በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሂትለር መኮንንነት ወደ እውነተኛው አምላክ አገልጋይነት

ከሂትለር መኮንንነት ወደ እውነተኛው አምላክ አገልጋይነት

ከሂትለር መኮንንነት ወደ እውነተኛው አምላክ አገልጋይነት

ጎትሊፕ በርንሃርት እንደተናገረው

በጀርመን ቬቨልስበርግ ግንብ በነበረው ኤስ ኤስ የሚባለው የሂትለር ልዩ የክብር ዘብ ውስጥ መኮንን ሆኜ አገለግል ነበር። ሚያዝያ 1945 በአቅራቢያችን በነበረው ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን እስረኞች እንድገድል ትእዛዝ ተሰጠኝ። እነዚህ እስረኞች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። አንድ የኤስ ኤስ መኮንን የበላዮቹ የሚሰጡትን ትእዛዝ ያላንዳች ጥያቄ እንዲታዘዝ ይጠበቅበት ነበር። ይህን ማድረግ ሕሊናዬ ስላልፈቀደልኝ አጣብቂኝ ውስጥ ገባሁ። ይህ የሆነበትን ምክንያት ልንገራችሁ።

1922 ጀርመን ውስጥ ራይን በሚባለው ወንዝ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንደር ተወለድኩ። ምንም እንኳ አካባቢው አጥባቂ የሮማ ካቶሊኮች የሚኖሩበት ቢሆንም ቤተሰቦቼ ግን በ17ኛው መቶ ዘመን የተጀመረው ፓየቲዝም የሚባል ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ አባላት ነበሩ። በ1933 የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሂትለር በጀርመን ሥልጣን ያዘ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በትምህርትም ሆነ በስፖርት ጥሩ ውጤት ስላመጣሁ ፖላንድ ውስጥ በመሪየንበርክ ከተማ (በአሁኑ ጊዜ ማልቦርክ ትባላለች) በሚገኝ አካዳሚ ገብቼ እንድማር ተመረጥኩ። ከአገሬ ብዙ መቶ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በዚህ አካዳሚ ስለ ብሔራዊ ሶሻሊዝም (ናዚ) ርዕዮተ ዓለም ጥልቅ እውቀት አዳበርኩኝ። በዚህ አካዳሚ ውስጥ ተማሪዎች አክብሮት፣ ትጋትና ታማኝነት ስለማሳየት፣ ግዴታን ስለ መገንዘብ እንዲሁም በጀርመናዊነት ስለ መኩራትና ስለ መሳሰሉት ነገሮች ይማሩ ነበር።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነትና ኤስ ኤስ

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ላይፕሽታንዳርተ ኤስ ኤስ አዶልፍ ሂትለር በሚባል ሂትለር በቀጥታ በሚያዘው ልዩ የክብር ዘብ ውስጥ ተመዘገብኩ። ይህ የጦር ክፍል የመንግሥት ባለሥልጣኖችን የሚያጅቡ ወታደሮችን ያቀርብ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን እንዲፈጽም ግዳጅ ይሰጠው ነበር። በቤልጂየም፣ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ፣ በሩማኒያ፣ በቡልጋሪያና በግሪክ የተደረጉትን ውጊያዎች አይቻለሁ። በቡልጋሪያ ሳለሁ በሠራዊቱ ውስጥ የሚያገለግል አንድ ቄስ ባካሄደው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቼ ነበር። በዚህ ጊዜ ‘ጠላቶቻችንም እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ያደርጉ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። በተጨማሪም ‘ለመሆኑ አምላክ ጦርነትን ይባርካል? አንደኛውን ወገንስ ይደግፋል?’ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ።

ከጊዜ በኋላ ወጣቶች ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጣን እንዲይዙ በሚሠለጥኑበት ዩንከሹለ በሚባል አካዳሚ ውስጥ እንድማር ተመረጥኩ። በዚህ አካዳሚ ውስጥ ከሠለጠንኩ በኋላ በርሊን የሚገኘውን የሂትለር ዋና መሥሪያ ቤት በሚጠብቅ እዝ ውስጥ ተመደብኩ፤ እዚያ እያለሁ በአንድ ወቅት ሂትለር በአንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ሰው ላይ በሰው ፊት ሲጮኽበት ተመለከትሁ። ይህን ስመለከት ‘ይህ አሳፋሪ ባሕርይ ነው’ ብዬ አሰብኩ፤ ይሁን እንጂ ከአፌ አውጥቼ ለመናገር አልደፈርኩም!

