በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደመና ውስጥ የሚገኝ ኮራል ሪፍ

በደመና ውስጥ የሚገኝ ኮራል ሪፍ

ከፓፑዋ ኒው ጊኒ የተላከ ደብዳቤ

በደመና ውስጥ የሚገኝ ኮራል ሪፍ

ዕለቱ ማክሰኞ ሲሆን በፓፑዋ ኒው ጊኒ በምትገኘው ሊ በምትባል ከተማ ውስጥ ገና ከማለዳው አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ሙቀቱ ከብዷል። እኔና ባለቤቴ፣ በሞሮቤ አውራጃ ሮለንሰን በሚባል ተራራ ላይ ሌንግባቲ በተባለችው መንደር ውስጥ የሚገኘውን አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ለመጎብኘት እየተዘጋጀን ነው።

የምንጓዘው አራት ሰዎችን ብቻ በምትይዝ ባለ አንድ ሞተር አውሮፕላን ሲሆን ጉዟችን 30 ደቂቃ ብቻ ይፈጃል። እንዲህ ባሉ ጉዞዎች ወቅት ብዙ ጊዜ ከአብራሪው ጎን በመቀመጥ ሁለታችንም በጆሮ ማዳመጫ ተጠቅመን እንጫወታለን፤ ይህን የምናደርገው ሞተሩ በጣም ስለሚጮኽ ነው። አብራሪው ከፊት ለፊታችን ሰሌዳው ላይ ያሉትን የበረራ መሣሪያዎች እያሳየ ተግባራቸው ምን እንደሆነ ይነግረኝ እንዲሁም ድንገት አንድ ነገር ቢያጋጥመው አውሮፕላንዋን እኔ እንደማበር እየተናገረ ይቀልድ ነበር። ይህን ሲል በፓፑዋ ኒው ጊኒ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ አገልጋይ አጋጥሞት የነበረው ነገር ትዝ አለኝ። በጉዞ ላይ እያሉ አብራሪው ራሱን ሲስት እስኪነቃና አውሮፕላንዋን እስኪያሳርፋት ድረስ በአውቶማቲክ ማብረሪያው አማካኝነት አውሮፕላንዋ በአየር ላይ ስትሽከረከር ነበር። ደስ የሚለው እኛ ያደረግነው በረራ ሰላማዊ ስለነበር ምንም አልተከሰተም።

በአሁኑ ጊዜ እየበረርን ያለነው በሰንሰለታማ ተራሮች ላይ ሲሆን ድንገት ደመናው ከፈት ሲልልንና ስንታጠፍ ከረጅሙ የተራራ አናት የነበረን ርቀት ወደ 100 ሜትር ገደማ ብቻ ነበር። ከፊት ለፊታችን ከእንጨት የተሠሩና የሣር ክዳን ያላቸው ቤቶች ችምችም ብለው የሚገኙባት የሌንግባቲ መንደር ታየችን። አብራሪው አውሮፕላንዋ በምታርፍበት ሜዳ ላይ እያንዣበበ የመንደሩ ልጆች በሜዳው ላይ እግር ኳስ እየተጫወቱ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ወደታች ተመለከተ። በተጨማሪም ባለፈው ከመጣ ወዲህ አሳማዎች የቆፈሩት ጉድጓድ መኖር አለመኖሩን አረጋገጠ። ተመልሶ ወደ ሸለቋማው አካባቢ ካመራ በኋላ “ጥሩ ይመስላል፤ ለማረፍ እንሞክራለን” በማለት ተናገረ። ዞረን ከመጣን በኋላ የመንደሩ ነዋሪዎች ተራራውን ገምሰው በአቅራቢያው ከሚገኝ ተራራ ላይ የተሰባበረ የኮራል በሃ ድንጋይ አምጥተው በመደልደል ባዘጋጁት አነስተኛ ሜዳ ላይ አረፍን።

ከዚህ በፊት ወደዚህ አካባቢ በመጣሁባቸው ጊዜያት የተሰባበሩ የኮራል በሃ ድንጋዮችን ተመልክቼ ‘ይህ ሰንሰለታማ ተራራ ምን ያህል ዕድሜ ይኖረው ይሆን?’ ብዬ አስቤ ነበር። በመቶ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ስፋት ያለውን ይህን የቀድሞ ኮራል ሪፍ ከውቅያኖሱ በላይ 4 ኪሎ ሜትር ከፍታ ያለው ተራራ እንዲሆን ያደረገው ኃይል ምን ያህል ኃይለኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትም! ከአውሮፕላን ወርደን ‘በደመና ውስጥ የሚገኝ ኮራል ሪፍ’ ብዬ የጠራሁትን መሬት ረገጥን።

