በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

3. ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል

3. ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

3. ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል

ኤድዋርድ ጆን ኤር የተባለው አሳሽ፣ ነለቦር የተሰኘውን ምድረ በዳ ለማቋረጥ ባደረገው አስቸጋሪ ጉዞ ወቅት ከአሸዋ ክምርና ከባሕር ዛፍ ውስጥ ውኃ እንዴት ማውጣት እንደሚቻል በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ አቦሪጂኖች ተማረ። ኤር አካባቢውን በሚገባ ከሚያውቁት ሰዎች እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ በኋላ ላይ ሕይወቱን አትርፎለታል።

ከዚህ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው አንድን ከባድ ሥራ በተሳካ መንገድ ለመወጣት በአብዛኛው ይበልጥ ተሞክሮ ካላቸው ሰዎች እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ስታስብም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የሌላ ሰው እገዛ ሳያስፈልጋቸው መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንደሚችሉ አድርጎ አላሰበም። በአንድ ወቅት “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን [ከፍቶላቸው]” ነበር። (ሉቃስ 24:45) ኢየሱስ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች በውስጡ ያሉትን ትምህርቶች ለመረዳት እንዲችሉ ከሌሎች እርዳታ ማግኘት እንዳለባቸው ያውቅ ነበር።

ማን ሊረዳህ ይችላል?

ኢየሱስ ተከታዮቹ ለሰዎች እንዲህ ያለውን እርዳታ እንዲሰጡ አዟቸዋል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) የክርስቲያኖች ተቀዳሚ ሥራ ሰዎችን ማስተማርን ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማብራራትን ያካትታል። እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ ይረዳሉ።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከላይ ያለውን ትእዛዝ ከሰጠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ አስገራሚ ሁኔታ ተከሰተ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከኢትዮጵያ የመጣ አንድ የቤተ መንግሥት ባለሟል የኢሳይያስን ትንቢት እያነበበ እንደነበር ይናገራል። ሆኖም ይህ ሰው ከሚያነበው ትንቢት ውስጥ ያልገባው ነገር ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት ግልጽ ያልሆነለት የትንቢቱ ክፍል የሚከተለው ነው፦ “እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል ጠቦት እሱም አፉን አልከፈተም። ውርደት በደረሰበት ወቅት ፍትሕ ተነፈገ። ስለ ትውልዱ ማን በዝርዝር ሊናገር ይችላል? ምክንያቱም ሕይወቱ ከምድር ላይ ተወግዷል።”—የሐዋርያት ሥራ 8:32, 33፤ ኢሳይያስ 53:7, 8

ባለሥልጣኑም ጥሩ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት የነበረውን ክርስቲያኑን ፊልጶስን “ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው?” በማለት ጠየቀው። (የሐዋርያት ሥራ 8:34) ቅን ልብ ያለው ይህ ኢትዮጵያዊ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ የነበረ ሲሆን አመራር ለማግኘትም ሳይጸልይ አልቀረም። የኢሳይያስን ትንቢት ያነብ የነበረው በጉጉትና በቅን አስተሳሰብ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ የሚያነበውን ነገር መረዳት አስቸግሮት ነበር። ኢትዮጵያዊው ባለሥልጣን ፊልጶስን እንዲረዳው በትሕትና ጠየቀው። ፊልጶስ ስለ ትንቢቱ የሰጠው ማብራሪያ ልቡን ስለነካው ክርስቲያን ለመሆን ወሰነ።—የሐዋርያት ሥራ 8:35-39

በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ፊልጶስና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች ይሠሩት የነበረውን ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ከ235 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲያውቁ በፈቃደኝነት ይረዳሉ። ይህን ለማድረግ ቅዱሳን መጻሕፍትን ርዕስ በርዕስ ለማስጠናት በሚያስችላቸው ዘዴ ይጠቀማሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ደረጃ በደረጃ ለማጥናት የሚረዳው ይህ ዘዴ፣ አንድን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚሉ ለመመርመር ያስችላል። *—“ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ይቻላል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

‘ለጥያቄዎቼ ሁሉ መልስ አግኝቻለሁ’

በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ስቲቨን፣ ባልባኔራና ጆአን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ስቲቨን እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ወይም ዘገባዎችን በማነጻጸር ብቻ አብዛኛውን ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ እውነቱን በግልጽ ማወቅ የሚቻል መሆኑ በጣም አስገርሞኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ማንም ሰው ይህንን ዘዴ አላሳየኝም። የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት፣ አጥጋቢ መልስ በማይገኝላቸው ጥያቄዎችና እርስ በርስ በሚቃረኑ ሐሳቦች የተሞላ መሆን እንደማያስፈልገው ማወቄ ትልቅ እፎይታ አስገኝቶልኛል።”

ባልባኔራም በስቲቨን ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ትላለች፦ “የተማርኩት ነገር በሙሉ እርስ በርሱ የሚስማማና ምክንያታዊ ነው። የተማርኳቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን አምኜ የተቀበልኩት ‘ቤተ ክርስቲያኒቱ’ ስላለች ሳይሆን ለእያንዳንዱ ነገር አጥጋቢ ማብራሪያ ስለተሰጠኝ ነው።” ጆአንም እንዲህ ብላለች፦ “ለጥያቄዎቼ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ማግኘቴ ለአምላክ ከፍተኛ አክብሮት እንዲኖረኝ አድርጎኛል። አምላክ፣ ሰዎች ሊያነሷቸው ለሚችሉ ጥያቄዎች ሁሉ አስቀድሞ አጥጋቢ የሆኑ መልሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩ ማድረጉ በጣም የሚያስደንቅ ነው።”

የምታውቀው የይሖዋ ምሥክር አለ? ካለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያስችለው ይህ ዝግጅት እንዴት እንደሚከናወን እንዲያሳይህ ለምን አትጠይቀውም? የምታውቀው የይሖዋ ምሥክር ከሌለ ደግሞ በዚህ መጽሔት ገጽ 4 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች መካከል ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ። የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ካገኘህና አስተሳሰብህን ሰፋ አድርገህ የምታነብ ከሆነ እንዲሁም ብቃት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የሚሰጥህን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት አስቸጋሪ አይሆንብህም። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ብዙዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ርዕስ በርዕስ እንዲያጠኑ አስችሏቸዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ይቻላል

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በሚያስጠኑበት ጊዜ ከሚወያዩባቸው ርዕሶች ውስጥ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

• አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

• ሙታን የት ናቸው?

• የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው?

• አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?

• የቤተሰቤን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት . . . አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ ጸልይ፣ አስተሳሰብህን ሰፋ አድርገህ አንብበው እንዲሁም ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል