በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ “አማካሪዎች”

በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ “አማካሪዎች”

በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ “አማካሪዎች”

በዛሬው ጊዜ ኮምፒውተር የሚጠቀሙ ሰዎች ስለ ልጅ አስተዳደግ ለወላጆች የተሰጡ ምክሮችን ከኢንተርኔት ለማግኘት ቢፈልጉ ከ26 ሚሊዮን የሚበልጡ የማመሳከሪያ ጽሑፎችን ወዲያውኑ ማግኘት ይችላሉ። እያንዳንዱን ጽሑፍ ለማንበብ አንድ አንድ ደቂቃ ብትመድብ ሁሉንም አንብበህ ሳትጨርስ ልጅህ አድጎ ራሱን ችሎ ከቤት ሊወጣ ይችላል።

ታዲያ የሕፃናት ሐኪሞችና የሥነ ልቦና ጠበብት እንዲሁም ኢንተርኔት ባልነበሩበት ዘመን ወላጆች ምክር የሚያገኙት ከየት ነበር? በጥቅሉ ሲታይ ምክር የሚያገኙት ከዘመድ አዝማዶቻቸው ነበር። እናቶች፣ አባቶች፣ አክስቶችና አጎቶች ምክር ለመስጠት፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ልጆችን ለመጠበቅ ምንጊዜም ዝግጁዎች ነበሩ። ሆኖም በብዙ አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ መፍለሳቸው ይህ ዓይነቱ የጠበቀ የቤተሰብ ትስስር ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አድርጓል ለማለት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው እንደሚታየው እናቶችና አባቶች ልጆችን የማሳደጉን ከባድ ኃላፊነት ብቻቸውን ለመወጣት ተገደዋል።

በዘመናችን ልጆችን የመንከባከብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በፍጥነት እየጨመሩ የሄዱበት አንደኛው ምክንያት ይህ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ሌላው ምክንያት ደግሞ በሳይንስ ላይ ትምክህት የመጣሉ መንፈስ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው። በ1800ዎቹ ማገባደጃ ላይ አሜሪካውያን፣ ሳይንስ ማንኛውንም ዓይነት የኑሮ ዘርፍ ማሻሻል ይችላል የሚል እምነት አድሮባቸው ነበር። ልጆችን በማሳደግ ዘርፍም እርዳታ እንደሚሰጣቸው ተማምነው ነበር። የእናቶች ብሔራዊ ኮንግረስ በአሜሪካ የተባለው ድርጅት በ1899 ስለ “ወላጆች ችሎታ ማነስ” የተሰማውን ቅሬታ በይፋ በተናገረ ጊዜ “ሳይንሳዊ” ድጋፍ እንሰጣለን የሚሉ በርካታ አማካሪዎች ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ አማካሪዎች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚሉትን እናቶችና አባቶች ለመርዳት ቃል ገብተው ነበር።

ስለ ልጅ አስተዳደግ ከመጻሕፍት ምክር መፈለግ

ሆኖም እነዚህ አማካሪዎች ያበረከቱት ድርሻ ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ድሮ ከነበሩት ወላጆች ጋር ሲነጻጸሩ ጭንቀታቸው ቀንሷል? ያሉበትስ ሁኔታ ከቀድሞዎቹ የተሻለ ነው? በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ሁኔታው እንደዚያ አይደለም። ጥናቱ እንዳመለከተው ትንንሽ ልጆች ካሏቸው ወላጆች መካከል 35 በመቶ የሚያህሉት የሚተማመኑበት ምክር ለማግኘት ገና ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ኅሊናቸው የሚነግራቸውን ከማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል።

አን ኸልበርት የተባሉ አንዲት ሴት በአሜሪካን አገር ልጆችን ማሳደግ:- አማካሪዎች፣ ወላጆችና ስለ ልጆች የተሰጠ የአንድ ምዕተ ዓመት ምክር በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የልጅ አስተዳደግን በተመለከተ ቀደም ሲል የወጡ ሙያዊ ጽሑፎችን ይዘት ዳስሰዋል። የሁለት ልጆች እናት የሆኑት እኚህ ሴት እንደተናገሩት አማካሪዎቹ በጽሑፎቻቸው ላይ የሰጧቸው ብዙዎቹ ምክሮች ተጨባጭነት ባለው ሳይንሳዊ ምርምር ላይ የተመረኮዙ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ምክራቸው በአብዛኛው የተመረኮዘው በራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ ላይ ነው። ያለፈውን ጊዜ መለስ ብለን ስናስብ የጻፏቸው ነገሮች በአብዛኛው እርባና የሌላቸው፣ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከተለመደው አስተሳሰብ ወጣ ያሉ ይመስላሉ።

ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል? እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙ ሰዎች ስለ ልጅ አስተዳደግ የሚሰጧቸው ምክሮች፣ አስተያየቶችና የእርስ በርስ ሙግቶች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመብዛታቸው ግራ እየተጋቡ መጥተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚሰማቸው ሁሉም ወላጆች አይደሉም። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወላጆች በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስተማማኝ የምክር ምንጭ መሆኑን ካስመሰከረው ጥንታዊ የጥበብ ጎተራ እየተጠቀሙ ነው።