በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓሣ ማጥመድ፣ በአእዋፍ ዓለም

ዓሣ ማጥመድ፣ በአእዋፍ ዓለም

ዓሣ ማጥመድ፣ በአእዋፍ ዓለም

ሰዎችም ሆኑ ወፎች ዓሣ ለማጥመድ ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን ማከናወን ይኖርባቸዋል፤ እነዚህም (1) ዓሣውን ማግኘት፣ (2) ወደ ዓሣው መቅረብ እና (3) ዓሣውን መያዝ ናቸው።

የጥንት ግብፃውያን ዓሣ ለማጥመድ ይጠቀሙበት የነበረው ዓይነተኛው ዘዴ ዓሣውን በጦር መውጋት ነበር። እነዚህ ዓሣ አጥማጆች ይህን ዘዴ ተግባራዊ ከማድረጋቸው ከብዙ ዘመናት በፊት ሽመላ የተባለው ወፍ ዝርያዎች ይህን የመሰለ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር።

በግብፅ በናይል ደለል አካባቢ በብዛት የሚገኘው ግራጫ ሽመላ እንደ ጦር ሹል በሆነው መንቆሩ ዓሦችን ወግቶ ይይዛል። ይህ ወፍ በአንድ ጊዜ ሁለት ዓሦችን ወግቶ መያዝ የሚችል ሲሆን በቀን ከግማሽ ኪሎ በላይ ዓሣ መመገብ ይችላል። ሽመላ በዘዴኝነቱ ከዓሣ አጥማጆች ይበልጣል ማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ ሲታይ ሽመላዎች ዓሦችን አድፍጦ በመያዝ ረገድ የተካኑ ናቸው። አንድ ሽመላ ብዙ ጥልቀት በሌለው ውኃ ላይ በቀስታ ይዋኛል፤ ወይም መንቆሩን አዘጋጅቶ አንድ ቦታ ላይ አድፍጦ ይጠብቃል። ከዚያም ዓሣው ዒላማው ውስጥ ሲገባለት በመጎንበስ በመንቆሩ ለቀም ያደርገዋል። አንድ ወፍ ዓሣ የማጥመዱ ሥራ እንዲሳካለት ትዕግሥተኛ መሆን ያስፈልገዋል።

ማባበያ ሰጥቶ ማጥመድ

ዘ ላይፍ ኦቭ በርድስ የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው በጃፓን የሚገኙት ባለ አረንጓዴ ጀርባ ሽመላዎች፣ በሰው ሠራሽ ኩሬዎች ውስጥ ለሚረቡ ዓሦች የዳቦ ቁርስራሽ የሚበትኑ ሰዎችን የሚኮርጁ ይመስላሉ። እነኚህ ዘዴኛ ወፎች የዳቦ ቁርስራሽ ተጠቅመው ዓሦቹን ወደ እነሱ እንዲቀርቡ በማድረግ በቀላሉ ይይዟቸዋል።

በካሪብያን ደሴቶች የሚገኙት ሳቢሳ የተባሉ የወፍ ዝርያዎችም ዓሦች ወደ እነሱ እንዲቀርቡ ለማድረግ የዳቦ ቁርስራሽ ይጠቀማሉ። እንዲያውም ሳቢሳዎች ቢጫ የሆነውን እግራቸውን ብቻ በመጠቀም ያለምንም ማባበያ ዓሦችን ይይዛሉ። እነዚህ ወፎች ብዙ ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ በአንድ እግራቸው ቆመው ሌላኛውን እግራቸውን እያወዛወዙ የዓሦቹን ቀልብ ለመሳብ ይሞክራሉ።

አፈፍ አድርጎ መያዝ

ወፎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ዓሦችን ያጠምዳሉ። በተለምዶ ኦስፕሪ ተብለው የሚጠሩት ዓሣ አዳኝ ንስሮች ዓሦችን አፈፍ አድርገው በመውሰድ ይታወቃሉ። እነዚህ ወፎች ወደ ውኃው ወለል ቀረብ ብለው የሚዋኙትን ዓሦች እያንዣበቡ ይፈልጋሉ። ዓሣውን እንዳዩት ክንፋቸውን አጥፈው ወደ ውኃው ተወርውረው በመግባት ዓሣውን በጥፍራቸው ቆንጥጠው በመያዝ ከውኃው ያወጡታል። ይህ ዘዴ በጣም ከፍተኛ የሆነ የማየት ችሎታና ቅልጥፍና ይጠይቃል።

የአፍሪካ ዓሣ አዳኝ ንስር አንዳንዴ በጥፍሮቹ የያዘው ዓሣ በጣም ስለሚከብደው ዓሣውን ይዞ መብረር ሊያቅተው ይችላል። አንዳንዴ የሚይዘው ዓሣ ክብደቱ እስከ 2.7 ኪሎ ግራም ሊደርስ ይችላል! በዚህ ጊዜ ንስሩ ምን ያደርጋል? የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች አንዳንድ ንስሮች በክንፋቸው ውኃውን እየቀዘፉ ዓሣውን ወደ ባሕር ዳርቻ ሲወስዱት ተመልክተዋል!

