውም ላይ እንዲካፈሉ ይጠሯቸውና ሽርሽር ይዘዋቸው ይሄዱ ነበር። በተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች መሳተፍን ጨምሮ አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችሉ ሌሎች አጋጣሚዎችም ነበሩ። ሪዩሱኬ በ1979 ኮሄይ ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችን

አንድ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሲጎበኘን አቅኚ (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚጠሩበት ስያሜ ነው) መሆን እንደምፈልግ ነገርሁት። በወቅቱ ከነበረኝ ሁኔታ አንጻር ይህን እርምጃ መውሰድ ጥበብ ስላልነበረ ልጆቼ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥብቅ መሠረት ኖሯቸው እንዲያድጉ የማድረጉን አስፈላጊነት በደግነት አሳሰበኝ። “ዋናው ነገር የአቅኚነት መንፈስ መያዛችን ነው” አለኝ። በመሆኑም ረዳት አቅኚ በመሆን ልጆቼ እረፍት ሲሆኑ አብረን እናገለግል ነበር። ይህ አገልግሎት ሴኪቺን እየተንከባከብኩ ደስታ እንዳገኝና የአእምሮ ሰላሜን ጠብቄ እንድመላለስ ረድቶኛል።

በመጨረሻም በመስከረም 1979 ዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ቻልኩ። ከዚያ ሪዩሱኬም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በግንቦት 1984 አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ኮሄይ ደግሞ በመስከረም 1984 አቅኚ ሆነ። በዚህ መንገድ ሦስታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማራን። በርካታ ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ የመርዳት መብት ያገኘሁባቸውን 20 የአቅኚነት ዓመታት መለስ ብዬ ስመለከታቸው ይህ አገልግሎት የደረሱብኝን መከራዎች ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሰጠኝ ይሰማኛል።

ሪዩሱኬ ከካንሳይ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ አጠገብ በተገነባው የማስተማሪያ ሕንጻ ግንባታ በፈቃደኛ ሠራተኛነት ተሳትፏል። ከዚያም ለሰባት ዓመታት በሃዮጎ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ጠባቂ ሆኖ አገልግሏል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በኮቤ በአቅራቢያችን በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን እኔን በመንከባከብ ላይ ነው። ኮሄይ ከ1985 ጀምሮ ኢብና በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በፈቃደኛ ሠራተኛነት ያገለግላል።

ያገኘኋቸው ብዙ በረከቶች ኃይል ሰጥተውኛል

ለብዙ ዓመታት በሳምንት ሁለትና ሦስት ጊዜ ሴኪቺን ለማየትና ገላውን ለማጠብ ሆስፒታል ስመላለስ ኖሬያለሁ። ይህ እርሱን ለመንከባከብ ከተመደቡት ሠራተኞች በተጨማሪ የማደርገው ነገር ነበር። ሴኪቺ በሆስፒታል ለ27 ዓመታት ከቆየ በኋላ በመስከረም 1996 በአንድ ተንከባካቢ እርዳታ ቤታችን ለመኖር ተመልሷል። በአፍንጫው በኩል በገባለት ቱቦ አማካኝነት ፈሳሽ ምግብ ይወስዳል። ዓይኖቹ ተገልጠው ባያውቁም አንዳንድ ነገር ስንለው ቀስ ብሎ ይመልሳል። ሴኪቺ እንደዚያ ሆኖ ማየቴ አንጀቴን ይበላዋል። ይሁን እንጂ የወደፊቱን ታላቅ ተስፋ በማሰብ እጽናናለሁ።

ሴኪቺ ወደ ቤት ከመመለሱ ትንሽ ቀደም ብሎ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ሚስቱ እቤታችን እንዲያርፉ አድርጌ ስለነበር በትንሿ ቤታችን ውስጥ አምስት ሆነን ለአንድ ዓመት ያህል ቆይተናል። ከሴኪቺ ጋር እንደገና አብረን የምንኖርበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር ሆኖም ተመልሶ በመምጣቱ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ለብዙ ዓመታት ሴኪቺ ዓይኖቹን የሚገልጥባቸውን ቀናት ስናፍቅ ኖሬያለሁ። አሁን ግን ምኞቴ ይሖዋ የፈቀደው ነገር እንዲሆን ነው።

በሙሉ ልብ “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” ብዬ መናገር እችላለሁ። (ምሳሌ 10:​22) ሴኪቺ ጤናማ ሆኖ ያሳለፍነው የደስታ ሕይወት በጣም አጭር ቢሆንም ‘ታላቁን ፈጣሪያችንን ባሰቡት’ ሁለት ልጆቻችን እጅግ ተክሼአለሁ። ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ!​—⁠መክብብ 12:​1

ዛሬም ምኞቴ በአቅኚነት መቀጠል ማለትም ሌሎች “እውነተኛውን ሕይወት” እንዲያገኙ መርዳትና ሴኪቺን በፍቅር መንከባከብ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​19) በሕይወቴ የገጠመኝ ነገር መዝሙራዊው የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት እውነተኝነት አስተምሮኛል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።”​—⁠መዝሙር 55:22

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴና እኔ ከሪዩሱኬ ጋር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሴኪቺ አደጋው ከመድረሱ ከስድስት ወር በፊት ከሁለቱ ልጆቻችን ጋር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን ያሰቡትን ’ ሁለቱን ወንዶች ልጆቻችንን ሪዩሱኬንና ኮሄይን (ከላይ ) በማግኘት ተባርከናል