በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

ገንዘብህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

ገንዘብህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ሦስት ዓይነት አማራጮች አሉ። እነዚህም (1) መጠቀም፣ (2) ማጠራቀም ወይም (3) መስጠት ናቸው። በመጀመሪያ ገንዘብን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል እንመልከት።

ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት ጥሩ ዕቅድ የተደረገበት በጀት አውጥቶ የመኖርን አስፈላጊነት በግልጽ አሳይቷል። በጀት ሲባል ምን ማለት ነው? በቀላል አነጋገር አንድ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ የንግድ ተቋም ወይም መንግሥት ገቢውን እንዴት እንደሚጠቀምበት አስቀድሞ የሚያወጣው ግምታዊ ስሌት ነው።

የቤተሰብ በጀት

በጀት ማውጣት የምትችለው እንዴት ነው? በዴኒስ ቻምበርስ የተዘጋጀው በጀቲንግ የተባለው መጽሐፍ “በጀቱ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በጀት በማውጣቱ ሥራ መሳተፍ አለባቸው” ብሏል። የቤተሰቡ አባላት በጀቱ በታቀደው መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ አልፎ አልፎ በጀቱን መገምገም አለባቸው። ጥሩ በጀት ማውጣት የሚክስ የቤተሰብ ፕሮጀክት ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ከቤተሰቡ ገቢ ጋር የሚጣጣም ሕይወት ለመምራት ጥረት እንዲያደርግ ያነሳሳዋል።

አንዳንድ ሰዎች በጀት ለማውጣት በኮምፒውተር ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ አንድ ወረቀት ላይ መሐል ለመሐል በማስመር በአንደኛው ረድፍ ገቢዎቻቸውን፣ በሁለተኛው ረድፍ ደግሞ ወጪዎቻቸውን ይመዘግባሉ። በተጨማሪም ለእረፍት ጊዜ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ጨምሮ ግብር እንደ መክፈል ያሉ ዓመታዊ ወጪዎችን በወርሃዊው በጀት ውስጥ ማካተት አስፈላጊ ነው።

ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ የተገኘው በጀት የማውጣት ዘዴ “ምግብ፣” “ኪራይ፣” “ትራንስፖርት፣” “ኤሌክትሪክ፣” “ሕክምና” ወዘተ የሚሉ ርዕሶች የተጻፉባቸው ፖስታዎች ወይም ፋይሎች መጠቀም ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች ከላይ ለተዘረዘሩት ወጪዎች የሚሆን ወርሃዊ ገንዘብ በተለያዩ ፖስታዎች ውስጥ ያስቀምጡ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን፣ ብዙ ሰዎች ገንዘብን በባንክ አስቀምጦ በሚያስፈልግበት ጊዜ ብቻ በማውጣት መጠቀም ቀላልና አስተማማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ሁለት ሴት ልጆች ያሏቸውና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ጆናታንና አን ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙት በፋይል በጀትን የመከፋፈል ዘዴ ነው። ጆናታን እንዲህ ብሏል፦ “ደሞዛችሁ በቀጥታ ወደ ባንክ የሚገባ ከሆነ ልዩ ልዩ ወጪዎቻችሁን ለመሸፈን ከባንክ በምታወጡት ገንዘብ ረገድም ጥብቅ መሆናችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ለሥጋ የመደባችሁት ወርሃዊ ወጪ ካለቀባችሁ ተጨማሪ ሥጋ ለመግዛት ስትሉ ተቀማጭ ለማድረግ ከወሰናችሁት ገንዘብ ላይ መውሰድ አይገባችሁም።”

ጆናታን የራሱ ንግድ የነበረው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እሱና ቤተሰቡ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች በመሆን የአምልኮ ቦታዎችን በመገንባት ሥራ እየተካፈሉ ይገኛሉ። በዚህ ሥራ መቀጠል ስለሚፈልጉም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በበጀት መኖር አስፈልጓቸዋል። መላው ቤተሰብ በጀቱ በታቀደው መሠረት ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥና አንዳንድ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ በየጊዜው ይወያያል።

ከሁሉ የላቀ ደስታ

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ያሉንን ነገሮች ማለትም ጊዜን፣ ጉልበትን እንዲሁም ካለን ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለሌሎች መስጠት የላቀ ደስታ ያስገኛል። አቅምህ የሚፈቅደውን ያህል እንዲህ ማድረግህ ገንዘብህን ከምትጠቀምባቸው ሦስት አማራጮች መካከል የተሻለው ነው።

ክሪስ ፋረል ዘ ኒው ፍሩጋሊቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ‘በገንዘብ ለመጠቀም ገንዘብ ቆጥቦ ማስቀመጥ ያስፈልጋል’ ብለዋል። አክለውም “ገንዘብህን መጠቀም ከምትችልባቸው አማራጮች ሁሉ እጅግ ጠቃሚውና ከሁሉ የተሻለው ለሌሎች መስጠት ነው” ብለዋል። * ፋረል በመቀጠል እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “‘ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?’ ብለህ ስታስብ አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብና ንብረት ሳይሆን ከሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት፣ ጥሩ ትዝታዎችህና ለሌሎች ጠቃሚ ነገር ስታከናውን የሚሰማህ ስሜት ሆኖ ታገኘዋለህ።”

ማይክል ዋግነር የተባሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ወጣቶች ቆጣቢ እንዲሆኑ ለማበረታታት ብለው በጻፉት ዩር መኒ፣ ደይ ዋን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ችግረኛ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ስትነሳሱ፣ ያሳያችሁት ደግነትና ልግስና የተለያዩ መልካም ምላሾችን ያስገኝላችኋል። ከሁሉም በላይ የሚያስደስታችሁ ግን አንድን ሰው በመርዳታችሁ የሚሰማችሁ ስሜት ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ይናገራል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ያሉህን ነገሮች በጥበብ እንድትጠቀም የሚረዱህ ሐሳቦችን ይዟል። አሁን ደግሞ ጥበብ ካዘሉት ከእነዚህ ሐሳቦች መካከል ሰባቱን እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ገንዘባችንን፣ ለሌሎች ስጦታ ገዝቶ በመስጠት ወይም ደግሞ ወዳጅ ዘመዶቻችንን በመጋበዝ ልንጠቀምበት እንችላለን።