ወደ ባሕር ጠልቆ መያዝ

ጋኔት እና ቡቢ የተባሉ የወፍ ዝርያዎች ዓሣ ለመያዝ በቀጥታ ተወርውረው ወደ ባሕሩ ይጠልቃሉ። ጥቂት ወፎች አንድ ላይ ሆነው በማንዣበብ ወደ ውኃው ወለል ተጠግተው በኅብረት የሚዋኙ ዓሦችን ይቃኛሉ። የዓሦቹ ብርማ ቀለም የባሕሩን ጥቁር ሰማያዊ ቀለም ፈዘዝ ወዳለ አረንጓዴ ይለውጠዋል። ጋኔት እና ቡቢ የተባሉት ወፎች ይህን ምልክት ሲያዩ ዓሦቹን ለማጥመድ ይንቀሳቀሳሉ።

ጋኔት የተባሉት ወፎች እጅብ ብለው የሚንቀሳቀሱ ዓሦችን ሲመለከቱ በሰዓት እስከ 97 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት እንደ ቀስት እየተወረወሩ ወደ ባሕር ይጠልቃሉ። ወፎቹ በኦሎምፒክ ውድድር እንዳሉ ጠላቂዎች ማራኪ ትርዒት ያሳያሉ። የቀረው መንጋም እንቅስቃሴያቸውን ሲመለከት ከድግሱ ተካፋይ ለመሆን በፍጥነት ወደ አካባቢው ይደርሳል።

ቡቢ እና ጋኔት የተባሉት ወፎች፣ እንደ ሽመላዎች ወደ ባሕሩ እንደገቡ ዓሣውን በመንቆራቸው አይወጉትም። ወፎቹ በከፍተኛ ኃይል ቁልቁል ስለሚወረወሩ ወደ ውኃው ውስጥ ጠልቀው ይገባሉ። ከዚያም ሽቅብ በሚወጡበት ጊዜ ዓሣውን ይይዙትና ይውጡታል።

ተርን የተባሉት ወፎችም የተዋጣላቸው ጠላቂዎች ናቸው፤ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ዝቅ ብለው በውኃው ላይ ሲያንዣብቡ ይቆያሉ። ሃንድቡክ ኦቭ ዘ በርድስ ኦቭ ዘ ወርልድ የተሰኘው መጽሐፍ ተርን የተባሉት ወፎች እንደ ቡቢ እና ጋኔት ውኃው ውስጥ ተወርውረው ከመግባት ይልቅ “የረቀቀ የበረራ ችሎታቸውንና ቅልጥፍናቸውን” እንደሚጠቀሙ ዘግቧል። ወደ ባሕሩ ሳይጠልቁ ዓሣውን አፈፍ አድርገው ይዘው ይሄዳሉ። ለአጭር ጊዜ ውኃ ውስጥ ጠልቀው በመግባት ዓሦችን አሳድደው የሚይዙት አልፎ አልፎ ብቻ ነው።

በቡድን ማጥመድ

ሻሎ (ፔሊካን) የተባሉት ወፎች ግዙፍ መንቆር ያላቸው በመሆኑ ቀርፋፋ መስለው ይታዩ ይሆናል፤ ይሁንና የተዋጣላቸው በራሪዎችና ዓሣ አጥማጆች ናቸው። ቡናማ ሻሎዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ባሕር ጠልቀው በመግባት ዓሣ የሚይዙ ቢሆንም ዓሣ አጥማጆች በመረባቸው የያዟቸውን ዓሦች ቀምተው የሚበሉበት ጊዜም አለ። በቡድን ሆኖ ዓሣ በማጥመድ ረገድ ሻሎዎችን የሚወዳደር የለም።

ሻሎዎች የሚኖሩት በመንጋ ሆነው ነው። እነዚህ ወፎች ተረዳድቶ በጋራ የማጥመድ ባሕርያቸው በጣም የሚደነቅ ነው። ብዙውን ጊዜ ወደ አንድ ደርዘን የሚጠጉ ሻሎዎች አንድ ላይ ሆነው ባሕሩ ላይ ካረፉ በኋላ የግማሽ ክብ ቅርጽ በመሥራት በውኃው ላይ ይንሳፈፋሉ። ከዚያም ቀስ ብለው እየዋኙ እጅብ ብለው የሚንቀሳቀሱትን ዓሦች ጥልቀት ወደሌለው አካባቢ እየነዱ ይወስዷቸዋል። እግረ መንገዳቸውንም ክንፋቸውን እየዘረጉ ውኃው ውስጥ በጭንቅላታቸው በመጥለቅ ዓሦቹን ይውጧቸዋል።

እርግጥ ነው፣ እንደ ሰዎች ሁሉ ወፎችም ዓሣ ማጥመድ ሁልጊዜ ላይቀናቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ከዓሣ አጥማጆች ጋር ሲወዳደሩ ብዙውን ጊዜ ውጤታማ ናቸው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአፍሪካ ዓሣ አዳኝ ንስር

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Photolibrary

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግራጫ ሽመላ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰሜኑ ጋኔት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለመደው ዓይነት ተርን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአውስትራሊያ ሻሎ