በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአስቴር መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው የፋርስ ንጉሥ ጠረክሲስ ማን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአስቴር መጽሐፍ እንደሚገልጸው ንጉሥ ጠረክሲስ (መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ አሐሽዌሮስ ይባላል)፣ አስቴር የተባለችውን አይሁዳዊት ልጃገረድ ንግሥት እንድትሆን የመረጣት ሲሆን እሷም በሕዝቧ ላይ የተቃጣውን የዘር ማጥፋት ሙከራ ማስቆም ችላለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሐሽዌሮስ ተብሎ የተጠራውን የፋርስ ንጉሥ ማንነት በተመለከተ ምሁራን የተለያዩ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ ኖረዋል። ይሁንና በፋርስ ሐውልቶች ላይ የተገኘውን በሦስት ቋንቋዎች የተዘጋጀ መረጃ መተርጎም መቻሉ ለዚህ ጥያቄ እልባት የሰጠው ይመስላል። ይህ መረጃ በአስቴር መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው አሐሽዌሮስ፣ የታላቁ ዳርዮስ (ሂስታስፒስ) ልጅ የሆነው ቀዳማዊ ጠረክሲስ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። በሐውልቶቹ ላይ በተገኙት የባቢሎንና የፋርስ ጽሑፎች ላይ ያለው ሐሳብ በዕብራይስጥ ሲቀመጥ ጠረክሲስ የሚለው ስም የሰፈረበት መንገድ፣ ስሙ በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ በዕብራይስጥ ከተጻፈበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል።

በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ስለ አሐሽዌሮስ የተጻፈው ሐሳብ በሙሉ ስለ ቀዳማዊ ጠረክሲስ ከሚታወቀው ነገር ጋር ይስማማል። ይህ የፋርስ ንጉሥ በሱሳ፣ ኤላም ከሚገኘው መዲናው ሆኖ ሜዶናውያንንም ይገዛ የነበረ ሲሆን ግዛቱ ከሕንድ አንስቶ በሜድትራንያን እስከሚገኙት ደሴቶች ይደርስ ነበር። (አስቴር 1:2, 3፤ 8:9፤ 10:1) ሉዊስ ቤልስ ፔተን የተባሉት ምሁር፣ “ከፋርስ ነገሥታት መካከል [ከላይ የሰፈረው ሐሳብ] በሙሉ የሚስማማው ከጠረክሲስ ጋር ብቻ” እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም “[በአስቴር] መጽሐፍ ላይ ስለ አሐሽዌሮስ የሰፈረው ሐሳብ ሄሮዶተስና ሌሎች የግሪክ የታሪክ ጸሐፊዎች ስለ ጠረክሲስ ካሰፈሩት ዘገባ ጋር ይስማማል” ብለዋል።

በጥንቷ ግብፅ ጡብ ይሠራ እንደነበር የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፀአት መጽሐፍ ግብፃውያን፣ ዕብራውያን ባሪያዎቻቸውን ጡብ ያሠሯቸው እንደነበር ይናገራል። ባሪያዎቹ ጭቃና ጭድ ተጠቅመው በየዕለቱ የተወሰነላቸውን ያህል ጡብ መሥራት ነበረባቸው።​—ዘፀአት 1:14፤ 5:10-14

በጥንት ዘመን በናይል ሸለቆ በፀሐይ የደረቁ ጡቦችን ማምረት ትልቅ ቦታ የሚሠጠው ሥራ ነበር። ከጡብ የተሠሩ ጥንታዊ ሐውልቶች ዛሬም ድረስ በግብፅ ይገኛሉ። በ15ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በተገነባው በቴብስ የሚገኝ የሬክማየር መቃብር ላይ ያለው ሥዕል ጡብ የሚሠራበትን መንገድ በግልጽ ያሳያል፤ ይህ መቃብር የተሠራው በዘፀአት መጽሐፍ ላይ የተገለጹት ክንውኖች በተፈጸሙበት ጊዜ አካባቢ ነው።

ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ በሥዕሉ ላይ የሚታየውን ክንውን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ከኩሬ ውኃ ቀድተው ያመጣሉ፤ ከዚያም ጭቃውን በገሶ ከቀላቀሉት በኋላ ለጡብ መሥሪያ አመቺ ወደ ሆነ ቦታ ይወስዱታል። ጡብ የሚሠሩት ሰዎች ከእንጨት የተሠራ ቅርጽ ማውጫ መሬት ላይ አስቀምጠው ጭቃውን እዚያ ውስጥ ይጠቀጥቁታል። ከዚያም ቅርጽ ማውጫውን ሲያነሱት የሚያገኙትን ጡብ በፀሐይ ያደርቁታል። በቅርጽ ማውጫ እየተጠቀሙ የሠሯቸውን በርካታ ጡቦች በመደዳ ያስቀምጧቸዋል፤ ጡቦቹ ሲደርቁም ጥቅም ላይ እስኪውሉ ድረስ ይደረድሯቸዋል። ይህ ዘዴ ዛሬም ቢሆን በመካከለኛው ምሥራቅ ይሠራበታል።”

በሁለተኛው ሺህ ዓ.ዓ. የተጻፉ የተለያዩ የፓፒረስ መዛግብትም፣ ባሪያዎች ጡብ ይሠሩ እንደነበር፣ ይህንን ለማድረግ ጭድና የሸክላ አፈር እንደሚጠቀሙና ሠራተኞቹ በየዕለቱ የተወሰነ መጠን ማምረት እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻሉ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጠረክሲስን (የቆመው) እና ታላቁ ዳርዮስን (የተቀመጠው) የሚያሳይ የድንጋይ ሐውልት

[የሥዕሉ ምንጭ]

Werner Forman/Art Resource, NY

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሬክማየር መቃብር ላይ የሚገኘው ሥዕል

[የሥዕሉ ምንጭ]

Erich Lessing/Art Resource, NY