በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ቻይና

ቤጂንግ ውስጥ በ2013 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የተመዘገበው የፍቺ ቁጥር በ2012 በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከነበረው ጋር ሲወዳደር 41 በመቶ አሻቅቧል። ይህ የሆነበት ምክንያት ባለትዳሮች በቅርቡ በቤት ሽያጭ ትርፍ ላይ የተጣለውን የ20 በመቶ ግብር ለመሸሽ ስለፈለጉ እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ። በዚህ አሠራር መሠረት፣ ፍቺ ፈጽመው ሁለተኛ ቤታቸውን የሚሸጡ ባልና ሚስቶች ከዚህ ግብር ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ።

ዓለም

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል ብዙዎች ነፍሳትን መብላት ቢለምዱ ጥሩ እንደሚሆን ሐሳብ አቅርቧል። በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ለምግብነት የሚውሉ ነፍሳት ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ በመሆናቸውና ሰዎች በማይመገቧቸው ነገሮች ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች እንድናገኝ ስለሚያስችሉን “የሥጋ ምትክ በመሆን ረገድ ጥሩ አማራጭ” ናቸው። ይሁን እንጂ “በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድ [ነፍሳትን] መመገብ እንደ አስጸያፊ ነገር” እንደሚቆጠር አክሎ ገልጿል።

ካናዳ

የሥነ ተዋልዶ ጤና ክሊኒኮች ከሕግና ከሥነ ምግባር አንጻር አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል፤ ምክንያቱም በበረዶ ቤት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ፅንሶች “ባለቤቶቻቸው” እነማን እንደሆኑ ማወቅ ስላልተቻለ ክሊኒኮቹ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ግራ ገብቷቸዋል። በአንድ ክሊኒክ ውስጥ ብቻ፣ በብልቃጥ ውስጥ ፅንስ እንዲፈጠርላቸው ጠይቀው ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ተመልሰው ያልመጡ ወይም “የጠፉ” ሰዎች ንብረት የሆኑ 1,000 ፅንሶች አሉ።

አየርላንድ

በአየርላንድ የሚኖሩ ካቶሊኮች ከዚህ በፊት ጋብቻቸውን በሃይማኖታዊ ወይም በመንግሥታዊ ተቋማት ከመፈጸም አንዱን መምረጥ ነበረባቸው፤ በ2013 ግን ከሃይማኖት ይልቅ በሰብዓዊ ጥበብ መመራትን የሚደግፉ (ሂዩማኒስት) ቡድኖች ሃይማኖታዊ ያልሆነ ጋብቻ ማስፈጸም ጀመሩ። ሮይተርስ የዜና አገልግሎት እንደገለጸው “በመንግሥት ተቋማት ከሚደረገው የምዝገባ ሥርዓት ያለፈ ነገር ማድረግ የሚፈልጉ ሆኖም ሃይማኖታዊ ሥርዓት የማይፈልጉ ሰዎች ምርጫ ታፍኖ በመቆየቱ” ይህን አዲስ አማራጭ የሚያቀርቡ ድርጅቶች በወረፋ ተጨናንቀዋል።