በርሊን ሳለሁ በዋናው መሥሪያ ቤት ትሠራ ከነበረች ኢንገ ከተባለች ሴት ጋር ተዋወቅሁ። ልንጋባ በዝግጅት ላይ ሳለን ተገቢውን የክረምት ልብስ እንኳ ሳልይዝ የነበርኩበት እዝ ወደ ሩሲያ ጦር ግንባር በድንገት በአውሮፕላን ተወሰደ! እዚያ ያጋጠመን ሁኔታ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነበር፤ ምክንያቱም በ1941/1942 የክረምቱ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር። በዚያም ለሁለተኛ ጊዜ የብረት መስቀል ኒሻን ተሸለምኩ። ከጊዜ በኋላ በውጊያ ላይ እያለን ተመትቼ በጣም ስለተጎዳሁ በአውሮፕላን ወደ ጀርመን ተላክሁ። እኔና ኢንገ በ1943 ተጋባን።

ከዚያም በባቫሪያን ተራሮች በሚገኘው ሂትለር ኦበርዛልትስበርግ በሚባል ወታደራዊ ተቋም ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ተመደብኩ። ሃይንሪክ ሂምለር የሚባለው የኤስ ኤስ አዛዥም የሚሠራው በዚህ ነበር። ሂምለር፣ ፌሊክስ ከርስተን የተባለ የእሽት አገልግሎት የሚሰጠው የእሱ ዶክተር እንዲያክመኝ አደረገ። በኋላም ከርስተን በበርሊን አቅራቢያ ሃርትስቫልደ ተብሎ የሚጠራ ርስት እንደነበረው ተረዳሁ። በጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ ከርስተን በአቅራቢያው ባለው ማጎሪያ ካምፕ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በርስቱ ላይ እንዲሠሩለት ሂምለርን ፈቃድ ጠየቀው። ሂምለርም በሐሳቡ ተስማማ፤ ከርስተን የይሖዋ ምሥክሮቹን በአክብሮት ይይዛቸው ነበር። ስዊድን ውስጥ በከርስተን ቤት ትሠራ የነበረች አንዲት የይሖዋ ምሥክር አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ በከርስተን ቦርሳ ውስጥ በመክተት ለጀርመን ወንድሞች ትልክላቸው ነበር። *

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተዋወቅሁ

በ1944 ማብቂያ ላይ ሂምለር የአንድ ኤስ ኤስ የጦር አዛዥ ረዳት ሆኜ እንድሠራ መደበኝ፤ ይህ ሰው በፓደቦርን ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውና 400 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የቬቨልስበርግ ግንብ ዋና አዛዥ ነበር። ሂምለር ቬቨልስበርግን የኤስ ኤስ ርዕዮተ ዓለምን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለማስረጽ የሚያገለግል ማዕከል እንዲሆን አቅዶ ነበር። በግንቡ አቅራቢያ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ተብለው ይጠሩ ነበር) ተብለው የሚጠሩ ለየት ያሉ እስረኞች የታሰሩበት ኒደሃገን የሚባል አንድ አነስተኛ ማጎሪያ ካምፕ ይገኝ ነበር።

እዚያ እያለሁ ኧርነስት ሽፔክት የሚባል አንድ እስረኛ ብዙ ጊዜ እየመጣ ቁስሌን ያክምልኝ ነበር። ሲመጣም “እንደምን አደሩ ጌታዬ” ይል ነበር።

እኔም “‘ሃይል ሂትለር!’ (ሂትለር አዳኝ ነው!) የማትለው ለምንድን ነው?” በማለት ኮስተር ብዬ ጠየቅሁት።

እሱም “እርስዎ ያደጉት በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው አይደል?” በማለት በዘዴ ጠየቀኝ።

