ሐምሌ 15, 2025
ዓለም አቀፋዊ ዜና
በራማፖ ሥራው ሲቀጥል ቦታው መልክ እየያዘ መጥቷል። የውኃ ማቆሪያ ኩሬ (መሃል በስተ ግራ) ጎርፍ ተከላካይ ሲሆን ከግንባታ ቦታው ወደ ውጭ የሚፈስሰው ውኃ ንጹሕ እንዲሆን ያደርጋል
የዋናው መሥሪያ ቤት ፕሮጀክት በራማፖ
የራማፖ ግንባታ ሪፖርት 1
መሬቱን የማመቻቸት ሥራ እየተካሄደ ነው
ኅዳር 2024 ባለሥልጣናት የራማፖን የግንባታ ንድፍ ማጽደቃቸውን ተከትሎ ቦታው ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ሥራዎች (መሬቱን የማመቻቸት ሥራ) ተጀምረዋል። ይህ ሥራ 18 ወራት ገደማ እንደሚወስድ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ 133,800 ሜትር ኩብ የሚሆን አፈርና ድንጋይ ተቆፍሮ ወጥቷል፤ ይህም የኦሎምፒክ መጠን ያላቸው 54 ገደማ የመዋኛ ገንዳዎችን ሊሞላ የሚችል መጠን ነው። ተቆፍሮ የወጣው አፈርና ድንጋይ በግንባታው ቦታ በሌላ አካባቢ ያለውን መሬት ለመደልደል ጥቅም ላይ ይውላል። ከዚህ ሥራ ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ፣ የቧንቧና የሌሎች አገልግሎቶች መስመሮችን መሬት ሥር የመቅበር ሥራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው።
በስተ ግራ፦ ትሬሲ ፓነል እና ባለቤቱ ቪክቶሪያ። በስተ ቀኝ፦ ቪክቶሪያ በአፈር መድፊያ መኪናዋ አጠገብ ሆና
በግንባታ ሥራ ልምድ ያላቸው ብዙ ወንድሞችና እህቶች ፕሮጀክቱ ላይ ለማገዝ ራሳቸውን አቅርበዋል። ለምሳሌ ትሬሲ እና ቪክቶሪያ የተባሉት ባልና ሚስት የመጡት ከኦክላሆማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። ትሬሲ በራማፖው ፕሮጀክት ላይ መሬት ቁፋሮ ላይ ይሠራል። ቪክቶሪያ ደግሞ አፈር በሚያጓጉዝና በሚደፋ ከባድ መኪና ላይ ለመሥራት አስፈላጊው ሥልጠና ተሰጥቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለ ከባድ መኪና ላይ መሥራት እችላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። እኛ ፈቃደኝነቱ ካለንና በይሖዋ እርዳታ ከተማመንን እሱ በእኛ ተጠቅሞ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን እንደሚችል ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖልኛል።”
ካርል ናይት እና ባለቤቱ ዛይድ
ካርል እና ዛይድ የተባሉ ሌላ ባልና ሚስት ብሪታንያ ውስጥ በተካሄደው የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ ለተወሰኑ ዓመታት አግዘዋል። የካርል ሥራ መሬቱን ለግንባታ ከማመቻቸት ጋር የተያያዘ ሲሆን ዛይድ ደግሞ ዶዘር እና ሌሎች ከባድ ማሽኖች ላይ ትሠራለች። ባልና ሚስቱ ከሥራቸው የሚወዱት አንዱ ነገር ፕሮጀክቱ ላይ ለማገዝ ራሳቸውን ካቀረቡ ብዙ ወጣት ወንድሞችና እህቶች ጋር መሥራት ነው። ዛይድ የእነዚህን ወጣቶች ወላጆች አስመልክታ ስትናገር “ልክ እንደ ሐና ልጃቸውን ‘ለይሖዋ አውሰዋለሁ’ ማለት በመቻላቸው ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስቡት” ብላለች። (1 ሳሙኤል 1:28 የግርጌ ማስታወሻ) ከ18 እስከ 25 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ150 በላይ ወንድሞችና እህቶች በራማፖ ግንባታ ላይ እያገዙ እንዳለ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነገር ነው።
ሥራው ወደፊት እየገሰገሰ ሲሄድ ይሖዋ በዚህ አስደናቂ ፕሮጀክት ላይ ለማገዝ ራሳቸውን ያቀረቡትን ሁሉ መባረኩን እንዲቀጥል ጸሎታችን ነው።—መዝሙር 110:3