በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባሮክ የኤርምያስ ታማኝ ጸሐፊ

ባሮክ የኤርምያስ ታማኝ ጸሐፊ

ባሮክ የኤርምያስ ታማኝ ጸሐፊ

“የኔርያን ልጅ ባሮክን” ታውቀዋለህ? (ኤርምያስ 36:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአራት ምዕራፎች ላይ ብቻ የተጠቀሰ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዘንድ ግን የኤርምያስ ጸሐፊና የቅርብ ወዳጅ እንደሆነ ይታወቃል። ባሮክና ኤርምያስ፣ የይሁዳ መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ 18 ዓመታትም ሆነ ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት አሰቃቂ ጥፋት ባደረሱባት ወቅት ከዚያም ወደ ግብፅ በተሰደዱበት ጊዜ ሁሉ አብረው ነበሩ።

በቅርብ ዓመታት፣ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተዘጋጁና “የኔሪያሁ ልጅ [የኔርያ የዕብራይስጥ ስም] የሆነው የጸሐፊው የበረክያሁ [የባሮክ የዕብራይስጥ ስም]” የሚል ጽሕፈት የተቀረጸባቸው ሁለት የሸክላ ማኅተሞች a መገኘታቸው ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የዚህን ሰው ማንነት ለማወቅ እንዲነሳሱ አድርጓል። ባሮክ ማን ነበር? ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታ፣ የነበረው የትምህርት ደረጃና ሥልጣን ምን ይመስል ነበር? ከኤርምያስ ጎን ጸንቶ መቆሙስ ምን ያሳያል? ከባሮክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታሪክ የምናገኛቸውን መረጃዎች በመመርመር የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እንሞክር።

ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታና የነበረው ሥልጣን

ባሮክ በይሁዳ ከነበሩ ታዋቂ ጸሐፍት ቤተሰብ እንደተወለደ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ምሁራን ያምናሉ። እንዲህ ብለው ለመደምደም ምክንያት የሆኗቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ባሮክን “ጸሓፊው” በሚል ለየት ያለ የማዕረግ ስም ይጠራዋል። ከዚህም በላይ የባሮክ ወንድም ሠራያ በንጉሥ ሴዴቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን እንደነበረው ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ።—ኤርምያስ 36:32፤ 51:59

ፊሊፕ ኪንግ የተባሉ አርኪኦሎጂስት፣ በኤርምያስ ዘመን የነበሩትን ጸሐፍት በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መገባደጃና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መጀመሪያ ላይ፣ ባለሙያዎች የሆኑት ጸሐፍት በይሁዳ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። . . . ጸሐፍት የሚለው የማዕረግ ስም የሚሰጠው ለንጉሡ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ነበር።”

ከዚህም በተጨማሪ በዝርዝር እየተመለከትነው የምንሄደው ኤርምያስ ምዕራፍ 36፣ ባሮክ ከንጉሡ አማካሪዎች ጋር መገናኘት ይችል የነበረ ከመሆኑም በላይ የመመገቢያ አዳራሹንም ሆነ በዚያን ጊዜ መኮንን ወይም ባለ ሥልጣን የነበረውን የገማርያን ክፍል መጠቀም ይችል እንደነበረ ያሳያል። ይህን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጄምስ ሚዩለንበርግ እንዲህ ይላሉ:- “ባሮክ ወደ ጸሐፊው ክፍል የመግባት መብት የነበረው ከመሆኑም ሌላ ጥቅልሉን ጮክ ብሎ ባነበበበት ወሳኝ ወቅት ከተገኙት የንጉሡ ባለ ሥልጣናት ጋር እኩል ሥልጣን ነበረው። ባሮክ ከባለ ሥልጣናቱ መካከል አንዱ ነበር።”

ኮርፐስ ኦቭ ዌስት ሴሚቲክ ስታምፕ ሲልስ የተባለው መጽሐፍ ስለ ባሮክ እንዲህ በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል:- “የበረክያሁ የሸክላ ማኅተም የተገኘው በርከት ካሉ የሌሎች ባለ ሥልጣናት የሸክላ ማኅተሞች ጋር በመሆኑ ባሮክ/በረክያሁ ከሌሎቹ ባለ ሥልጣናት ጋር ተመሳሳይ ቦታ ነበረው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል።” ከላይ ያሉት መረጃዎች፣ ባሮክና ወንድሙ ሠራያ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታት ታማኙን ነቢይ ኤርምያስን ይደግፉ የነበሩ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት እንደሆኑ ያሳያሉ።

