በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፅንስ ማስወረድ ምንም ችግር የማያስከትል መፍትሔ ነው?

ፅንስ ማስወረድ ምንም ችግር የማያስከትል መፍትሔ ነው?

ፅንስ ማስወረድ ምንም ችግር የማያስከትል መፍትሔ ነው?

ቢል ከልጅነቱ ጀምሮ ፅንስ ማስወረድ ከመግደል የማይተናነስ ከባድ ኃጢአት እንደሆነ በጥብቅ ያምን ነበር። ይሁን እንጂ በ1975 ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅበት ሁኔታ ሲያጋጥመው ለበርካታ ዓመታት ሲከተለው በነበረው በዚህ አቋሙ ላይ ለውጥ አደረገ። በዚያ ጊዜ ቪክቶሪያ የምትባለው ሴት ጓደኛው ያረገዘች ሲሆን ቢል ትዳር መመሥረትም ሆነ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት የመሸከም ፍላጎት አልነበረውም። “ወዲያውኑ አመቺ የሆነውን መፍትሔ መረጥኩና ለቪክቶሪያ ፅንሱን ማስወረድ እንዳለባት ነገርኳት” በማለት ተናግሯል።

ቢል ‘አመቺ መፍትሔ’ ብሎ የጠራው ፅንስ የማስወረድ ድርጊት፣ ያልታሰበና የማይፈለግ እርግዝና በሚያጋጥምበት ጊዜ እንደ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ የሚታይ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ዘዴ ነው። በ2007 የተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው በ2003 በመላው ዓለም 42 ሚሊዮን ፅንስ የማስወረድ ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ፅንስ ማስወረድ ዘር፣ ዜግነት ሃይማኖትና አስተዳደግ እንዲሁም የኑሮና የትምህርት ደረጃ ሳይለይ ከጉርምስና አንስቶ እስከ ማረጥ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች የሚፈጸም ድርጊት ነው። የማይፈለግ እርግዝና ቢያጋጥማችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ብዙዎች ፅንስ ማስወረድን የሚመርጡት ለምንድን ነው?

“ሌላ አማራጭ አልታየኝም”

አንዲት የ35 ዓመት ሴት እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በእርግዝና ያሳለፍኳቸው ወራት በጣም ከባድ የነበሩ ከመሆኑም በላይ ምጥ አስቸግሮኝ ነበር፤ በተጨማሪም ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አልፎ ተርፎም በቤት ውስጥ ኃይለኛ ውጥረት ነበረብኝ። የሚገርመው ወልጄ ገና ስድስት ሳምንት እንዳለፈኝ እንደገና አረገዝኩ። ስለዚህ ፅንሱን ለማስወረድ ወሰንን። ፅንሱን ማስወረድ ኃጢአት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ አልታየኝም።”

ሴቶች ፅንስ እንዲያስወርዱ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶቹ ፅንስ የሚያስወርዱት በገንዘብ ችግር ምክንያት ይሆናል፤ ሌሎች ደግሞ ከጓደኛቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ስለተበላሸ ምናልባትም ከዚያ ሰው ጋር ዳግም የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት ነገር እንዲኖር ስለማይፈልጉ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ሴትየዋ ወይም ሁለቱም የመውለድ እቅድ ላይኖራቸው ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ፅንስ ማስወረድ የሚመርጡት ስማቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሊሆን ይችላል። ዶክተር ሱዛን ዊክለንድ ዚስ ኮመን ሲክሬት—ማይ ጆርኒ አዝ አን አቦርሽን ዶክተር በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩት ነጥብ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። ውርጃ እንዲፈጸምላት የፈለገች አንዲት ታካሚ እንደሚከተለው በማለት ነግራቸው ነበር፦ “ወላጆቼ በጣም ሃይማኖተኛ ናቸው። . . . ሳላገባ ልጅ ከወለድኩ ስማቸው ይጠፋል። ጓደኞቻቸው ሁሉ ልጃቸው ኃጢአት እንደፈጸመች ሊያውቁ ነው።”

ዶክተር ዊክለንድ በማስከተል “እሺ ይሁን፣ ኃጢአት ሠርተሻል እንበል፤ ታዲያ ስለ ማስወረድስ ምን ይሰማቸዋል?” ብለው ጠየቋት። ከዚያም ልጅቷ እንዲህ በማለት መለሰች፦ “ማስወረድማ ምንም ይቅርታ የሌለው ኃጢአት ነው። ቢሆንም ሳያገቡ ከመውለድ ይሻላል፤ ምክንያቱም በሚስጥር ሊያዝ ይችላል። ፅንሱን ባስወርድ በቤተ ክርስቲያን ያሉት [የወላጆቼ] ጓደኞች ምንም ሊያውቁ አይችሉም።”

ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ አብዛኛውን ጊዜ ፅንስ ለማቋረጥ የሚደረገው ውሳኔ ቀላል አይደለም። ብዙውን ጊዜ ኃይለኛ ሥቃይ ያስከትላል። ይሁንና አንዳንዶች እንደሚያስቡት ማስወረድ ምንም ችግር የማያስከትል መፍትሔ ነው?

የሚያስከትለውን መዘዝ አስቡበት

በ2004፣ ግፊት ተደርጎባቸው ፅንስ ባስወረዱ 331 ሩሲያውያንና 217 አሜሪካውያን ሴቶች ላይ የተደረገ ጥናት፣ በሁለቱም ወገን ካሉት ሴቶች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ከውርጃው በኋላ መጥፎ ስሜት እንደተሰማቸው አመልክቷል። ወደ 50 በመቶ የሚጠጉት ሩሲያውያንና 80 በመቶ የሚያህሉት አሜሪካውያን በማስወረዳቸው “የጥፋተኝነት ስሜት” ተሰምቷቸዋል። ከአሜሪካውያኑ ሴቶች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ‘ራሳቸውን ይቅር ማለት አልቻሉም ነበር።’ ራሳቸውን እንደ ሃይማኖተኛ የማይቆጥሩ በርካታ ሴቶችም እንኳ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸው ከሆነ ታዲያ ብዙ ወጣት ሴቶች አሁንም ፅንስ የሚያስወርዱት ለምንድን ነው?

ብዙውን ጊዜ ሴቶች ፅንስ የሚያስወርዱት ሌሎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚፈጥሩባቸው ጫና ስለሚበረታባቸው ነው። ወላጆች፣ የትዳር ጓደኛ ወይም አሳቢ የሆኑ ጓደኞች፣ ከሁለት መጥፎ አማራጮች ውስጥ የተሻለው ምርጫ እንደሆነ በመናገር ፅንስ ማስወረድን ያበረታቱ ይሆናል። ይህ ደግሞ እርግጠኛ ባልሆነ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የችኮላ ውሳኔ ወደማድረግ ሊመራ ይችላል። ውርጃ ስለሚያስከትለው የአእምሮ ችግር ያጠኑ ጵርስቅላ ኮልማን የተባሉ አንዲት ዶክተር እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “ሴቶቹ በስንት ጭንቀት ውሳኔ ላይ ከደረሱና ውርጃው ከተከናወነ በኋላ አስተሳሰባቸው የሚሻሻለው ብዙውን ጊዜ በሐዘን ከተደቆሱ እንዲሁም በጥፋተኝነትና በጸጸት ስሜት ከተሠቃዩ በኋላ ነው።”

ፅንስ ያስወረዱ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚጸጸቱት ‘ሕይወት አጥፍቼ ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ ስለሚያስጨንቃቸው ነው። በደቡብ ዳኮታ ስለ ውርጃ ለማጥናት የተሰማራው ግብረ ኃይል ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ፅንስ ያስወረዱ ብዙ ነፍሰ ጡር ሴቶች “ከማሕፀናቸው የወጣው ነገር ሕይወት ያለው ነገር ሳይሆን ‘ተራ ሥጋ’ እንደሆነ ተደርጎ ስለተነገራቸው የተሳሳተ አመለካከት አድሮባቸው ነበር፤ ይሁንና እውነቱ ቢነገራቸው ኖሮ እንደማያስወርዱ ተናግረዋል።”

ይህ ጥናት ፅንስ ያስወረዱ 1,940 ሴቶች የሰጡትን “ለየት ያለና እጅግ የሚያሳዝን ምሥክርነት” ከገመገመ በኋላ “ከእነዚህ ሴቶች ውስጥ ብዙዎቹ ሕይወት የለውም ተብሎ የተነገራቸውን ልጅ በማጣታቸው በንዴትና በሐዘን ይብሰለሰላሉ” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። በተጨማሪም ጥናቱ እንደገለጸው “እናትየው ልጇን እንደገደለች ማወቋ የሚያስከትልባት ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ብዙውን ጊዜ በእጅጉ ይጎዳታል።”

ታዲያ እውነታው ምንድን ነው? ፅንስ ማስወረድ ሲባል ከነፍሰ ጡሯ ሰውነት ሥጋ ቆርጦ ማውጣት ማለት ብቻ ነው? በማህፀን ውስጥ ያለ ልጅ በእርግጥ ሕይወት ያለው ሰው ነው?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

መውለድና ማስወረድ ሲነጻጸሩ

በ2006 የተደረገ አንድ ጥናት ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል እያሉ አርግዘው የነበሩ ብዙ ሴቶችን የሕይወት ታሪክ እንደገና መርምሮ ነበር። ጥናት ከተደረገባቸው ውስጥ ግማሾቹ የወለዱ ሲሆን ግማሾቹ ደግሞ አስወርደው የነበሩ ናቸው። ጥናቱ እንዳረጋገጠው “ልጅ የወለዱት ሴቶች ፅንስ ካስወረዱት ሴቶች አንጻር ሲታዩ እምብዛም ሥነ ልቦናዊ የምክር አገልግሎት ማግኘት አያስፈልጋቸውም፣ ለእንቅልፍ ችግር ብዙም የተጋለጡ አይደሉም፣ ማሪዋና የማጨስ አጋጣሚያቸውም በጣም ያነሰ ነው።”—ጆርናል ኦቭ ዩዝ ኤንድ አዶለሰንስ

አንድ ሌላ ዘገባ ደግሞ “በዓለም ላይ ሠፊ ምርምር ከተደረገባቸው አራት ትልልቅ ጥናቶች የተገኙ ውጤቶችን” አቅርቦ ነበር። እነዚህ ጥናቶች ምን አመልክተዋል? “ውርጃ ፈጽመው የነበሩት ሴቶች ለተለያየ የአእምሮ ችግር የመጋለጣቸው አጋጣሚ ውርጃ ፈጽመው ከማያውቁት ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ነው።”—በደቡብ ዳኮታ ስለ ውርጃ ለማጥናት የተሰማራው ግብረ ኃይል ያወጣው ሪፖርት—2005