በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“አሁን አገልግሎት በጣም እወዳለሁ!”

“አሁን አገልግሎት በጣም እወዳለሁ!”

ያደግኩት በኒው ዚላንድ፣ ሳውዝ አይላንድ በምትገኘው በባልክሉታ ከተማ ነው። ልጅ እያለሁ ይሖዋንም ሆነ እውነትን እወድ ነበር። ስብሰባ መሄድ ሥራ ሆኖብኝ አያውቅም፤ እንዲያውም ጉባኤ ውስጥ ስሆን ደስ ይለኝ ነበር። በተፈጥሮዬ ተግባቢ ሰው ባልሆንም በየሳምንቱ አገልግሎት መውጣት የምወደው ነገር ነበር። አብረውኝ ለሚማሩት ልጆችም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ከመስበክ ወደኋላ ብዬ አላውቅም። የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ እኮራ ነበር፤ አሥራ አንድ ዓመት ሲሆነኝ ራሴን ለአምላክ ወሰንኩ።

ደስታዬ ጠፋ

የሚያሳዝነው ግን 13 ዓመት ገደማ ሲሆነኝ፣ ከይሖዋ ጋር የነበረኝ የጠበቀ ወዳጅነት እየቀዘቀዘ መጣ። አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ገደብ የለሽ ነፃነት ያላቸው ይመስል ነበር፤ እኔም የቀረብኝ ነገር እንዳለ ማሰብ ጀመርኩ። የወላጆቼ መመሪያዎች እና ክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ነፃነቴን እንደገደቡብኝ ተሰማኝ፤ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ሸክም ሆኑብኝ። ይሖዋ መኖሩን ተጠራጥሬ ባላውቅም በመንፈሳዊ ባዶ እንደሆንኩ ይሰማኝ ጀመር።

ያም ቢሆን የቀዘቀዘች ክርስቲያን ላለመባል ስል ለይስሙላ ያህል አገልግሎት እወጣ ነበር። አገልግሎት የምወጣው ሳልዘጋጅ በመሆኑ ከሰዎች ጋር ውይይት መጀመር እንዲሁም ውይይቱን ማስቀጠል ይከብደኝ ነበር። በመሆኑም አገልግሎቴ ፍሬያማና አስደሳች አልነበረም፤ ይህም አገልግሎቱን ይበልጥ እንድጠላው አደረገኝ። ‘ሰው እንዴት ከሳምንት ሳምንት፣ ከወር ወር መስበክ ይችላል?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ነፃነት ለማግኘት ቆርጬ ተነሳሁ። ስለዚህ ጓዜን ጠቀለልኩና ቤተሰቦቼን ትቼ ወደ አውስትራሊያ ሄድኩ። ወላጆቼ ከቤት መውጣቴ በጣም አሳዝኗቸው ነበር። ሁኔታው ቢያስጨንቃቸውም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈሌን እንደምቀጥል አስበው ነበር።

አውስትራሊያ ውስጥ ስኖር መንፈሳዊነቴ ይበልጥ እያሽቆለቆለ ሄደ። ከስብሰባዎች መቅረት ጀመርኩ። ልክ እንደ እኔው ዛሬ ስብሰባ ነገ ደግሞ ጭፈራ ቤት ከሚያመሹ ወጣቶች ጋር መቀራረብ ጀመርኩ፤ ወደ ምሽት ክለቦች እየሄድን ስንጠጣና ስንጨፍር እናመሽ ነበር። መለስ ብዬ ሳስበው አንድ እግሬ እውነት ውስጥ፣ አንድ እግሬ ደግሞ ዓለም ውስጥ እንደነበር ይሰማኛል፤ ግን በሁለቱም ደስተኛ አልነበርኩም።

ባልጠበቅኩት መንገድ ጠቃሚ ትምህርት አገኘሁ

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ከአንዲት እህት ጋር የተወሰነ ጊዜ አሳለፍኩ፤ ይህች እህት በወቅቱ ባይታወቃትም ስለ ሕይወቴ አቅጣጫ ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገችኝ። በወቅቱ አምስት ያላገባን እህቶች አብረን እንኖር ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ባለቤቱን ታማራን ለአንድ ሳምንት ቤታችን እንዲያርፉ ጋበዝናቸው። ባለቤቷ የጉባኤ ሥራዎችን ሲያከናውን ታማራ ከእኛ ጋር ጊዜ ታሳልፍ፣ ትጫወትና ትስቅ ነበር። ይህ በጣም አስደሰተኝ። ታማራ ምክንያታዊ እና በቀላሉ የምትቀረብ ናት። ይህች እህት በጣም መንፈሳዊ ሆና እያለ ያን ያህል ዘና ልታደርገን መቻሏ በእጅጉ አስገረመኝ።

