በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አልፐንሆርን—ከግንድ የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ

አልፐንሆርን—ከግንድ የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ

አልፐንሆርን—ከግንድ የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ

በስዊዝ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች መልእክት ለመለዋወጥ ለብዙ መቶ ዘመናት አልፐንሆርን የሚባል ልዩ መሣሪያ ሲጠቀሙ ኖረዋል። የአንዳንድ አልፐንሆርኖች ቁመት በመሣሪያዎቹ ከሚጫወቱት ሰዎች ሁለት እጥፍ ስለሚበልጥ ለአያያዝ አመቺ አይመስሉም። ይሁን እንጂ አልፐንሆርን በእጅ ሊያዝ የሚችል መሣሪያ ነው። አንዳንድ የአልፐንሆርን ዓይነቶች ተነቃቅለው አመቺ በሆነ መያዣ ውስጥ ሊቀመጡ ይችላሉ። ከአልፐንሆርን የሚወጣው ድምፅ የአልፕስ ተራሮችን አቋርጦ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስካሉት ሸለቋማ አካባቢዎች ድረስ ጥርት ብሎ ሊሰማ ይችላል!

አልፐንሆርን የሚሠራበት መንገድ

አልፐንሆርን የሚሠራው ስፕሩስ ከሚባል የጥድ ዝርያ ሲሆን ይህን ዛፍ ውብ በሆኑት የስዊዝ ተራሮች ላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በአካባቢው ያለው የአየር ጠባይና የቦታ አቀማመጥ አቀበታማ በሆኑ ቦታዎች የሚበቅሉትን እነዚህን የስፕሩስ ዛፎች ከታች በኩል ቆልመም ብለው እንዲያድጉ ያስገድዳቸዋል።

አንድ ሰው አልፐንሆርን ለመሥራት የሚያገለግል ተስማሚ ዛፍ ከመረጠ በኋላ ግንዱን መሃል ለመሃል በጥንቃቄ ለሁለት ይሰነጥቀዋል፤ ከዚያም የተሰነጠቀውን ግንድ ልዩ በሆነ መሮ ይቦረቡረዋል። ይህ ሥራ ብቻ 80 ሰዓት ሊፈጅ ይችላል! ባለሙያው የግንዱን ውስጠኛ ክፍል በብርጭቆ ወረቀት እያሸ በደንብ ያለሰልሰዋል። ከዚያም ተቦርቡረው የለሰለሱትን ሁለቱን ክፍሎች በሙጫ ያጣብቃቸውና ዙሪያውን በበርች ዛፍ ልጥ ጥብቅ አድርጎ ያስረዋል። በተጨማሪም አልፐንሆርኑን በሚጫወቱበት ወቅት ከታች ድጋፍ የሚሆን እንጨት ጫፉ ላይ ያጣብቅበታል። በመጨረሻም ለአልፐንሆርኑ ተስማሚ የሆነ መንፊያ ይገጥምለታል እንዲሁም ድምፅ በሚወጣበት በኩል ባለው የመሣሪያው ክፍል ላይ ቅርጽ በማውጣት ወይም ሥዕል በመሳል በሚገባ ያሳምረዋል፤ ከዚያም በተለያዩ ነገሮች ለብልሽት እንዳይዳረግ ቫርኒሽ ይቀባዋል።

በጥንት ዘመን ይሰጥ የነበረው አገልግሎት

በጥንት ጊዜ የበግ እረኞችና ከብት ጠባቂዎች በተራራው አናት ላይ ካለው መስክ ላይ ሆነው አልፐንሆርንን በመንፋት “ሁሉም ነገር ሰላም ነው” የሚል መልእክት በሸለቆው ውስጥ ለሚኖሩት ቤተሰቦቻቸው ያስተላልፉ ነበር። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ይህን መሣሪያ የሚጠቀሙት ወተት ለማለብ ሲፈልጉ ላሞቻቸውን ለመጥራት ነበር። የስዊዝ የወተት ላም አርቢዎች፣ ላሞች በሚታለቡበት ወቅት ዘና የሚያደርገውን የአልፐንሆርን ድምፅ የሚሰሙ ከሆነ ተረጋግተው ይቆማሉ የሚል የቆየ እምነት ነበራቸው።