እንደተለመደው የመንደሩ ነዋሪዎች የአውሮፕላን ድምፅ ሲሰሙ ከተለያየ አቅጣጫ እየሮጡ መጡ። አብራሪው ሞተሩን እያጠፋ እያለ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አንድ ሰው ወደ አውሮፕላንዋ ሲመጣ አየሁ። ይህ ሰው ዙንግ የሚባል ሲሆን በዚያ አካባቢ የሚካሄደውን የይሖዋ ምሥክሮች ሳምንታዊ የትምህርት ፕሮግራም በኃላፊነት እንዲከታተል ከተመደቡት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ዙንግ በአካባቢው ሰዎች ዘንድ ንጹሕ አኗኗር ያለው፣ ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኑ ይታወቃል። እንዲህ ዓይነት ሰው ሊሆን የቻለው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተምሮ ተግባራዊ ስላደረገ እንደሆነ ይናገራል። ሰላም ከተባባልንና ከተጨባበጥን በኋላ ከዙንግና ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከተራራው ትንሽ ወረድ ብሎ ወደሚገኝ አካባቢ ሄድን። ከኋላችን ተከትለው የመጡ ልጆች ሻንጣችንን ‘እኔ ልሸከም’ በማለት እርስ በርስ ይጣሉ ነበር።

ትንሽ ከሄድን በኋላ በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በስድስት ወር አንዴ የሚጎበኛቸው ተጓዥ አገልጋይ እንዲያርፍበት አስበው ወደሠሩት አንድ አነስተኛ የእንጨት ቤት ደረስን። ፓፑዋ ኒው ጊኒ ሞቃታማ የአየር ንብረት ያላት አገር ብትሆንም ያለንበት አካባቢ ተራራማ በመሆኑ አካባቢው ይቀዘቅዛል። ምሽት ላይ ኩራዛችንን ስናበራ ብዙውን ጊዜ ከሰዓት በኋላ ላይ ከሸለቆ አካባቢ ተነስቶ ወደ ተራራው ሲተም የነበረው ጉም በቤቱ ወለል መካከል በሚገኝ ክፍተት ቀስ እያለ ሲገባ እመለከት ነበር። በዚህ ጊዜ እንዲሞቀን ብለን በበረዶ ወቅት የሚለበስ ጃኬትና ጂንስ ለብሰን ላየን ሰው፣ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በባሕሩ ዳርቻ በነበረው ሙቀት ስንጨነቅ የነበርን ሰዎች ላንመስለው እንችላለን።

በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የዚህ አካባቢ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው ሊ በምትባለው ከተማ መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። ይህ ሰው ወደዚህ መንደር ተመልሶ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን በጣም የሚኮሩበት አነስተኛ መሰብሰቢያ ገነባ። ይሁንና በአካባቢው ያለ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ይህን የመሰብሰቢያ ቦታ ሙሉ በሙሉ አቃጠለው። ይህን ያደረጉት ሰዎች አካባቢው የሉተራን እምነት ተከታዮች ብቻ እንደሆነ በኩራት ተናግረው ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ተቃውሞው ባያባራም የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሠሩ ሲሆን የምሥራቹ አስፋፊዎች ቁጥር ቀስ በቀስ አድጎ 50 ደረሰ። ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ አሁን በቅንዓት በዚህ ሥራ ላይ እየተካፈሉ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የመንደሩ ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሯቸውን የይሖዋ ምሥክሮች በደስታ ይቀበላሉ። በአካባቢው ካሉት ነዋሪዎች ውስጥ ማንበብ የሚችሉት በጣም ጥቂቶች ቢሆኑም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማስተማር ሲሉ ማንበብ ተምረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በመሰብሰቢያ አዳራሻቸው ውስጥ በየሳምንቱ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እስከ 200 ሰዎች ይገኛሉ።

በአካባቢው ኤሌክትሪክ የለም። ማታ ማታ ሁላችንም ምግብ በሚሠራበት እሳት ዙሪያ ተሰብስበን አንድ ላይ እንበላለን፣ እናወራለን እንዲሁም እንስቃለን። ጓደኞቻችንን በእሳቱ ደብዛዛ ብርሃን ስናያቸው ፊታቸው ላይ የሚነበበው ፈገግታ ይሖዋን በማገልገላቸው ደስተኞች መሆናቸው በግልጽ ይታያል። ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ አንዳንዶቹ ቦምቦም ወይም ቀስ ብሎ የመንደድ ባሕርይ አለው ብለው የሚያስቡትን የዘንባባ ቅርንጫፍ ከእሳቱ ውስጥ መዘዝ አድርገው እያወጡ ጫካውን አቆራርጠው ወደየቤታቸው ይሄዳሉ።

ወደ ቤታችን ስንመለስ የአካባቢውን ጸጥታ አስተውለን ነበር። ዙሪያችን የሚሰማ ነገር ቢኖር የተፈጥሮ ድምፅ ብቻ ነው። ከመተኛታችን በፊት ከፍ ብሎ በሚገኘው በዚህ ቦታ ላይ ሆነን ለመጨረሻ ጊዜ ጥርት ያለውን ሰማይ ስንመለከት በከዋክብቱ ብዛት በጣም ተደነቅን።

ሳምንቱ በፍጥነት አልፎ ነገ የሚመጣውን አውሮፕላን እየጠበቅን ነው። ከዚህ በኋላ ቀዝቃዛ በሆነችውና በጉም ውስጥ በምትገኘው በሌንግባቲ የቀረን አንድ ሌሊት ብቻ ነው፤ ነገ ኃይለኛ ሙቀትና ወበቅ ወዳለበት ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንመለሳለን።