ካማል ቨርዲ | የሕይወት ታሪክ
“ከልጅነቴ ጀምሮ የፍትሕ ጉዳይ ያንገበግበኛል”
ነሐሴ 1973 እኔና ሁለት እህቶቼ በትዊከንሃም፣ እንግሊዝ በተካሄደ “መለኮታዊ ድል” የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኝተን ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ ከ1926 ጀምሮ ሕንድ ውስጥ በሚስዮናዊነት ካገለገለው ከወንድም ኤድዊን ስኪነር ጋር ተዋወቅን። ፑንጃብኛ እንደምንችል ሲያውቅ “ታዲያ እዚህ ምን ትሠራላችሁ? ለምን ወደ ሕንድ አትመጡም?” አለን። ስለዚህ ሄድን። በፑንጃብኛ መስክ ማገልገል የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነበር። በቅድሚያ ግን ይህን ውይይት ከማድረጋችን በፊት ያለውን ታሪክ ልንገራችሁ።
የተወለድኩት ሚያዝያ 1951 በናይሮቢ፣ ኬንያ ነው። ወላጆቼ ሕንዳውያን ሲሆኑ የሲክ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። አባቴ ወንድሙ ከሞተ በኋላ የወንድሙን ሚስት ስላገባ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። የመጀመሪያ ሚስቱ የሆነችው እናቴ ይህን ከመቀበል ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራትም። እናቴና እንጀራ እናቴ በአብዛኛው የሚወልዱት ተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነበር። ስለዚህ ከእናቴም ሆነ ከእንጀራ እናቴ ከተወለዱ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ከአጎቴ ልጅ ጋር አብረን ነው ያደግነው። በአጠቃላይ ሰባት ልጆች ነበርን። በ1964 ልክ 13 ዓመት ሲሆነኝ አባቴ ሞተ።
ፍትሕን ፍለጋ
ልጅ ሳለሁ በዙሪያዬ ብዙ አለመግባባትና መድልዎ አይ ነበር። በኋላ እንደተረዳሁት የቤተሰባችን ሕይወት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ከሊያና ከራሔል ሕይወት ጋር ይመሳሰላል። ኬንያዊ የሆኑት ሠራተኞቻችን ብዙ በደል ይደርስባቸው ነበር፤ እነሱን የበታቻችን አድርገን እንድናያቸው ይነገረናል። አባቴ እንድንቀራረብ የሚፈልገው አውሮፓዊ ከሆኑ ጎረቤቶቻችን ጋር ነው፤ ከእነሱ ብዙ ነገር መማር እንደምንችል ይሰማዋል። ከአፍሪካውያን ግን ምንም የምንማረው ነገር እንደሌለ ስለሚሰማው እንድንርቃቸው ይነግረናል። ፓኪስታናውያንም እንደ ጠላት ተደርገው ስለሚታዩ ከእነሱም ጋር እንድንቀራረብ አይፈቀድልንም ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ የፍትሕ ጉዳይ ያንገበግበኛል፤ የአባቴ አመለካከት ልክ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር።
የሲክ ሃይማኖት የተቋቋመው በ15ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ናናክ በተባለ የሂንዱ ሃይማኖታዊ መምህር ነው። እውነተኛው አምላክ አንድ እንደሆነ የሚገልጸውን ጨምሮ የናናክን ትምህርቶች ተቀብዬ ነበር። ሆኖም በዚያ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ያለውን የፍትሕ መጓደል ሳይ ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር።
ከሃይማኖቱ ጋር በተያያዘ የሚያሳስበኝ ሌላም ነገር ነበር። የሲክ ሃይማኖት ጥቂት መቶ ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ፦ ‘ከዚያ በፊትስ? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው የመጀመሪያው አምልኮ የቱ ነው? መምህሮቹ ራሳቸው መመለክ ያለበት፣ እውነተኛው አንድ አምላክ ብቻ እንደሆነ እያስተማሩ ቤተሰቤን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች ለመምህሮቹ ምስሎች የሚሰግዱት ለምንድን ነው?’