“አዎን፣ ያደግሁት በፓየቲስት እምነት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው” ብዬ መለስኩለት።

“እንግዲያውስ፣ መዳን የሚገኘው በአንድ ሰው ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ያውቃሉ ማለት ነው። ‘ሃይል ሂትለር!’ የማልለው ለዚህ ነው” በማለት መለሰልኝ።

እኔም በመልሱ በጣም በመገረምና በመደነቅ “ለመሆኑ የታሰርከው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁት።

“የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነኝ” አለኝ።

ከኧርነስትና ፀጉር አስተካካይ ሆኖ ይሠራ ከነበረው ኤሪክ ኒኮላይዚግ ከሚባል ሌላ የይሖዋ ምሥክር ጋር ባደረግሁት ውይይት ልቤ ተነካ። ይሁን እንጂ ከእስረኞች ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረግ ክልክል ስለነበር በነበርኩበት እዝ ውስጥ አዛዤ የሆነው መኮንን ውይይቱን እንዳቆም ነገረኝ። ይሁን እንጂ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን አባላት በሚኖሩባትና የክርስቲያን አገር እንደሆነች በሚነገርላት በጀርመን የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ቢሆን ኖሮ ጦርነት አይኖርም ነበር የሚል ሐሳብ መጣብኝ። በተጨማሪም ‘የይሖዋ ምሥክሮች ሊደነቁ እንጂ ሊሰደዱ አይገባም’ ብዬ አሰብኩ።

በዚህ ወቅት ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት በጣም ተጨንቃ ልጇን በመኪና ወደ ሐኪም ቤት እንድናደርስላት ለመጠየቅ ስልክ ደወለች፤ ልጇ ትርፍ አንጀቱ በአስቸኳይ በቀዶ ሕክምና መውጣት ነበረበት። እኔም በአፋጣኝ መኪና አዘዝኩላት፤ ሆኖም አዛዤ የሆነው መኮንን ያስተላለፍኩትን ትእዛዝ ሻረው። ለምን? ባለቤቷ በሐምሌ 1944 ሂትለርን ለመግደል ሙከራ አድርጎ የነበረ አንድ ቡድን አባል ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት ተገድሎ ነበር። ልጁ ሕክምና ሳያገኝ በመቅረቱ ሞተ፤ እኔም ምንም ማድረግ አልቻልኩም። ያ አጋጣሚ እስከ ዛሬ ድረስ ሕሊናዬን ሲወቅሰኝ ይኖራል።

ዕድሜዬ ገና በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ቢሆንም በናዚ ፕሮፓጋንዳ ሳልታለል የሕይወትን ትክክለኛ ገጽታ መመልከት ጀምሬ ነበር። በተጨማሪም ለይሖዋ ምሥክሮችና ለሚያስተምሩት ትምህርት የነበረኝ አድናቆት ጨምሮ ነበር። ይህ ደግሞ በሕይወቴ ውስጥ አስደናቂ ውሳኔ እንዳደርግ ገፋፍቶኛል።

ሚያዝያ 1945 የሕብረ ብሔሩ ጦር እየተቃረበ ስለነበር የበላይ አዛዤ ከቬቨልስበርግ ሸሽቶ ሄደ። ከዚያም አንድ እዝ ግንቡን እንድደመስስና እስረኞቹንም እንድገድል የሚጠይቅ ትእዛዝ ይዞ ከሂምለር ዘንድ መጣ። በአቅራቢያው የነበረው የማጎሪያ ካምፕ አዛዥ ሊገደሉ የሚገባቸውን እስረኞች ስም ዝርዝር ሰጠኝ፤ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች እንዲገደሉ የተወሰነው ለምንድን ነው? በአንዳንዶቹ ሕንፃዎች ውስጥ ተደብቀዋል ተብለው የሚታመኑና በሂትለር አገዛዝ ወቅት የተዘረፉ የሥነ ጥበብ ውጤት የሆኑ ውድ ሀብቶች ያሉበትን ቦታ ስለሚያውቁ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከተገደሉ ያ ሚስጥር ሊወጣ አይችልም! ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮችን እንድገድል ከተሰጠኝ ትእዛዝ ማምለጥ የምችለው እንዴት ነው?

