ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ “ባረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያስቀምጥ ሰው የለም” ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?

በጥንት ጊዜ ከእንስሳት ቆዳ በተሠራ አቁማዳ ውስጥ ወይን ጠጅ ማስቀመጥ የተለመደ ነበር። (ኢያሱ 9:13) አቁማዳ እንደ ግልገል ወይም ፍየል ካሉ የቤት እንስሳት ቆዳ ይሠራ ነበር። አቁማዳ የሚሠራው ፍየሉ ከታረደ በኋላ ጭንቅላቱና እግሮቹ ተቆርጠው ቆዳው ምንም ቦታ ሳይቆረጥ ሙሉውን በመግፈፍ ነው። ከዚያም ቆዳው ይለፋና አንገቱ ወይም አንድ እግር ብቻ ሲቀር ሌሎች ቀዳዳዎች በሙሉ ይሰፋሉ፤ ይህ ያልተሰፋው ክፍል የአቁማዳው አፍ ሆኖ ያገለግላል። የአቁማዳው አፍ በውታፍ ይዘጋል ወይም በሲባጎ ይታሰራል።

ከጊዜ በኋላ ቆዳው ስለሚቆረፍድ እንደልብ ሊለጠጥ አይችልም። በመሆኑም ያረጀ አቁማዳ እየፈላ የሚሄድ አዲስ ወይን ጠጅ ለማስቀመጥ አይሆንም። ምክንያቱም ወይኑ እየፈላ ሲሄድ የቆረፈደውን ቆዳ ሊያፈነዳው ይችላል። በሌላ በኩል አዲስ አቁማዳ የመለጠጥ ባሕርይ ስላለው አዲስ ወይን ሲፈላ የሚኖረውን ግፊት መቋቋም ይችላል። ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሲናገር በወቅቱ በሚገባ የሚታወቀውን አንድ ሐቅ እየጠቀሰ ነበር። አንድ ሰው አዲስ የወይን ጠጅ ባረጀ አቁማዳ ውስጥ ቢያስቀምጥ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ መጨመር አለበት።”—ሉቃስ 5:37, 38

ጳውሎስ በሮማውያን ከመያዙ ጋር በተያያዘ የተጠቀሱት “ነፍሰ ገዳዮች” እነማን ነበሩ?

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚናገረው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሁካታ በተፈጠረበት ወቅት የሮም ጦር አዛዥ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮችን” በመምራት ዓመፅ ያስነሳው ሰው ስለመሰለው በጥበቃ ሥር እንዲሆን አደረገው። (የሐዋርያት ሥራ 21:30-38) ስለ እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

“ነፍሰ ገዳዮች” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሲካሪ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን “ሲካ የሚጠቀሙ” ወይም ጩቤ የሚጠቀሙ የሚል ትርጉም አለው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ሲካሪ ስለተባሉት ሰዎች ሲገልጽ በፖለቲካዊ ዓላማ ተነሳስተው ግድያ ለመፈጸም የተደራጁና የሮም የምንጊዜም ጠላት የነበሩ አክራሪ የአይሁድ ዓማፂ ቡድኖች እንደሆኑ ተናግሯል።

ጆሴፈስ እንደገለጸው ሲካሪዎች “በጠራራ ፀሐይ ከተማ ውስጥ ሰዎችን ይገድሉ ነበር፤ አብዛኛው ጊዜ ይህን የሚያደርጉት በበዓል ቀናት ሲሆን ጠላቶቻቸውን ለመውጋት የሚጠቀሙባቸውን ጩቤዎች ልብሳቸው ውስጥ በመሸሸግና ከሕዝቡ ጋር በመቀላቀል ነው።” እነዚህ ሲካሪዎች የወጉት ሰው ሲሞት ማንም ሰው እንዳይጠረጥራቸው ለማድረግ ሲሉ በሰውየው ሞት እንደተናደዱ ለማስመሰል ይሞክራሉ። ጆሴፈስ እነዚህ ሲካሪዎች ቆየት ብሎ ማለትም ከ66 እስከ 70 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ላስነሱት ዓመፅ ትልቅ ሚና ተጫውተው እንደነበር አክሎ ተናግሯል። በመሆኑም ጳውሎስን የያዘው ሮማዊ የጦር አዛዥ የዚህ ቡድን መሪ ብሎ የጠረጠረውን ሰው በቁጥጥር ሥር የማዋል ከፍተኛ ጉጉት ነበረው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያረጀ አቁማዳ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሠዓሊ አንድን ነፍሰ ገዳይ በሥዕሉ እንዳስቀመጠው