በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አካባቢያዊ ሁኔታ በጤናህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

አካባቢያዊ ሁኔታ በጤናህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

አካባቢያዊ ሁኔታ በጤናህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ዓለም የተፈጥሮ ሀብት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዎልተር ሪድ በቅርቡ ከተመድ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰው ልጅ በዓለም አቀፍ አካባቢያዊ ሥርዓቶች ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በአሁኑ ጊዜ “እነዚህን ዑደቶች በከፍተኛ ሁኔታ ወደሚያቃውስበት” ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ተናግረዋል። ዶክተር ሪድ እንዳሉት ይህ በአካባቢያዊ ዑደቶች ላይ የሚደርሰው ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና ላይ አስጊ ሁኔታዎች ይፈጥራል። በተባበሩት መንግሥታት እየታተመ የሚወጣው አወር ፕላኔት የተሰኘው መጽሔት ዎርልድ ሪሶርስስ 1998-99 የተባለውን መጽሐፍ በተመለከተ ሂስ በሰጠበት አንድ ጽሑፍ ላይ በሰዎች ጤና ላይ ከተጋረጡት አስጊ ሁኔታዎች አንዳንዶቹን ዘርዝሯል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:-

□ በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ የሚከሰተው የአየር ብክለት በየዓመቱ ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጉ ሕፃናትን ለሕልፈተ ሕይወት ከሚዳርጉት የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች ጋር ዝምድና አለው።

□ የንጹሕ ውኃ እጥረትና የንጽሕና አጠባበቅ ዘዴ ጉድለት በየዓመቱ የሦስት ሚልዮን ሕፃናትን ሕይወት ለሚቀጥፉት የተቅማጥ በሽታዎች መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ከረጅም ጊዜ በፊት ከላቲን አሜሪካ ጠፍቶ የነበረው ኮሌራ በዚያው አህጉር ዳግም አንሰራርቶ በ1997 ብቻ 11, 000 ሰዎች ገድሏል።

በየዕለቱ በዓለማችን ድሃ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከ30, 000 የሚበልጡ ሕፃናት ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር ዝምድና ባላቸው በሽታዎች ሳቢያ እንደሚሞቱ ይነገራል። እስቲ አስበው፣ በዓመት ውስጥ በእያንዳንዷ ዕለት 30, 000 ሰዎች ይሞታሉ፤ እነዚህ ሰዎች ወደ 75 የሚጠጉ ግዙፍ አውሮፕላኖች መቀመጫዎችን በሙሉ ሊሞሉ የሚችሉ ናቸው!

ይሁን እንጂ በጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካባቢያዊ ሁኔታዎች በታዳጊ አገሮች ውስጥ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። አወር ፕላኔት እንደገለጸው “በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ከ100 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች አሁንም ድረስ አደገኛ ለሆነ አየር የተጋለጡ” ሲሆን ይህ አየር በአስም በሽታ ለሚያዙ ሰዎች ቁጥር ማሻቀብ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ዓለም አቀፋዊ ጉዞና የንግድ ልውውጥ ባደጉት አገሮች ውስጥ ወደ 30 የሚጠጉ አዳዲስ ተዛማች በሽታዎች እንዲከሰቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም ቀደም ሲል በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ በሽታዎች “በከፍተኛ መጠን አገርሽተዋል” ሲል ሪፖርት አድርጓል።

የሚያሳዝነው ነገር ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር ዝምድና ካላቸው ከእነዚህ በሽታዎች መካከል አብዛኞቹ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ያሉት በአሁኑ ጊዜ ባለው ቴክኖሎጂና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በዝቅተኛ ዋጋ ሊወገዱ የሚችሉ ሆነው ሳለ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል ለሁሉም ሰው ንጹሕ ውኃ በማቅረብና ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ሁኔታ በመፍጠር በጤና ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ማድረግ ይቻላል። እዚህ ግብ ዳር ለመድረስ ምን ያህል ገንዘብ ይጠይቅ ይሆን? የተመድ ራዲዮ የተባበሩት መንግሥታት የ1998 የሰብዓዊ ዕድገት ሪፖርትን ጠቅሶ እንደዘገበው ለእያንዳንዱ ሰው ንጹሕ ውኃ ለማቅረብና ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ዘዴ ለመፍጠር 11 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ አውሮፓውያን በአንድ ዓመት ውስጥ ለአይስ ክሬም ከሚያወጡት ገንዘብ ያነሰ ነው!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፎቶ:- Casas, Godo-Foto