በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ይህ በእርግጥም እጅግ ቅዱስና ታላቅ የሆነው የአምላክ ስም ነው”

“ይህ በእርግጥም እጅግ ቅዱስና ታላቅ የሆነው የአምላክ ስም ነው”

 “ይህ በእርግጥም እጅግ ቅዱስና ታላቅ የሆነው የአምላክ ስም ነው”

ይህን ሐሳብ የተናገረው የኪዩሳው ኒኮላስ በመባል የሚታወቅ ሰው ሲሆን እንዲህ ያለው በ1430 ባቀረበው ስብከት ላይ ነበር። * ይህ ሰው ስለተለያዩ ነገሮች የማወቅ ፍላጎት የነበረው ሲሆን ካጠናቸው ትምህርቶች መካከል ግሪክኛን፣ ዕብራይስጥን፣ ፍልስፍናን፣ ሒሳብን እንዲሁም ሥነ መለኮትንና ሥነ ፈለክን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ኒኮላስ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸውን ሕጎች በማጥናት በ22 ዓመቱ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በ1448 ካርዲናል ሆኖ ተሹሟል።

ከ550 ዓመታት ገደማ በፊት የኪዩሳው ኒኮላስ፣ በኩስ ከተማ የአረጋውያን መጦሪያ ተቋም አቋቋመ፤ ኩስ በአሁኑ ጊዜ በርንካስትል ኩስ ተብላ የምትጠራ ሲሆን የምትገኘውም ጀርመን ውስጥ ከቦን ከተማ በስተደቡብ 130 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ መጦሪያ ተቋሙ በነበረበት ሕንፃ ውስጥ የኪዩሳ ቤተ መጻሕፍት ይገኛል፤ ቤተ መጻሕፍቱም ከ310 በላይ ጥንታዊ ጽሑፎችን ይዟል። ከእነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች አንዱ ኮዴክስ ኩሳኑስ 220 ሲሆን ይህ ጽሑፍ ኒኮላስ በ1430 ያቀረበውን ስብከት ይዟል። የኪዩሳው ኒኮላስ፣ ኢን ፕሪንሲፒዮ ኤራት ቬርበም (በመጀመሪያ ቃል ነበረ) በሚል ርዕስ ባቀረበው በዚህ ስብከት ላይ የይሖዋ ስም በላቲን የሚጠራበትን Iehoua (ኢኦዋ) የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። * በዚህ ጥንታዊ ጽሑፍ ገጽ 56 ላይ የአምላክን ስም በተመለከተ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰፍሯል:- “አምላክ ለራሱ ያወጣው ስም ነው። ቴትራግራማተንን ማለትም አራት ፊደላትን የያዘው ስም ነው፤ . . . ይህ በእርግጥም እጅግ ቅዱስና ታላቅ የሆነው የአምላክ ስም ነው።” የኪዩሳው ኒኮላስ የተናገረው ይህ ሐሳብ የአምላክ ስም በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ይስማማል።—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም

በ15ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የተዘጋጀው ይህ ኮዴክስ፣ ቴትራግራማተንን “ኢኦዋ” ብለው ከተረጎሟቸው በዛሬው ጊዜ ከሚገኙ እጅግ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ጽሑፍ፣ የአምላክን ስም “ይሖዋ” ከሚለው ስም ጋር በሚመሳሰሉ መጠሪያዎች መጻፍ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲሠራበት የቆየ በጣም የተለመደ አካሄድ እንደነበር የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የኪዩሳው ኒኮላስ ሌሎች መጠሪያዎችም ነበሩት፤ ኒኮላዎስ ክሪፍትስ (ክሬፕስ)፣ ኒኮላዎስ ኩሳኑስ እንዲሁም የኩስ ኒኮላዎስ ተብሎም ይጠራ ነበር። ኩስ የምትገኘው ጀርመን ውስጥ ሲሆን የኒኮላስ የትውልድ ከተማ ነች።

^ አን.3 ይህ ስብከት የሥላሴን ትምህርት የሚደግፍ ነበር።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኪዩሳ ቤተ መጻሕፍት