ኤርምያስን በይፋ መደገፍ

ባሮክ በታሪክ ቅደም ተከተል ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው በኤርምያስ ምዕራፍ 36 ላይ ሲሆን ይኸውም “ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት” ወይም በ625 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ መሆኑ ነው። በዚህ ወቅት ኤርምያስ በነቢይነት ማገልገል ከጀመረ 23 ዓመት ሆኖታል።—ኤርምያስ 25:1-3፤ 36:1, 4

ይሖዋ ኤርምያስን “የብራና ጥቅልል ውሰድ፤ . . . ከኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት አንሥቶ እስካሁን ድረስ ስለ እስራኤል፣ ስለ ይሁዳና ስለ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የነገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት” አለው። ዘገባው ቀጥሎም “ኤርምያስም የኔርያን ልጅ ባሮክን ጠራው፤ ባሮክም እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ተቀብሎ በብራናው ላይ ጻፈ” ይላል።—ኤርምያስ 36:2-4

ባሮክ የተጠራው ለምን ነበር? ኤርምያስ “እኔ ተከልክያለሁና ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግባት አልችልም” በማለት ነገረው። (ኤርምያስ 36:5) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ኤርምያስ ቀደም ብሎ ያነበባቸው መልእክቶች ባለ ሥልጣናቱን አስቆጥተዋቸው ሊሆን ስለሚችል የይሖዋ መልእክት በሚነበብበት የቤተ መቅደሱ አካባቢ እንዳይደርስ እገዳ ተጥሎበት ነበር። (ኤርምያስ 26:1-9) ባሮክ ታማኝ የይሖዋ አምላኪ እንደነበረ አያጠራጥርም። በመሆኑም “ነቢዩ ኤርምያስ የነገረውን ሁሉ” አድርጓል።—ኤርምያስ 36:8

ለ23 ዓመታት ሲነገሩ የነበሩትን ማስጠንቀቂያዎች መጻፍ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በላይ ኤርምያስ ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበቀ ሊሆን ይችላል። ይሁንና በኅዳር ወይም በታኅሣሥ 624 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሮክ “በብራና ላይ የተጻፈውን የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት . . . በገማርያ ክፍል ውስጥ ሆኖ ለሕዝቡ ሁሉ አነበበው።”—ኤርምያስ 36:8-10

የገማርያ ልጅ ሚክያስ የተከናወነውን ነገር ለአባቱና በርከት ላሉ መኳንንቶች ነገራቸው፤ እነርሱም ባሮክን ጠርተው ለሁለተኛ ጊዜ ጥቅልሉን ጮክ ብሎ እንዲያነብላቸው ጠየቁት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እነርሱም ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ እርስ በርሳቸው በፍርሀት በመተያየት ባሮክን፣ ‘ይህን ሁሉ ቃል ለንጉሡ መንገር ይገባናል’ አሉት፤ . . . ‘አንተና ኤርምያስ ሄዳችሁ ተሸሸጉ፤ የት እንዳላችሁም ማንም አይወቅ’ አሉት።”—ኤርምያስ 36:11-19

ንጉሥ ኢዮአቄም፣ ኤርምያስ በባሮክ ተጠቅሞ ያስጻፈውን ሲሰማ ጥቅልሉን በንዴት ቀዳዶ እሳት ውስጥ ጨመረው፤ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ኤርምያስንና ባሮክን እንዲይዟቸው አዘዛቸው። በይሖዋ ትእዛዝ መሠረት ኤርምያስና ባሮክ ተደብቀው በበፊቱ ጥቅልል ላይ የነበረውን ሐሳብ በድጋሚ ጻፉት።—ኤርምያስ 36:21-32

