በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በ20ኛው መቶ ዘመን ትንባሆ ለ100 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።”— የዓለም የጤና ድርጅት፣ ስዊዘርላንድ

“ከ1996 እስከ 2003 ባሉት ዓመታት [በዩናይትድ ኪንግደም] የልብ ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸውና ቀይ የደም ሴል በደም ሥራቸው የወሰዱ 9,000 የሚሆኑ ሕሙማን ምንም ደም ካልወሰዱት ታካሚዎች ጋር ሲነጻጸሩ በቀጣዩ ዓመት ለሞት ሊጋለጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሦስት እጥፍ ጨምሯል፤ ቀዶ ሕክምና በተደረገላቸው 30 ቀን ውስጥ ሊሞቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ደግሞ ስድስት እጥፍ ገደማ እንደጨመረ ተረጋግጧል።”ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ

በእርግጥ የሰላም ጊዜ ነው?

ቪ ፎርኤልድራር የተሰኘ ለወላጆች የሚዘጋጅ አንድ የስዊድን መጽሔት “ገና ከታላላቅ በዓሎቻችን አንዱ ነው”፤ ይሁን እንጂ “የጠብ ጊዜም” ጭምር ነው በማለት ገልጿል። እንዲያውም የገና ሰሞን ቤተሰቦች “ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ የሚጣሉበትና የሚጨቃጨቁበት ወቅት ነው።” ከላይ የተጠቀሰው መጽሔት፣ ትንንሽ ልጆች ያሏቸውን ከ1,100 የሚበልጡ ወላጆች በበዓሉ ሰሞን ስለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ጠይቋቸው ነበር። ከእነዚህ መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰባቸው “ገናን እንዴትና የት እናክብረው” በሚለው ጉዳይ እንደሚጨቃጨቅ ገልጸዋል። ብዙ ወላጆች ደግሞ አያቶች ከረሜላና ሌሎች የማያስፈልጉ ስጦታዎችን እየሰጡ ልጆቻቸውን ስለሚያሞላቅቁባቸው ይበሳጫሉ።

መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል

በካናዳ የሚታተመው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ “ለጋስ ከሆንክ ገንዘብ ደስተኛ ያደርግሃል” የሚል አንድ ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ምንም እንኳ ጥናት ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ገንዘቡን ለራሳቸው ጉዳይ ማዋሉ እንደሚያስደስታቸው አስተያየት የሰጡ ቢሆንም በገንዘባቸው ሌሎችን የረዱ ሰዎች፣ ያወጡት የገንዘብ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን የበለጠ ደስታ እንዳገኙ ገልጸዋል። “ሀብት ለደስታ ዋስትና እንደማይሆን በተደጋጋሚ የተደረጉት ጥናቶች አሳይተዋል” በማለት ጋዜጣው ተናግሯል። “ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያስችላቸውን ገንዘብ ካገኙ በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘታቸው ያን ያህል ደስታ አይጨምርላቸውም።”

በኢንተርኔት ልታገኘው ትችላለህ!

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለሥልጣኖች፣ ጠላቶቻቸው በኢንተርኔት አማካኝነት “አደገኛ የሆኑ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ማግኘት” ይችሉ እንደሆነ ለማጣራት ሙከራ አድርገው እንደነበር ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት ዘግቧል። ባለሥልጣኖቹ “እንዲህ ዓይነቶቹን መሣሪያዎች በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ሲያውቁ እጅግ ተገረሙ።” በጣም የታወቁ የኢንተርኔት የመገበያያ ድረ ገጾችን በመጠቀም “ለዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች የሚዘጋጀውን ብረት ለበስ ትጥቅ ለመሥራት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች፣” “የኑክሌር፣ የባዮሎጂና የኬሚካል መሣሪያን የሚከላከል ያገለገለ ልብስ፣” የተዋጊ አውሮፕላን መለዋወጫዎች እንዲሁም “ሌሎች አደገኛ መሣሪያዎችን” ለመግዛት ምንም ችግር አልገጠማቸውም። ሻጮቹ እንዲህ ዓይነቶቹን መሣሪያዎች እንዴት እንዳገኟቸው ባይታወቅም አንዳንዶቹ “በአሁኑ ጊዜ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው” መሆኑን መጽሔቱ ገልጿል።

ጥንታዊው ኃይለኛ ሙጫ

በጥንት ዘመን አንድ ሮማዊ ባለሥልጣን ለሰልፍ ሲወጣ በሚያደርገው የራስ ቁር ላይ በሎረል ቅጠል አምሳል ከብር የተሠራ ጌጥ ተለጥፎ ተገኝቷል፤ ጌጡን ለመለጠፍ ጥቅም ላይ የዋለው ሙጫ በአሁኑ ጊዜ ካሉት ኃይለኛ ማጣበቂያዎች ጋር ተመሳሳይነት አለው። ጀርመን ውስጥ በቦን ከተማ በሚገኘው ራይንላንድ ሙዚየም ውስጥ ቅርሶችን የሚያድሱት ፍራንክ ቪለ ይህን ግኝት የደረሱበት በአጋጣሚ ነበር። እኚህ ሰው በራይን ወንዝ ወለል ውስጥ ቢያንስ ለ1,500 ዓመታት ተቀብሮ ከቆየና ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንደኛው መቶ ዘመን ከተሠራ አንድ የብረት ራስ ቁር ላይ አንዲት አነስተኛ ብረት በጥሩ መጋዝ ተጠቅመው ለማላቀቅ እየሞከሩ ነበር። “ከመጋዙ የሚወጣው ሙቀት በራስ ቁሩ ላይ የተለጠፈችውን በሎረል ቅጠል ቅርጽ ከብር የተሠራች ጌጥ እንድትነቀል ሲያደርጋት በሙጫው ሳቢያ የተፈጠሩ ክር የሚመስሉ ምልክቶች ታዩ” በማለት ፍራንክ ቪለ ገልጸዋል። የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው ይህ ኃይለኛ ማጣበቂያ ከሬንጅ፣ ከግንድ ቅርፊት ላይ ከተወሰደ ሙጫና ከበሬ ሞራ የተሠራ ነበር።