በ1965 የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰባችን ወደ ሕንድ ተዛወረ። ብዙ ገቢ ስላልነበረን ኑሮ በጣም ከብዶን ነበር። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ወደ እንግሊዝ ተዛወርን። በአንድ ጊዜ ሁለት ሁለት እየሆንን ተጉዘን ሌስተር በሚባል ቦታ መኖር ጀመርን።
በ16 ዓመቴ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን እየሠራሁ ማታ ማታ በመማር፣ የተቋረጠውን ትምህርቴን ቀጠልኩ። ግን በምሠራበት ቦታ ሠራተኞች መድልዎ እንደሚደርስባቸው አስተዋልኩ። ለምሳሌ እንግሊዛውያን ሠራተኞች የሚከፈላቸው ከስደተኞች የበለጠ ነበር። ለፍትሕ ካለኝ ተቆርቋሪነት የተነሳ ገና በወጣትነቴ በሠራተኞች ማኅበር ውስጥ የመብት ተሟጋች ሆንኩ። ስደተኛ ሴቶች የሥራ አድማ በማድረግ ከእንግሊዛውያኑ እኩል ደሞዝ እንዲከፈላቸው እንዲጠይቁ አስተባበርኩ። ምኞቴ ፍትሕ ሰፍኖ ማየት ነበር።
መልሱን አገኘሁ
ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁት በ1968፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ወንዶች በሬን ባንኳኩበት ጊዜ ነው። የአምላክ መንግሥት ሁሉንም ሰው እኩል እንደሚያደርግ የሚገልጸው ተስፋ ወዲያውኑ ትኩረቴን ሳበው። ከሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ከባለቤቱ ጋር ተመልሶ መጣ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ጃስዊንደር የተባለችው እህቴና ከእንጀራ እናቴ የምትወለደው ቻኒ የተባለችው እህቴም ማጥናት ጀመሩ። ስድስት ምዕራፎችን ብቻ ካጠናን በኋላ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእሱ ቃል እንደሆነና ለሁሉም እውነተኛ ፍትሕ ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንን።
ሆኖም ከቤተሰብ ከባድ ተቃውሞ ገጠመን። አባቴ ከሞተ በኋላ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ከእንጀራ እናቴ የሚወለደው ወንድሜ ነበር። ወንድሜ በእንጀራ እናቴ ቆስቋሽነት ከባድ ተቃውሞ ያደርስብን ጀመር። ታናናሽ እህቶቼን ጃስዊንደርን እና ቻኒን ውስጡ ብረት ባለው ጫማ በእርግጫ ይመታቸው ነበር። እኔ 18 ዓመት ስለሞላኝ ከሕግ አንጻር መብት እንዳለኝ ገብቶታል፤ እህቶቼ ግን ገና ዕድሜያቸው ስላልደረሰ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። በአንድ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ እሳት ከለኮሰበት በኋላ ወደ ፊታቸው አስጠግቶ “እስቲ ይሖዋ የምትሉት አምላካችሁ እሳቱን ያጥፋላችሁ!” አላቸው። በወቅቱ በተወሰኑ ስብሰባዎች ላይ በድብቅ የተገኘን ቢሆንም ብቸኛ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በነፃነት ማምለክ ፈልገን ነበር። ሆኖም በዚያ ሁኔታ ሥር ይህ ፈጽሞ እንደማይቻል ተሰማን። ስለዚህ ከቤት ጠፍተን የተሻለ ደህንነት ወደምናገኝበት ቦታ ለመሄድ ማቀድ ጀመርን። እንዴት?
ለምሳና ለአውቶቡስ መሳፈሪያ የሚሰጠንን ገንዘብ እንዲሁም ለእንጀራ እናቴ እንዳስረክብ ከሚጠበቅብኝ ከደሞዜ ላይ የተወሰነውን በሚስጥር ማጠራቀም ጀመርን። ሦስት ሻንጣዎችን ገዝተን ሌላ ቦታ ካስቀመጥናቸው በኋላ ቀስ በቀስ በልብስ ሞላናቸው። ግንቦት 1972 ጃስዊንደር 18 ዓመት ሊሞላት ጥቂት ሲቀራትና ያጠራቀምነው ገንዘብ 100 ፓውንድ (260 የአሜሪካ ዶላር) ሲሞላልን ባቡር ተሳፍረን በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ ወደምትገኝ ፔንዛንስ የተባለች ቦታ ሄድን። ፔንዛንስ ስንደርስ የሕዝብ ስልክ ተጠቅመን እዚያ ላሉት የይሖዋ ምሥክሮች ደወልን። ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። ለቤት ኪራይና ለኑሮ የሚያስፈልገንን ገቢ ለማግኘት ስንል የዓሣ ሆድ ዕቃ ማውጣትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እንሠራ ነበር።
ሃሪና ቤቲ ብሪግስ ከተባሉ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ቀጠልን። መስከረም 1972 ቤተሰቦቻችን ሳያውቁ ተጠመቅን፤ የተጠመቅነው በትሩሮ የስብሰባ አዳራሽ መድረክ ሥር ባለች ትንሽዬ የጥምቀት ገንዳ ውስጥ ነው። ቻኒ በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች፤ እኔና ጃስዊንደር ደግሞ በገንዘብ እንደግፋት ነበር።
ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል
ሃሪ እና ቤቲ በሰማንያዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ቢሆኑም በእንግሊዝ ደቡብ ምዕራብ የባሕር ዳርቻ ወደሚገኙ አይል ኦቭ ሲሊ በመባል የሚታወቁ ደሴቶች አዘውትረው በመሄድ ይሰብኩ ነበር። የእነሱ ምሳሌነት እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ አነሳሳን። በመሆኑም በ1973 ከወንድም ስኪነር ጋር በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ውይይት ካደረግን በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብን ወሰንን።
ጥር 1974 ወደ ኒው ዴልሂ፣ ሕንድ ለመሄድ የአንድ ጉዞ ቲኬት ቆረጥን። እዚያ ስንደርስ ወንድም ዲክ ካተሪል በሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ በእንግድነት ተቀበለን። ቻኒ በዘወትር አቅኚነት ማገልገሏን ቀጠለች፤ እኔና ጃስዊንደር ደግሞ በአገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርን።
በኋላ ላይ በሰሜን ምዕራብ ሕንድ በሚገኘው በፑንጃብ ግዛት እንድናገለግል ተመደብን፤ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቻንዲጋር በተባለች ከተማ በሚገኝ የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ከቆየን በኋላ የራሳችንን ቤት ተከራየን። መስከረም 1974 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ፤ ከዚያም በ1975 ልዩ አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። በስብከቱ ሥራ ስካፈል፣ ተጨማሪ ሰዎች ስለ ይሖዋ ፍቅርና ፍትሕ መማር እንዲችሉ በፑንጃብኛ የተዘጋጀ ጽሑፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስተዋልኩ። በ1976 ሦስታችንም በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ጽሑፎችን በፑንጃብኛ በመተርጎሙ ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። ታይፕራይተር ወይም ኮምፒውተር ስላልነበረ ሥራው በጣም አድካሚ ነበር። የተረጎምነውን በእጃችን መጻፍና እያንዳንዱን ነገር እያነበብን ስህተት አለመኖሩን ማረጋገጥ ነበረብን። ከዚያ በአካባቢው ወዳለ የድሮ ማተሚያ ማሽኖች ያሉት ማተሚያ ቤት እየሄድን እያንዳንዱን ፊደል ማሽኑ ውስጥ በማስገባት እናሳትም ነበር።
በፑንጃብ፣ ሕንድ ውስጥ በቻንዲጋር የሚገኘው ጉባኤያችን
የጤና ችግር ቢያጋጥመኝም ደስተኛ ሆኜ መቀጠል
ብዙም ሳይቆይ ሕይወታችን ተቀየረ። ጃስዊንደር ትዳር መሥርታ ወደ ካናዳ ሄደች። ቻኒ ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ ለተወሰነ ጊዜ መጥቶ የነበረን ጀርመናዊ ወንድም አግብታ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደች። እኔ ደግሞ በጠና ታምሜ ጥቅምት 1976 ወደ እንግሊዝ ተመለስኩ። ለእውነት በጎ አመለካከት የነበራቸው ወላጅ እናቴና ወንድሜ በደግነት ተቀብለውኝ በሌስተር አብሬያቸው መኖር ጀመርኩ። ኢቫንስ ሲንድሮም የተባለ ያልተለመደ የጤና ችግር እንዳለብኝ በምርመራ ታወቀ፤ ይህ የጤና ችግር የሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት የደም ሴሎችን እንዲያጠቁ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በቀዶ ሕክምና ጣፊያዬ የወጣ ከመሆኑም ሌላ የተለያዩ ሕክምናዎችን መውሰድ ነበረብኝ። አቅኚነቴን ማቆም ግድ ሆነብኝ።
ወደ ይሖዋ ከልቤ በመጸለይ የጤናዬ ሁኔታ ከተሻሻለ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንደምመለስ እነግረው ነበር። ደግሞም ያደረግኩት ይህንኑ ነው! በሽታው አልፎ አልፎ የሚባባስበት ጊዜ ቢኖርም በ1978 ዎልቨርሃምፕተን ወደተባለ ፑንጃብኛ በስፋት የሚነገርበት አካባቢ ተዛውሬ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። የስብሰባ መጋበዣዎችን በእጃችን እንጽፍና በአቅራቢያችን ወዳሉ ማተሚያ ቤቶች ወስደን እናባዛቸው ነበር። ከዚያም የፑንጃብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች በማሰራጨት የሕዝብ ንግግር ላይ እንዲገኙ እንጋብዛቸዋለን። በአሁኑ ጊዜ በብሪታንያ በፑንጃብኛ የሚካሄዱ አምስት ጉባኤዎችና ሦስት ቡድኖች አሉ።
በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙት ወንድሞች በሕንድ የፑንጃብኛ ተርጓሚ ሆኜ እንዳገለገልኩ ያውቁ ነበር። ስለዚህ ቅርንጫፍ ቢሮው በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በለንደን ቤቴል በተመላላሽነት እንዳገለግል ግብዣ አቀረበልኝ። የተጠራሁት የጉርሙኪ ፊደላትንና የአጻጻፍ ሕጋቸውን ኮምፒውተር ውስጥ በማስገባቱ ሥራ እንዳግዝ ነው። ሰብዓዊ ሥራ እሠራ፣ ራቅ ያለ አካባቢ የምትኖረውን እናቴን እንከባከብ እንዲሁም በቤቴል በተመላላሽነት አገለግል ስለነበር ፕሮግራሜ በጣም የተጣበበ ነበር። ሆኖም በቤቴል የመሥራት መብት በማግኘቴ ደስተኛ ነበርኩ።
በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ በለንደን ቤቴል ሥልጠና ሲሰጠኝ
መስከረም 1991 የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆኜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ፑንጃብኛ እንድተረጉም ተጠራሁ። ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ነው። ለሥራው ብቁ እንደሆንኩ አይሰማኝም ነበር። በዚያ ላይ ታማሚ የነበርኩ ከመሆኑም በላይ ዕድሜዬ አዲስ ቤቴላዊ ሆኖ መግባት ከሚቻልበት የዕድሜ ገደብ በላይ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ይህን ልዩ መብት ሰጠኝ። በቤቴል አገልግሎቴ ደስተኛ ብሆንም የነበረብኝ የጤና ችግር አልተቀረፈም። በተደጋጋሚ ኬሞቴራፒ እና ሌሎች ሕክምናዎችን ለመውሰድ በማደርገው ጥረት ከደም ጋር በተያያዘ ችግሮች አጋጥመውኛል። ሐኪሞቼ በጥሩ ሁኔታ በማገገሜ በጣም ስለተደነቁ ለንደን ውስጥ በሚገኝ ትልቅ ሆስፒታል በተካሄደ 40 የሕክምና ባለሙያዎች የተገኙበት ሴሚናር ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ያለኝን አቋም በተመለከተ የ10 ደቂቃ ንግግር አቀረብኩ፤ ከዚያም በሆስፒታል መረጃ ዴስክ የሚሠራ ወንድም ተሰብሳቢዎቹ የነበሯቸውን ጥያቄዎች መለሰላቸው።
በእነዚህ ከባድ ጊዜያት እህቶቼ ጃስዊንደርና ቻኒ ከጎኔ አልተለዩም፤ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና ሌሎች ወዳጆቼም በደግነት ድጋፍ አድርገውልኛል። በፈተናዎቼ ሁሉ ይሖዋ ብርታት በመስጠት በአገልግሎት ምድቤ እንድቀጥል ረድቶኛል።—መዝሙር 73:26
የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች
በቤቴል ያሳለፍኳቸው 33 ዓመታት ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሼ የማይበት’ አጋጣሚ ሰጥተውኛል። (መዝሙር 34:8፤ ምሳሌ 10:22) በዕድሜ የገፉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምሳሌ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በፑንጃብኛ ያስጠናኋቸው በርካታ ጥናቶቼ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸው ደስታ ይሰጠኛል። ከቅርብ ቤተሰቦቼ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። እናቴና ወንድሜ የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም እናቴ ብዙ ጊዜ “አንቺ መቼም ራስሽን ለአምላክ የሰጠሽ ሰው ነሽ” ትለኛለች። ከቤቴል ወጥቼ በዕድሜ የገፋችውን እናታችንን አጠገቧ ሆኜ ለመንከባከብ ሐሳብ ሳቀርብ ወንድሜ “እየሠራሽ ያለሽው መልካም ሥራ ነው። እዚያው ቆዪ” አለኝ። እናቴ የምትኖረው ከቤቴል ርቆ በሚገኝ የአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ቢሆንም በቻልኩት መጠን እየሄድኩ እጠይቃታለሁ።
በሕይወቴ ውስጥ የሆነ ችግር ሲያጋጥመኝ ራሴን እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘ካማል አትፍሪ። ይሖዋ ጋሻ ይሆንሻል። የምታገኚውም ሽልማት እጅግ ታላቅ ይሆናል።’ (ዘፍጥረት 15:1) “የፍትሕ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ ትኩረት ስለሰጠኝና ሕይወቴ ትርጉም ባለው ሥራ የተጠመደ እንዲሆን ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ። (ኢሳይያስ 30:18) ‘ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” የማይልበትን’ ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።—ኢሳይያስ 33:24
በቼልምስፎርድ ቤቴል