በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስተ ግራ፦ በቺሊ የእርዳታ ሠራተኞች አውዳሚ ሰደድ እሳት ከደረሰ በኋላ የአንድን ባልና ሚስት ቤት ሲጠግኑ። በስተ ቀኝ፦ በናይጄርያ የሚኖሩ ሁለት እህቶች በአካባቢያቸው አደገኛ ጎርፍ ከተከሰተ በኋላ የእርዳታ ቁሳቁስ ሲቀበሉ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ በ2023—“የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል”

የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ በ2023—“የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል”

ጥር 26, 2024

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ” እንደሚነሳ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 7) በ2023 የአገልግሎት ዓመት ይህ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተናል። a ወደ 100 በሚጠጉ አገሮች ውስጥ ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰትም የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን ፍቅር አንጸባርቀዋል። እንዴት?

 በ2023 የአገልግሎት ዓመት ወንድሞቻችን ከ200 በሚበልጡ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ ድርጅቶች ለዓለም አቀፉ ሥራ ከተዋጣው ገንዘብ ውስጥ ለአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ በድምሩ ከአሥር ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አውጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የራሳቸውን ገንዘብ ተጠቅመው በአካባቢያቸው በእርዳታ ሥራ ተካፍለዋል። ያደረጋችሁት መዋጮ በወንድሞቻችን ላይ ከደረሱት አደጋዎች መካከል በሁለቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ለመርዳት ጥቅም ላይ የዋለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“እውነተኛ ፍቅር በእርግጥ አለ”

 በናይጄርያ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በየዓመቱ የጎርፍ መጥለቅለቅ ያጋጥማቸዋል። ይሁንና ጥቅምት 2022 የተከሰተው ጎርፍ በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት አሥር ዓመታት ከደረሱት ሁሉ የከፋው ነበር። ከ676,000 ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ወድሟል፤ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። የናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ የእርዳታ ሥራውን ለማስተባበርና መንፈሳዊ እገዛ ለማበርከት ወዲያውኑ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቋመ።

በናይጄርያ የሚኖሩ ወንድሞች በጎርፍ የተጥለቀለቁ መንገዶችንና ወንዞችን አቋርጠው የእርዳታ ቁሳቁስ ሲያደርሱ

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  •   7,505 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል

  •   860 ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል

  •   90 የስብሰባ አዳራሾችና አንድ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል

በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ

 ለእርዳታ ሥራው ከ250,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጥቷል፤ ገንዘቡ ለሚከተሉት ዓላማዎች ውሏል፦

  •   እንደ ሩዝ፣ ባቄላ እና ፓስታ ያሉ የምግብ ሸቀጦችን ለማቅረብ

  •   እንደ ፍራሽ እና አጎበር ያሉ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ለማሟላት

  •   ጉዳት ለደረሰባቸው ቤቶች ጥገና ወይም መልሶ ግንባታ

 ወንድሞቻችን በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እያንዳንዱን ሕንፃ በሚገባ በመገምገም መጠገን ይችል እንደሆነ በማጣራት ነው። ሕንፃው እንደ አዲስ መገንባት ካለበት ደግሞ በአካባቢው የተለመደውን ቀለል ያለ ንድፍ በመጠቀም መልሶ ለመገንባት ተሞክሯል።

 እርዳታ የተደረገላቸው ወንድሞችና እህቶች አመስጋኝነታቸውን ገልጸዋል። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ጎርፉ ሕይወታችንን አመሰቃቅሎታል፤ ምክንያቱም እርሻችንና ቤታችን ወደመ። ወንድሞችና እህቶች በዚያው ዕለት መጥተው እርዳታ ሲያበረክቱልንና ማረፊያ ሲያመቻቹልን እፎይታ ተሰማን። ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላኩት የምግብ ሸቀጦች ሲደርሱን በጣም ተደሰትን። ዮሐንስ 13:34, 35 በገዛ ሕይወታችን ሲፈጸም ስንመለከት ደስታችንን ለመግለጽ ቃል አልነበረንም። . . . እውነተኛ ፍቅር በእርግጥ አለ። ወንድሞቻችን ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ስለደረሱልን እኔና መላው ቤተሰቤ ልባዊ ምስጋናችንን መግለጽ እንፈልጋለን።”

 በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም ያከናወንነውን የእርዳታ ሥራ ተመልክተዋል። በሳባግሬያ፣ ባዬልሳ ግዛት የሚገኙ አንድ የማኅበረሰቡ መሪ እንዲህ ብለዋል፦ “በዓለም ላይ ብዙ ድርጅቶችና ቤተ ክርስቲያኖች አሉ፤ እንዲህ ያለ ነገር ያደረጉት ግን የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። . . . በዓለም ላይ ካሉት ግሩም ድርጅቶች አንዱ [የእናንተ] ድርጅት ነው።”

“የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል”

 የካቲት 2023 በቺሊ የተከሰቱት ከ400 የሚበልጡ እሳቶች መጠነ ሰፊ ውድመት አስከትለዋል። የቺሊን ወሳኝ መሠረተ ልማቶች የያዘ ከ430,000 ሄክታር በላይ መሬት ወድሟል። ስምንት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል። አደጋው ከደረሰ ብዙም ሳይቆይ ቅርንጫፍ ቢሮው የእርዳታ እንቅስቃሴውን ማስተባበር ጀመረ።

በቺሊ የእርዳታ ሠራተኞች መጠገን ያልቻለን ቤት እንደ አዲስ ሲገነቡ

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

  •   222 አስፋፊዎች መኖሪያቸውን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል

  •   20 ቤቶች ወድመዋል

በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ

 ለእርዳታ ሥራው ከ200,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጥቷል፤ ገንዘቡ ለሚከተሉት ዓላማዎች ውሏል፦

  •   ምግብ እና ውኃ ለማቅረብ

  •   ነዳጅ፣ የጽዳት ቁሳቁሶች እና መድኃኒቶች ለማቅረብ

  •   ጉዳት ለደረሰባቸው ቤቶች መልሶ ግንባታ

 አንድ ቤተሰብ ቤታቸውንና ንግዳቸውን ጨምሮ ያላቸው ንብረት ሁሉ በመውደሙ በጣም ደንግጠው ነበር። ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት ምንም መንገድ አልነበራቸውም። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ቤተሰቡ ቤታቸው የነበረበት ቦታ ባዶ ሆኖ ሲያዩ በሐዘን ይዋጡ ነበር። የመልሶ ግንባታ ሥራው እየገፋ ሲሄድ ግን ቀስ በቀስ ፍርሃታቸውን ማሸነፍ ቻሉ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ያሳዩአቸውን ፍቅር መመልከታቸው ሁኔታውን እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል። ቤተሰቡ በዚህ ሁኔታ ልባቸው በጥልቅ ስለተነካ የሌላ ወንድም ቤት መልሶ ሲገነባ ከፈቃደኛ ሠራተኞቹ ጋር ሆነው በሥራው ተካፍለዋል።

 በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእርዳታ ሥራው ልባቸው ተነክቷል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ያደረገው የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ዝግጅት በጣም አስደናቂ ነው። አደጋው በደረሰ በማግስቱ በቦታው ተገኝተው መሠረታዊ ቁሳቁሶችን እያከፋፈሉ ነበር። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ስለሚካሄደው የእርዳታ ሥራ ስናነብ ልባችን ይነካል። በራሳችን ላይ ሲደርስ ግን ሁኔታው እጅግ የተለየ ነው። ለድርጅቱ ያለን አድናቆት ይጨምራል፤ ወንድሞች የይሖዋን ባሕርይ ምን ያህል እንደሚያንጸባርቁ እንዲሁም በቁሳዊ፣ በመንፈሳዊም ሆነ በስሜታዊ የሚያስፈልገን ነገር መሟላቱ ምን ያህል እንደሚያሳስባቸው እንመለከታለን። የይሖዋን ፍቅር በዓይናችን አይተናል።”

 ይህ ሥርዓት እየተገባደደ ሲሄድ አደጋዎች መጨመራቸው አይቀርም። (ሉቃስ 21:10, 11) ይሁንና አፍቃሪ ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ‘እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር’ እንደሆነ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት እናያለን። (ማቴዎስ 28:20) በ​donate.jw.org እና በሌሎች መንገዶች አማካኝነት በልግስና የምታደርጉት መዋጮ እንዲሁም ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ሳትሳሱ መስጠታችሁ መንግሥቱንና አፍቃሪ የሆነውን ንጉሣችንን እንደምትደግፉ ያሳያል። በቀጣይነት ለምታሳዩት ልግስና እናመሰግናችኋለን።

a የ2023 የአገልግሎት ዓመት መስከረም 1, 2022 ጀምሮ ነሐሴ 31, 2023 አልቋል።