በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ጳውሎስ ይህን የጻፈው በግሪክኛ ሲሆን ይህ ሐሳብ ቃል በቃል ሲተረጎም “አምላክ የተነፈሰበት” የሚል ትርጉም አለው። ጳውሎስ ይህን ሲል አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እሱ የሚፈልገውን ሐሳብ ብቻ እንዲጽፉ መርቷቸዋል ማለቱ ነበር።

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ መጻሕፍትን ‘በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ ለማግኘት የሚያስችሉ ቅዱሳን መጻሕፍት’ በማለት ገልጿቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15

ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ አምላክ ነው የሚለውን ሐሳብ አጥብቀው ይቃወማሉ። አርኪኦሎጂስቱ ሰር ቻርልስ ማርስተን ተቺዎችን በተመለከተ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ያጣጥላሉ’ በማለት እንደገለጹት እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ስለመሆኑ የሰላ ትችት ይሰነዝራሉ። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን “አፈ ታሪኮችንና ተረቶችን የያዘ ጥንታዊ መጽሐፍ” እንደሆነ አድርገው ስለሚያዩት አይቀበሉትም።

ማስረጃዎቹን መርምር

በሰዎች ላይ እምነት እንድትጥል የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት ይችላል? በዚህ ረገድ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግህ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ያስጻፈው አምላክ ራሱ ከሆነ መጽሐፉን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ሞኝነት አልፎ ተርፎም ሕይወት የሚያሳጣ ይሆንብሃል። መጽሐፍ ቅዱስን የአምላክ ቃል ሳይሆን የሰዎች ቃል አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የመመራትህ እንዲሁም እምነትህ በቃሉ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የማድረግህ አጋጣሚ በጣም ጠባብ ይሆናል።—1 ተሰሎንቄ 2:13

መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሰዎች ላይ እምነት እንድትጥል የሚያደርግህ ምን እንደሆነ እንመልከት። በዚህ ረገድ አንድ የታወቀ ሐቅ አለ፦ እምብዛም በማታውቃቸው ሰዎች ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት መጣል በጣም አስቸጋሪ ነው። እነዚያ ሰዎች በእርግጥም ሐቀኞችና እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን የምትተማመነው በጊዜ ሂደት እያወቅካቸው ስትሄድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስንም በዚሁ መንገድ እያወቅከው ልትሄድ ትችላለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለህን እምነት የሚሸረሽሩ ግምታዊ ሐሳቦችን አልፎ ተርፎም ጭፍን አመለካከቶችን ዝም ብለህ አትቀበል። መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ” መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ጊዜ ወስደህ መርምር።

“ከወዳጆች” የሚሰነዘር ጥቃት

የመጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጆች” እንደሆኑ አድርገው የሚናገሩ ሰዎች ጭምር በዚህ መጽሐፍ ትክክለኝነትና ተአማኒነት ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት ሰምተህ በመጽሐፉ ላይ ጥርጣሬ አይደርብህ። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ክርስቲያን እንደሆኑ ቢናገሩም እንኳ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሰዎች እንደጻፏቸው አድርገው እንደሚናገሩ” ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ቲኦሎጂ ገልጿል።

በርካታ የሃይማኖት ምሑራን የመጽሐፍ ቅዱስን መጻሕፍት የጻፉትን ሰዎች ማንነት ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች የኢሳይያስን መጽሐፍ የጻፈው ነቢዩ ኢሳይያስ አይደለም ይላሉ። ይህ መጽሐፍ ኢሳይያስ ከኖረ ከብዙ ዘመን በኋላ እንደተጻፈ ይናገራሉ። በሎውዘር ክላርክ የተዘጋጀው ኮንሳይስ ባይብል ኮሜንታሪ የተባለው መጽሐፍ “የብዙ ሰዎች ሐሳብና የብዙ ትውልድ የሥራ ውጤት ነው” የሚል ትችት ሰንዝሯል። ይሁንና እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ጊዜ የተናገሯቸውን ኢሳይያስ ይህን መጽሐፍ እንደጻፈ የሚጠቁሙ ሐሳቦች ግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም።—ማቴዎስ 3:3፤ 15:7፤ ሉቃስ 4:17፤ ዮሐንስ 12:38-41፤ ሮም 9:27, 29

ከዚህ የከፋው ደግሞ እንደ ጆን ደመሎ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች “ታሪኮቹ ከተከናወኑ በኋላ ጸሐፊው እንደ ትንቢት አድርጎ የጻፋቸው እንደሆኑ” ተናግረዋል። እንዲህ ብለው መናገራቸውም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ምሥክርነት አለመቀበል ነው፤ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:15 ላይ “በነቢዩ ዳንኤል በተነገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል” በማለት ተናግሯል። አንድ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለፈን ታሪክ እንደ ትንቢት አድርጎ ለማቅረብ ከተደረገው የማታለል ተግባር ጋር ተባብሯል ብሎ ቢያስብ ምክንያታዊ ይሆናል? እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

የሚያመጣው ለውጥ አለ?

“የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን የጻፈው ማንስ ቢሆን ለውጥ ያመጣል?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የአንድ ጓደኛህ የኑዛዜ ቃል እንደሆነ አድርገህ ታስብ የነበረውን አንድ ሰነድ በእርግጥ እሱ እንዳልጻፈው ብታውቅ በዚያ ሰነድ ላይ እምነት ትጥላለህ? ባለሙያዎች፣ ሰነዱ የሐሰት እንደሆነና ወዳጆችህ በደግነት ተነሳስተው ጓደኛህ ለአንተ ይናዘዝልሃል ብለው የገመቱትን ነገር እንደጻፉ ነገሩህ እንበል። ይህ ለሰነዱ ያለህን ግምት አይቀንሰውም? የጓደኛህን ትክክለኛ ኑዛዜ ይዟል ብለህ በሰነዱ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ብዙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታማኝነት፣ ስለ ፆታ ሥነ ምግባርና ስለመሳሰሉት ነገሮች የሚናገረውን ሐሳብ ችላ ሲሉ ምንም የማይመስላቸው መሆኑ አያስደንቅም። ሰዎች ብሉይ ኪዳን የረባ ጥቅም የሌለው ይመስል “ይህማ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለ ነው!” ብለው ያላንዳች እፍረት ሲናገሩ ብዙ ጊዜ ሳትሰማ አትቀርም። ሰዎች ብሉይ ኪዳንን ጊዜ ያለፈበት አድርገው ቢናገሩም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ’ “ቅዱሳን መጻሕፍት” በማለት ጠርቷቸዋል።

“ምሑራን የሚያቀርቧቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ችላ ብለን ማለፍማ የለብንም” በማለት ትከራከር ይሆናል። ልክ ነው እንደዚያ ማድረግ የለብንም! ለምሳሌ ያህል፣ ስለ መጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንድናውቅ የረዱን ሐቀኛ ምሑራን ባለውለታዎቻችን ናቸው። ለብዙ መቶ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ ከአንዱ ቅጂ ወደ ሌላው ቅጂ ሲገለበጥ ጥቃቅን ስህተቶች እንደተፈጠሩ የሚካድ አይደለም። ይሁንና ማስታወስ ያለብህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ ጥቃቅን ስህተቶች መግባታቸውን በመቀበልና ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ፈጠራ ነው ብሎ በመናገር መካከል ትልቅ ልዩነት ያለ መሆኑ ነው።

‘በቅዱሳን መጻሕፍት’ ላይ ያለህን እምነት ጠብቀህ ኑር

ስለ መጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንድናውቅ የረዱን ሐቀኛ ምሑራን ባለውለታዎቻችን ናቸው

ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ከመናገሩ በፊት ይህ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ጽሑፍ ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት ለጢሞቴዎስ ገልጾለት ነበር። “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ብሎት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) በጳውሎስ ዘመን እንደ ‘ጠቢባንና ሊቃውንት’ ይቆጠሩ የነበሩ ሰዎች ሌሎችን ለማታለልና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለማዳከም ‘የማግባቢያ’ ቃል መናገር ጀምረው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:18, 19፤ ቆላስይስ 2:4, 8) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ እነዚህ ሰዎች በሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንዳይሸነፍ ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ ከቅዱሳን መጻሕፍት በተማራቸው ነገሮች ጸንቶ እንዲቀጥል’ አሳስቦታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15

በእነዚህ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ አንተም እንዲህ ማድረግህ የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። በማታለል ረገድ በጣም የተዋጣላቸው ሰዎች የሚናገሩት ‘የማግባቢያ’ ሐሳብ ያለውን የማታለል ኃይል አቅልለህ አትመልከት። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ማለትም በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከአምላክ ቃል በተማርካቸው ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት በመጣል ራስህን ጠብቅ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለህን እምነት መገንባት የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መመሪያዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን ሲጠቅስ እነዚህ ሐሳቦች ከሳይንስ ጋር እንደሚስማሙ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው እርስ በርሱ እንደማይጋጭ እንዲሁም ትንቢቶቹ ዝንፍ ሳይሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙና ሌሎች በርካታ ማስረጃዎችን ሊያሳዩህ ዝግጁ ናቸው። እንዲህ ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ቅን ልብ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲያምኑ የረዳቸውን እውቀት ለማግኘት ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ።