ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰው የሚፈለገው ፍቅራዊ ደግነት ነው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 19:22 NW ) በእርግጥም ከፍቅር የመነጨ የደግነት ድርጊት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው ሐረግ ቀደም ሲል የነበረውን ዝምድና ለማጠናከር ተብሎ የሚደረግ የደግነት ተግባርን የሚያመለክት ሲሆን ዝምድናው አንደኛው ወገን ከዚህ በፊት ባሳየው የደግነት ተግባር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ፍቅራዊ ደግነት ታማኝነትንም ያመለክታል።

የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮአስ ይህንን አስፈላጊ ባሕርይ ሳያሳይ ቀርቷል። አክስቱና ባልዋ ዮዳሄ ትልቅ ውለታ ውለውለት ነበር። ኢዮአስ ገና ዓመት ያልሞላው ጨቅላ ሕፃን በነበረበት ወቅት ክፉ ሴት የነበረችው አያቱ ራስዋን ንግሥት ካደረገች በኋላ የዙፋኑ ወራሽ የሚሆኑትን የኢዮአስ ወንድሞች በሙሉ አስገደለቻቸው። ኢዮአስ ግን አክስቱና ባልዋ ስለደበቁት በሕይወት ሊተርፍ ቻለ። ከዚያም የአምላክን ሕግ እያስተማሩ አሳደጉት። ኢዮአስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ የሊቀ ካህንነት ሥልጣኑን በመጠቀም ክፉዋን ንግሥት አስወገደና ኢዮአስን አነገሠው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 22:10 እስከ 23:15

ወጣቱ ኢዮአስ ዮዳሄ በሕይወት ሳለ መልካም ንጉሥ ሆኖ ቢያስተዳድርም ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር አለ። አምላክ የዮዳሄን ልጅ ዘካርያስን በመላክ ከክህደት ጎዳናው እንዲመለስ አስጠነቀቀው። ኢዮአስ ግን ዘካርያስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል አደረገ። ኢዮአስ ትልቅ ውለታ ለዋለለት ቤተሰብ ታማኝ ሳይሆን ቀርቷል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 24:17-21

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW ] አላሰበም፣ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው” ይላል። ዘካርያስ ሊሞት ሲል “እግዚአብሔር ይየው፣ ይፈልገውም” ብሎ ነበር። የዘካርያስ ቃላት በከንቱ አልቀሩም፤ ኢዮአስ በጠና የታመመ ሲሆን በኋላም የገዛ አገልጋዮቹ ገደሉት።​—⁠2 ዜና መዋዕል 24:17-25

እንደ ንጉሥ ኢዮአስ ውለታ ቢስ ከመሆን ይልቅ ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የሚከተሉ ሁሉ አስደሳች የወደፊት ሕይወት ይኖራቸዋል:- “ምሕረትና [“ፍቅራዊ ደግነትና፣” NW ] እውነት ከአንተ አይራቁ፤ . . . በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስን . . . ታገኛለህ።”​—⁠ምሳሌ 3:3, 4