ወደ ካምፑ አዛዥ ሄጄ “የአሜሪካ ወታደሮች እየመጡ ነው። አንተና ወታደሮችህ ብትሄዱ የሚሻል አይመስልህም?” አልኩት። እሱም ይህን ለማድረግ ልቡ ተነሳስቶ ስለነበር ሄደ! ከዚያ በኋላ አንድ የኤስ ኤስ ወታደር ያደርጋል ተብሎ የማይታሰበውን ነገር አደረኩ፤ ይኸውም የይሖዋ ምሥክሮችን እንድገድል የተሰጠኝን ትእዛዝ ሳልፈጽም ቀረሁ። በዚህ ምክንያት እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከሞት ተረፉ።

ወንድማቸው የመሆን ክብር አገኘሁ

ከጦርነቱ በኋላ እኔና ኢንገ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተን መጽሐፍ ቅዱስን በከፍተኛ ጉጉት ማጥናት ጀመርን። አውጉስተ የምትባል አንዲት እህትና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ እርዳታ አድርገውልናል። በጦርነት ወቅት የደረሰብኝ ጉዳትና ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው ከባድ ጊዜ ኑሮን አስቸጋሪ አድርጎብን ነበር። ያም ሆኖ እኔና ባለቤቴ ሕይወታችንን ለይሖዋ በመወሰን እኔ በ1948 ኢንገ ደግሞ በ1949 ተጠመቅን።

በ1950ዎቹ ዓመታት በጦርነቱ ወቅት በቬቨልስበርግ የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እንደገና ለመገናኘት ወደዚያ ተመልሰው ነበር። ከእነሱም መካከል ኧርነስት ሽፔክትና ኤሪክ ኒኮላይዚግ እንዲሁም በዚያን ጊዜ ታስሮ የነበረ ማክስ ሆልቬግ የሚባል አንድ ሌላ ታማኝ ወንድም ይገኙበታል። እነዚህ ደፋር የአምላክ አገልጋዮች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለእኔ በመመሥከራቸው የእነሱ ወንድም ተብዬ መጠራትን እንደ ታላቅ ክብር እቆጥረዋለሁ። እንደገና ካገኘኋቸው ሰዎች መካከል በቬቨልስበርግ ጸሐፊ ሆና ትሠራ የነበረችው ማርታ ኒማን ትገኝበታለች። እሷም የይሖዋ ምሥክሮችን ባሕርይ በጣም ታደንቅ ስለነበረ ራሷን ወስና የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።

አሁን ያለፉትን ዓመታት መለስ ብዬ ስቃኝ ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር’ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉ እረዳለሁ፤ ገራገርና በግምታዊ ሐሳብ የምመራ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ግን ይህን አልተገነዘብኩም ነበር። (1 ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም እንደ ሂትለር አገዛዝ ያሉ ጨካኝ መንግሥታትን በማገልገልና ይሖዋን በማገልገል መካከል ያለውን በጣም ሰፊ ልዩነት በግልጽ ማየት ችያለሁ። እንዲህ ያሉት መንግሥታት ሰዎች በጭፍን እንዲታዘዟቸው ይጠይቃሉ፤ ይሖዋ የሚፈልገው ግን ባሕርይውንና ዓላማውን በሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፈረው ትክክለኛ እውቀት ላይ ተመርኩዘን በፍቅር እንድናገለግለው ነው። (ሉቃስ 10:27፤ ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ ይሖዋ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ላገለግለው የሚገባኝ አምላክ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 የሐምሌ 1, 1972 (እንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ ገጽ 399ን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የካቲት 1943 በሠርጋችን ዕለት የተነሳነው ፎቶግራፍ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቬቨልስበርግ፣ የኤስ ኤስ ርዕዮተ ዓለምን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለማስረጽ የሚያገለግል ማዕከል እንዲሆን ታቅዶ ነበር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከባለቤቴ ከኢንገ ጋር