በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፒሳ አምሮት

የፒሳ አምሮት

የፒሳ አምሮት

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

በአንድ ወቅት፣ ቀዳማዊ ንጉሥ ፈርዲናንድ (1751–1825) ማንነቱን ደብቆ ተራ ሰው በመምሰል ኔፕልስ ውስጥ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ወደሚገኙበት አካባቢ ሄዶ እንደነበር ይነገራል። ንጉሡ ማንነቱን ደብቆ መሄድ ለምን አስፈለገው? አንድ ታሪክ እንደገለጸው ከሆነ፣ ንግሥቲቱ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዳይዘጋጅ የከለከለችውን ፒሳ ለመብላት ነበር።

ንጉሥ ፈርዲናንድ በዛሬ ጊዜ በሕይወት ቢኖር ኖሮ የሚወደውን ፒሳ ለማግኘት ያን ያህል አይቸገርም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ጣሊያን ውስጥ 30,000 ገደማ ፒሳ ቤቶች ያሉ ሲሆን ለእያንዳንዱ ነዋሪም በየዓመቱ 45 ፒሳ ማዘጋጀት ይችላሉ!

የድሆች ምግብ

ፒሳ መዘጋጀት የጀመረው በ1720 ገደማ በኔፕልስ እንደሆነ ይገመታል። በዚያን ጊዜ ፒሳ በዋነኛነት ይዘጋጅ የነበረው ለድሆች ሲሆን በየጎዳናው ላይ የሚሸጥ “በፍጥነት የሚዘጋጅ ምግብ” ነበር። ፒሳ አዟሪዎች የሚሸጡትን ጣፋጭ ምግብ በጭንቅላታቸው ተሸክመው በየመንገዱ እየተዘዋወሩ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ሰዎች እንዲገዟቸው ይጋብዙ ነበር። እነዚህ ሰዎች ፒሳዎቹ እንዳይቀዘቅዙ ስኩዶ በሚባል ከመዳብ በተሠራ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ያደርጉታል።

ቀዳማዊ ንጉሥ ፈርዲናንድ ለፒሳ ያለውን ፍቅር ከጊዜ በኋላ ለንጉሣዊው ቤተሰብ በይፋ ገልጿል። በየጎዳናው ይሸጥ የነበረው ጥሩ ጣዕም ያለው ይህ ምግብ ብዙም ሳይቆይ ተወዳጅነት እያገኘ በመምጣቱ የናጠጡ ሀብታሞችና የንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት እንኳ ሳይቀር ፒሳ ወደሚዘጋጅባቸው ቤቶች ይጎርፉ ጀመር። የፈርዲናንድ የልጅ ልጅ የሆነው ዳግማዊ ንጉሥ ፈርዲናንድ፣ በ1832 በካፖዲሞንቴ ቤተ መንግሥት በሚገኘው የአትክልት ሥፍራ ውስጥ በማገዶ እንጨት የሚሠራ የፒሳ መጋገሪያ እስከማስገንባት ደርሶ ነበር። እንዲህ በማድረጉ ወደ ቤተ መንግሥቱ በእንግድነት የሚመጡትን መሳፍንትና መኳንንት ማስደሰት ችሎ ነበር።

ፒሳ—ገንቢ ምግብ ነው?

በዛሬው ጊዜ ፒሳ በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያለው ምግብ ነው፤ ይሁንና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ፒሳ ገንቢ ምግብ ሊሆን የሚችለው ምግቡን ለማዘጋጀት የሚጨመሩት ነገሮች የካርቦሃይድሬት፣ የፕሮቲንና የቅባት ይዘታቸው የተመጣጠነ እንዲሁም በቪታሚኖች፣ በማዕድናትና በአሚኖ አሲድ የበለፀገ ከሆነ ነው። ፒሳ በምንሠራበት ወቅት የወይራ ዘይት ብንጠቀም ይመረጣል። ይህ ዘይት “የደም ቅዳ ቧንቧዎችን ለማጽዳት የሚረዳ ጥሩ ዓይነት ኮሌስትሮል” በሰውነት ውስጥ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ከዚህም ሌላ ፒሳ በደንብ ከበሰለ አብዛኛውን ጊዜ የምግብ ያለመፈጨት ችግር አያስከትልም። ለዚህ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ ዱቄቱ በሚለወስበትና እንዲቦካ በሚተውበት ጊዜ ውስጡ ያለው ካርቦሃይድሬት ከውኃ ጋር በደንብ ስለሚዋሃድ ነው። በተጨማሪም ፒሳ በበርካታ የካርቦሃይድሬት ዓይነቶች የበለጸገ ነው፤ ይህ ደግሞ ቶሎ የመጥገብ ስሜት ስለሚፈጥር ፒሳ ወዳድ የሆነ ሰው እንኳ ከመጠን በላይ እንዳይበላ ይረዳዋል።

በቀጣዩ ጊዜ ተወዳጁን ፒሳ ስትበላ በአንድ ወቅት የድሆች ምግብ እንደነበር አስታውስ። እንዲሁም ቀዳማዊ ንጉሥ ፈርዲናንድ ለፒሳ የነበረውን ፍቅር ገሃድ በማውጣቱ ልትደሰት ይገባል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፒሳ ጥሩ ጣዕም የሚኖረው በእንጨት ማገዶ ቢጋገር ነው። ፒሳው በሚበስልበት ወቅት የሚወጣው ጭስ ለፒሳው ልዩ መዓዛ የሚፈጥርለት ሲሆን ፒሳው መጋገሪያው ላይ ያለው አመድ ደግሞ ለየት ያለ ጣዕም ይሰጠዋል።

በዓለም ላይ በጣም ትልቁ ክብ ፒሳ የተሠራው በ1990 ነበር። የፒሳው ርዝመት ከ37 ሜትር የሚበልጥ ሲሆን ክብደቱም ከ120 ኩንታል በላይ ነበር!

የተለወሰውን የፒሳ ሊጥ ወደ ላይ የመወርወርና አየር ላይ እንዳለ የማሽከርከር ልማድ ሰዎችን ለማስደመም ብቻ ተብሎ የሚደረግ አይደለም። ፒሳው በዚህ ሁኔታ መሽከርከሩ ሊጡ ጠፍጣፋ የሆነ ክብ ቅርጽ እንዲይዝና ወፈር ያለ ጠርዝ ያለው ጥሩ የፒሳ ቂጣ እንዲሆን ያደርጋል።