ብዙ ከብት ጠባቂዎች፣ ላሞች ከበረታቸው በማይወጡባቸው የክረምት ወራት አልፐንሆርናቸውን ይዘው ወደ ከተማ በመሄድ ሰዎችን ያዝናናሉ፤ ይህም ኑሯቸውን ለመደጎም የሚያስችል ተጨማሪ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል። በጥንት ዘመን አልፐንሆርን ለጦርነት የክተት ጥሪ ለማሰማትም ያገለግል እንደነበር ታሪክ ይናገራል።

አልፐንሆርን መጫወት የሚቻለው እንዴት ነው?

ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር እንደሚባለው አልፐንሆርንም በሰው እጅ ሲያዩት ለመጫወት ቀላል ይመስላል። ምክንያቱም አልፐንሆርን የድምፅ አወጣጡን ለመቆጣጠር የሚረዱ ቀዳዳዎችም ሆኑ የሚነካኩ ቁልፎች የሉትም። ይሁንና በቱቦው ውስጥ የሚያልፈውን አየር ተቆጣጥሮ የሚፈለገውን ዓይነት ድምፅ ማውጣት በጣም ከባድ ነው።

አልፐንሆርን የተባሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች ማውጣት የሚችሉት 12 ዓይነት የተለያዩ ድምፆችን ብቻ ነው። ሁሉንም ቅኝቶች በዚህ መሣሪያ መጫወት ባይቻልም ለዚህ መሣሪያ የሚሆኑ የተለዩ ቅኝቶችን በማዘጋጀት አንድ የተዋጣለት ተጫዋች ስሜት ቀስቃሽ በሆነ መንገድ እንዲጫወታቸው ማድረግ ይቻላል።

ዝነኛ የሙዚቃ አቀናባሪዎች በኦርኬስትራ መልክ በሚቀርቡ ሥራዎቻቸው ላይ የአልፐንሆርን ድምፅ እንዲካተት አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የዎልፍጋንግ አማዲዩስ ሞዛርት አባት የሆነው ሌኦፖልድ ሞዛርት “ሲንፎኒያ ፓስቶሬላ” የተሰኘውን ዜማ የጻፈው በኦርኬስትራ እና ኮርኖ ፓስቶሪቲዮ በተባለው እንደ አልፐንሆርን ባለ መሣሪያ ተጠቅሞ ለመጫወት በሚመች መንገድ ነው። ብራሃምስ ደግሞ ዋሽንትና መለከት በመጠቀም ከስዊዝ አልፐንሆርን ጋር የሚመሳሰል ድምፅ መፍጠር የቻለ ሲሆን ቤትሆቨንም ፓስቶራል በተባለው የሙዚቃ ቅንብሩ ላይ የገጠርን ሕይወት ትዝታ ለመቀስቀስ ሲል የአልፐንሆርንን ድምፅ አስመስሎ ተጫውቷል።

አልፐንሆርን ስዊዘርላንድ ውስጥ በጽሑፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በስም የተጠቀሰው በ1527 የቅዱስ ኧርባን ገዳም ንብረት በሆነ አንድ የሒሳብ መዝገብ ላይ ነው። ዛሬም ወደ 500 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳ ለስለስ ያለውን የአልፐንሆርን ድምፅ ግርማ ሞገስ በተላበሱት የስዊዝ ተራሮች አናት ላይ ባሉ አረንጓዴ መስኮች ላይ ሲያስተጋባ መስማት የተለመደ ነው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልፐንሆርንን ነቃቅሎ በእጅ መያዝ ይቻላል