ባሮክ የተሰጠው ኃላፊነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ሳያውቅ አልቀረም። ከጥቂት ዓመታት በፊት በኤርምያስ ላይ የተሰነዘረውን ዛቻ አውቆ መሆን አለበት። “እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ” ትንቢት ይናገር የነበረው ኦርዮ የደረሰበትን ማለትም በንጉሥ ኢዮአቄም መገደሉን ሳይሰማ አልቀረም። እንደዛም ሆኖ ባሮክ የነበረውን ሙያና ከንጉሥ ባለ ሥልጣናት ጋር ያለውን ግንኙነት ኤርምያስን ለመደገፍ ተጠቅሞበታል።—ኤርምያስ 26:1-9, 20-24 የ1954 ትርጉም

“ታላቅ ነገር” አትፈልግ

ባሮክ የመጀመሪያውን ጥቅልል በጻፈበት ወቅት ከመጨነቁ የተነሳ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ሐዘን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ፤ ከልቅሶዬ ብዛት የተነሣ ደክሜያለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም።” ሆኖም የጭንቀቱ መንስዔ ምን ነበር?—ኤርምያስ 45:1-3

ይህን በተመለከተ ቀጥተኛ መልስ አናገኝም። ሆኖም ባሮክ የነበረበትን ሁኔታ በአእምሮህ ለመሳል ሞክር። ባሮክ፣ ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ ለ23 ዓመታት ሲሰጥ የቆየውን ማስጠንቀቂያ እንደገና ሲናገር ሕዝቡ ከሃዲ መሆኑና ይሖዋን አንፈልግም ማለቱ ይበልጥ ግልጽ ሳይሆንለት አልቀረም። ይሖዋ ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን አጥፍቶ ሕዝቡ ለ70 ዓመታት በግዞት ወደ ባቢሎን እንደሚወሰድ የተናገረው በዚያው ዓመት ሲሆን ምናልባትም ይህ ሐሳብ በጥቅልሉ ላይ ሰፍሮ ይሆናል፤ ይህም ባሮክን አስጨንቆት መሆን አለበት። (ኤርምያስ 25:1-11) ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ኤርምያስን ጸንቶ መደገፉ ሥልጣኑንና ሥራውን ሊያሳጣው ይችላል።

ያም ሆነ ይህ፣ ይሖዋ ራሱ ጣልቃ በመግባት ባሮክ ስለ መጪው ፍርድ እንዲያስታውስ ረድቶታል። ይሖዋ “በምድር ሁሉ የገነባሁትን አፈርሳለሁ፤ የተከልሁትን እነቅላለሁ” ሲል ነግሮታል። ከዚያም በመቀጠል “ታዲያ፣ ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? . . . አትፈልገው” በማለት ባሮክን መክሮታል።—ኤርምያስ 45:4, 5

ይሖዋ “ታላቅ ነገር” ብሎ የጠራው ምን እንደሆነ ለይቶ ባይነግረውም ይህ ነገር የራስ ወዳድነት ምኞት አሊያም ታዋቂ ለመሆን ወይም ቁሳዊ ብልጽግና ለማግኘት መፈለግ ሊሆን እንደሚችል ባሮክ ሳይገባው አይቀርም። ይሖዋ፣ ባሮክ ሐቁን እንዲቀበልና ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው እንዲገነዘብ ለማድረግ እንዲህ በማለት መክሮታል:- “በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥፋት አመጣለሁና . . . ነገር ግን በሄድህበት ሁሉ ሕይወትህ እንዲተርፍልህ አደርጋለሁ።” ባሮክ የትም ቢሄድ ውድ የሆነው ንብረቱ ማለትም ሕይወቱ ይተርፍለታል።—ኤርምያስ 45:5

ከ625 እስከ 624 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑትን እነዚህን ነገሮች ከሚገልጹት በኤርምያስ ምዕራፍ 36 እና 45 ላይ ከተመዘገቡት ሁኔታዎች በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባሮክ እንደገና የሚናገረው በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌምና ይሁዳ በባቢሎናውያን ከመጥፋታቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው። ታዲያ በዚያ ወቅት ምን ተፈጸመ?

ባሮክ በድጋሚ ከኤርምያስ ጎን ቆመ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ ባሮክ በድጋሚ የተገለጸው ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በከበቡበት ወቅት ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቡ ተመልሰው እንደሚቋቋሙ የሚያሳይ ምልክት እንዲሆን ሲል ኤርምያስ ከአጎቱ ልጅ በዓናቶት ያለውን መሬት እንዲገዛ በነገረው ጊዜ ኤርምያስ “በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተዘግቶበት ነበር።” በመሆኑም ሕጋዊ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲረዳው ባሮክን ጠራው።—ኤርምያስ 32:1, 2, 6, 7

ኤርምያስም እንዲህ በማለት ይናገራል:- “በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ [“ጻፍሁ፣” የ1879 ትርጉም]፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት። . . . የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤ . . . ለባሮክ ሰጠሁት።” ከዚያም የውሉ ሰነዶች ሳይበላሹ እንዲቆዩ በሸክላ ዕቃ ውስጥ እንዲያኖራቸው ባሮክን አዘዘው። አንዳንድ ምሁራን ኤርምያስ ውሉ ላይ ‘መጻፉን’ ሲናገር፣ ሁልጊዜ ይጽፍለት የነበረው የሠለጠነው ጸሐፊ ባሮክ እንዲጽፍለት ማድረጉን መግለጹ ይሆናል ብለው ያምናሉ።—ኤርምያስ 32:10-14፤ 36:4, 17, 18፤ 45:1

ባሮክና ኤርምያስ በወቅቱ የነበረውን ሕጋዊ አሠራር በመከተል የውሉን ሰነድ በሁለት ቅጂዎች አዘጋጁ። ኮርፐስ ኦቭ ዌስት ሴሚቲክ ስታምፕ ሲልስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “የመጀመሪያው የግዢ ውል ተጠቅልሎ በሸክላ መታተሙ ‘የታሸገ ሰነድ’ ተብሎ እንዲጠራ ያደረገው ሲሆን ይህ የውሉ ኦሪጂናል ቅጂ ነው። . . . ሁለተኛው ‘ያልታሸገ ሰነድ’ ደግሞ የታሸገውና ግዴታ ውስጥ የሚያስገባው ሰነድ ግልባጭ ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሚመለከቱት ይኼኛውን ሰነድ ነው። በመሆኑም በሁለት የፓፒረስ ወረቀቶች ላይ የተጻፉ ሁለት የተለያዩ ጽሑፎች ማለትም ዋናው እና ግልባጭ ሰነዶች ነበሩ።” እንደነዚህ ዓይነት ሰነዶችን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ማኖር የተለመደ እንደነበረ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ያረጋግጣሉ።

በመጨረሻም ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ከያዟት በኋላ አቃጠሏት፤ ከጥቂት ድሆች በስተቀር ሕዝቡን ሁሉ ማረኩ። ናቡከደነፆር ጎዶልያስን ገዢ አድርጎ የሾመው ሲሆን ይህ ሰው ከሁለት ወራት በኋላ በአይሁዳውያን ተገደለ። የቀሩት አይሁዳውያን ኤርምያስ በመንፈስ ተነሳስቶ የሰጣቸውን ምክር ችላ በማለት በተቃራኒ ወደ ግብጽ ለመሸሽ እቅድ አወጡ፤ ባሮክ በድጋሚ የተጠቀሰው እዚህ ቦታ ላይ ነው።—ኤርምያስ 39:2, 8፤ 40:5፤ 41:1, 2፤ 42:13-17

የአይሁድ መሪዎች “ትዋሻለህ! አምላካችን እግዚአብሔር፣ ‘እዚያ ለመኖር ወደ ግብፅ አትሂዱ ብለህ ንገራቸው’ ብሎ አልላከህም፤ ነገር ግን ባቢሎናውያን እንዲገድሉን ወይም ማርከው ወደ ባቢሎን እንዲወስዱን ለእነርሱ አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ የኔርያ ልጅ ባሮክ በእኛ ላይ አነሣሥቶሃል” ብለው ኤርምያስን ወቀሱት። (ኤርምያስ 43:2, 3) የአይሁድ መሪዎች ያቀረቡት ክስ ባሮክ በኤርምያስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል የሚል እምነት እንደነበራቸው ያሳያል። እንዲህ ብለው እንዲያምኑ ያደረጋቸው ባሮክ ሥልጣን ስላለው ወይም ከኤርምያስ ጋር የቆየ ወዳጅነት ስለነበረው የነቢዩ ጸሐፊ ከመሆን ያለፈ ነገር ያደርጋል ብለው ማሰባቸው ይሆን? እንደዚያ አስበው ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ የአይሁድ መሪዎች ያሰቡት ምንም ይሁን ምን መልእክቱ የመጣው ከይሖዋ ነበር።

መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተው የነበረ ቢሆንም የቀሩት አይሁዳውያን “ነቢዩ ኤርምያስንና የኔርያን ልጅ ባሮክን” ከእነርሱ ጋር ወሰዷቸው። ኤርምያስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “የእግዚአብሔርንም ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብፅ ገቡ፤ ዘልቀውም እስከ ጣፍናስ ድረስ ሄዱ።” ጣፍናስ፣ የናይል ወንዝ ከባሕር ጋር በሚገናኝበት አካባቢ ባለው ደለላማ መሬት ላይ በምሥራቅ በኩል የምትገኝና ከሲና ጋር የምትዋሰን የጠረፍ ከተማ ነች። ከዚህ በኋላ ባሮክ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ አልተጠቀሰም።—ኤርምያስ 43:5-7

ከባሮክ ምን ልንማር እንችላለን?

ከባሮክ ልንማር የምንችላቸው በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶች አሉ። ጎላ ብሎ የሚታየው አንደኛው ትምህርት፣ ባሮክ ሙያውንና ከባለ ሥልጣናት ጋር የነበረውን ግንኙነት ተጠቅሞ ይሖዋን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኑ ነው። እንዲህ ማድረጉ ሊያስከትልበት የሚችለውን መዘዝ በመፍራት ወደኋላ አላለም። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ወንዶችና ሴቶች የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ችሎታ ለቤቴል አገልግሎት፣ ለግንባታ ሥራና ለመሳሰሉት ተግባሮች በማዋል የባሮክ ዓይነት መንፈስ እያሳዩ ነው። አንተስ ይህን ዓይነቱን መንፈስ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

ይሁዳ ልትጠፋ አካባቢ ባሮክ ለራሱ “ታላቅ ነገር” የሚፈልግበት ጊዜ እንዳልሆነ በተነገረው ጊዜ ምክሩን በታዛዥነት ተቀብሎ መሆን አለበት፤ እንዲህ እንድንል ምክንያት የሚሆነን ሕይወቱ መትረፉ ነው። እኛም ዛሬ በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ጊዜ ውስጥ ስለምንገኝ ይህንን ምክር በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን ምክንያታዊ ነው። ይሖዋም በተመሳሳይ ሕይወታችንን እንደሚያተርፍልን ቃል ገብቶልናል። ታዲያ እኛስ ባሮክ እንዳደረገው እንዲህ ላሉት ማሳሰቢያዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንችላለን?

ከዚህ ታሪክ ልንማረው የሚገባን ሌላም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ትምህርት አለ። ኤርምያስ ከአጎቱ ልጅ ጋር ዘመዳሞች ቢሆኑም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ሕጋዊ ሥርዓቶችን እንዲከተሉ ባሮክ ረድቷቸዋል። ይህ ደግሞ፣ ክርስቲያኖች ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ለሚያደርጓቸው የንግድ ግንኙነቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። በመሆኑም የንግድ ግንኙነቶችን በጽሑፍ ማስፈሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ፣ ጠቃሚና ደግነት የሚንጸባረቅበት ተግባር ነው።

ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ባሮክ እምብዛም ያልተገለጸ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ልብ ሊሉት የሚገባ ምሳሌ ትቷል። አንተስ የኤርምያስ ታማኝ ጸሐፊ የነበረውን የባሮክን ግሩም ምሳሌ ትኮርጃለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሸክላ ማኅተም አንድ አስፈላጊ ሰነድ የታሰረበትን ገመድ ለማጣበቅ ያገለግላል። በሸክላው ላይ የባለቤቱን ወይም የላኪውን ማንነት የሚያመለክት ማኅተም ይቀረጽበት ነበር።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የባሮክ የሸክላ ማኅተም

[ምንጭ]

የሸክላ ማኅተም:- Courtesy of Israel Museum, Jerusalem