ታማራ ቀናተኛ ክርስቲያን እንደሆነች በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። ለእውነትና ለአገልግሎት ያላት ፍቅር ወደ ሌሎች የሚጋባ ነው። እኔ ለይሖዋ የማቀርበው አገልግሎት የይስሙላ ቢሆንም ደስተኛ አልነበርኩም፤ እሷ ግን ለይሖዋ ምርጧን እየሰጠች በጣም ደስተኛ ናት። አዎንታዊ አመለካከትና እውነተኛ ደስታ እንዳላት ማየቴ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። የታማራ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝን አንድ መሠረታዊ እውነታ እንዳስተውል አደረገኝ፦ ይሖዋ ሁላችንም “በደስታ” እና “በእልልታ” እንድናገለግለው ይፈልጋል።—መዝ. 100:2

ለአገልግሎት ያለኝን ፍቅር እንደገና አቀጣጠልኩ

እንደ ታማራ ደስተኛ መሆን ፈለግኩ፤ እንዲህ ያለ ደስታ ለማግኘት ግን በሕይወቴ ውስጥ ትላልቅ ለውጦች ማድረግ ነበረብኝ። ለውጥ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድብኝም ደረጃ በደረጃ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አደረግኩ። አገልግሎት ከመውጣቴ በፊት መዘጋጀት ጀመርኩ፤ እንዲሁም አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆኜ አገለግል ነበር። ይህም ፍርሃቴ እንዲቀንስና ይበልጥ በድፍረት እንድሰብክ ረድቶኛል። አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ በተጠቀምኩ መጠን እውነተኛ እርካታ ማግኘት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በየወሩ ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል ቻልኩ።

ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸውና በይሖዋ አገልግሎት የሚደሰቱ በተለያየ ዕድሜ የሚገኙ ወዳጆችን አፈራሁ። የእነሱ መልካም ምሳሌነት ቅድሚያ የምሰጣቸውን ነገሮች እንድገመግም እንዲሁም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዳዳብር ረዳኝ። አገልግሎት ይበልጥ ያስደስተኝ ጀመር። ውሎ አድሮም የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ደስተኛ ሆኜ መመላለስ ቻልኩ፤ በጉባኤው ውስጥ ቦታዬን እንዳገኘሁ ተሰማኝ።

የዕድሜ ልክ የአገልግሎት ጓደኛ አገኘሁ

ከአንድ ዓመት በኋላ አሌክስ ከተባለ ደግና ቅን የሆነ ሰው ጋር ተዋወቅኩ። አሌክስ ይሖዋን እና አገልግሎቱን በጣም ይወዳል። በወቅቱ የጉባኤ አገልጋይ የነበረ ሲሆን ለስድስት ዓመት በአቅኚነት ሲያገለግል ቆይቷል። በተጨማሪም አሌክስ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለመርዳት ሲል ወደ ማላዊ ሄዶ አገልግሏል። በዚያ የተዋወቃቸው ሚስዮናውያን በሕይወቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደሩበት ከመሆኑም በላይ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ መስጠቱን እንዲቀጥል አበረታተውታል።

በ2003 ከአሌክስ ጋር ተጋባን፤ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አብረን እየተካፈልን ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ግሩም ትምህርቶችን አግኝተናል። ይሖዋም ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች ባርኮናል።

ተጨማሪ በረከት አገኘን

በግሌኖ፣ ቲሞር ሌስተ ምሥራቹን ስንሰብክ

በ2009 ከኢንዶኔዥያ ደሴቶች አንዷ በሆነች ቲሞር ሌስተ የምትባል ትንሽ አገር ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። ግብዣው ሲቀርብልን ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ተሰማን፤ በጣም የተገረምንና የተደሰትን ቢሆንም ስጋትም ነበረን። ከአምስት ወራት በኋላ የአገሪቱ ዋና ከተማ ወደሆነችው ዲሊ ደረስን።

ወደዚያ ስንሄድ በአኗኗራችን ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ አስፈልጎናል። ከአዲስ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ምግብና የኑሮ ሁኔታ ጋር መላመድ ነበረብን። ብዙ ጊዜ አገልግሎት ስንወጣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ፣ ያልተማሩ እንዲሁም ጭቆና የደረሰባቸው ሰዎች እናገኝ ነበር። ጦርነትና ዓመፅ ያስከተለው አካላዊና ስሜታዊ ጠባሳ በብዙዎች ላይ ይታይ ነበር። *

አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነበር! ለምሳሌ በአንድ ወቅት ማሪያ * የተባለች በሐዘን የተዋጠች የ13 ዓመት ልጅ አግኝቼ ነበር። እናቷ የሞተችው ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ነው፤ አባቷን ደግሞ የምታገኘው ከስንት አንዴ ነበር። በእሷ ዕድሜ እንዳሉ ብዙ ልጆች ሁሉ ማሪያም ሕይወቷን እንዴት መምራት እንዳለባት ግራ ተጋብታ ነበር። በአንድ ወቅት ማሪያ ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች ስሜቷን አውጥታ ነገረችኝ። ሆኖም ቋንቋውን በደንብ ስለማልችል ማሪያ ምን እያለችኝ እንደነበር አልገባኝም። ማሪያን እንዳበረታታት እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ከዚያም የሚያጽናኑ ጥቅሶችን አውጥቼ አነበብኩላት። ማሪያ እውነትን በማወቋ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት አመለካከቷ፣ አለባበሷ እንዲሁም አጠቃላይ ሕይወቷ ሲለወጥ ተመለከትኩ። ሕይወቷን ወስና ተጠመቀች፤ በአሁኑ ወቅት እሷም ሌሎች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች። አሁን ማሪያ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ ያላት ሲሆን እንደምትወደድም ይሰማታል።

ይሖዋ በቲሞር ሌስተ የሚከናወነውን ሥራ እየባረከው ነው። አብዛኞቹ አስፋፊዎች የተጠመቁት ባለፈው አስር ዓመት ውስጥ ቢሆንም ብዙዎቹ አቅኚዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮች ወይም ሽማግሌዎች ሆነው እያገለገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን በአካባቢው በሚነገሩ ቋንቋዎች መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀቱ ሥራ ይካፈላሉ። በስብሰባዎች ላይ ሲዘምሩ መስማት፣ በፊታቸው ላይ የሚነበበውን ፈገግታ ማየት እንዲሁም በመንፈሳዊ የሚያደርጉትን እድገት መመልከት በጣም ያስደስተኝ ነበር።

ለየትኛውም ጉባኤ ባልተመደበ ክልል የመታሰቢያውን በዓል መጋበዣ ለማሰራጨት ከአሌክስ ጋር ስንሄድ

በሕይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ

በቲሞር ሌስተ የነበረን ሕይወት በአውስትራሊያ ከነበረን በእጅጉ የተለየ ነው፤ ያም ቢሆን በቲሞር ሌስተ በጣም አስደሳች ሕይወት አሳልፈናል። አንዳንድ ጊዜ በሕዝብ በተጨናነቁ መጓጓዣዎች እንጠቀም የነበረ ሲሆን መኪናው ውስጥ ከሰዎች በተጨማሪ የደረቁ ዓሦችና አትክልቶች ይጫኑ ነበር። በጣም በሚወብቅ ቤት ውስጥ ጥናት የምንመራበት ጊዜም ነበር፤ መሬቱ አፈር ነው፤ እግራችን ሥር ደግሞ ዶሮዎች ይለቃቅማሉ። እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ብዙውን ጊዜ ‘አቤት ደስ ሲል!’ ብዬ አስብ ነበር።

ወደ ክልላችን ስንሄድ

ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ወላጆቼ እኔን ስለ ይሖዋ ለማስተማር የሚችሉትን ሁሉ ስላደረጉ እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለሁ በመንፈሳዊ ተዳክሜ በነበረበት ጊዜም እንኳ ስለደገፉኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ። የምሳሌ 22:6 እውነተኝነት በእኔ ሕይወት ታይቷል። እናቴና አባቴ በእኔና በአሌክስ ይኮራሉ፤ ይሖዋ በዚህ መንገድ ሊጠቀምብን በመቻሉ በጣም ደስተኞች ናቸው። ከ2016 ወዲህ በአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ባሉ ክልሎች ውስጥ በወረዳ ሥራ እየተካፈልን ነው።

የካሌብና የሶፊያን ቪዲዮ ለአንዳንድ የቲሞር ሌስተ ልጆች ሳሳይ

በአንድ ወቅት የስብከቱን ሥራ እንደ ሸክም እቆጥረው እንደነበር አሁን ሳስበው ለማመን ይከብደኛል። አሁን አገልግሎት በጣም እወዳለሁ! በሕይወት ውስጥ የተለያየ ውጣ ውረድ ሊያጋጥም ቢችልም እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው አምላክን በሙሉ ልብ በማገልገል ብቻ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። በእርግጥም ከአሌክስ ጋር ሆኜ ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸው 18 ዓመታት በሕይወቴ ውስጥ በጣም የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ናቸው። መዝሙራዊው ዳዊት ለይሖዋ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት እውነተኝነት በሕይወቴ ተመልክቻለሁ፦ “አንተን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ . . . ሐሴት ያደርጋሉ፤ ምንጊዜም በደስታ እልል ይላሉ። . . . ስምህን የሚወዱም በአንተ ሐሴት ያደርጋሉ።”—መዝ. 5:11

እነዚህን ትሑት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት በጣም ያስደስታል!

^ አን.21 ቲሞር ሌስተ ከ1975 አንስቶ ለ20 ዓመት ያህል ፖለቲካዊ ነፃነት ለማግኘት በሚደረግ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።

^ አን.22 ስሟ ተቀይሯል።