በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌላ ቋንቋ መማር ትችላለህ!

ሌላ ቋንቋ መማር ትችላለህ!

ሌላ ቋንቋ መማር ትችላለህ!

ማይክ “ይህን አጋጣሚ በምንም ልለውጠው አልፈልግም” ሲል ፌልፕስ ደግሞ “በሕይወቴ ካደረግኳቸው ጥሩ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው” በማለት ተናግሯል። ሁለቱም እየተናገሩ ያሉት ሌላ ቋንቋ በመማር ስላሳለፉት ተፈታታኝ ሁኔታ ነው።

በዓለም ዙሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሌሎች ቋንቋዎችን በመማር ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ እንዲህ የሚያደርጉት እንዲያው ደስ ስለሚላቸው ሲሆን ሌሎቹ ሥራ ለማግኘት፣ የተቀሩት ደግሞ በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ ነው። ንቁ! የውጪ አገር ቋንቋ በመማር ላይ ካሉ በርካታ ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። ለእነዚህ ሰዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ‘ትልቅ ሰው ሆኖ አዲስ ቋንቋ መማር ምን ይመስላል? አንድ ሰው ሌላ ቋንቋ እንዲማር ምን ሊረዳው ይችላል?’ የሚሉት ይገኙበታል። ቀጥሎ ያሉት ሐሳቦች የተዘጋጁት እነርሱ የሰጡትን አስተያየት መሠረት በማድረግ ነው። አንተም በተለይ አዲስ ቋንቋ እየተማርክ ከሆነ ወይም ወደፊት የመማር ሐሳቡ ካለህ እዚህ ላይ የቀረቡት ነጥቦች አበረታች ብሎም የግንዛቤ አድማስህን የሚያሰፉ ሆነው እንደምታገኛቸው እንተማመናለን። ለምሳሌ ያህል፣ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ሰዎች አንድን አዲስ ቋንቋ አቀላጥፎ ለመናገር ወሳኝ ናቸው ብለው የጠቀሷቸውን አንዳንድ አስፈላጊ ባሕርያት እንመልከት።

ትዕግሥት፣ ትሕትናና ከሁኔታዎች ጋር ቶሎ መላመድ

ትንንሽ ልጆች የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች በመኖር ብቻ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን በቀላሉ መማር የሚችሉ ሲሆን አዋቂዎች ግን አንድን አዲስ ቋንቋ መማር አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት አዲስ ቋንቋ መማር ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ የሚማሩት ሰዎች ትዕግሥተኛ መሆን ስለሚያስፈልጋቸው ነው። አዋቂዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ፕሮግራማቸው የተጣበበ በመሆኑ አዲስ ቋንቋ መማር መጀመራቸው ሌሎች ጉዳዮቻቸውን ለጊዜውም ቢሆን እንዲተዉ ይጠይቅባቸዋል።

ጆርጅ “ትሕትና በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት ተናግሯል። “አዲስ ቋንቋ ስትማር እንደ ሕፃን ለመናገር አልፎ ተርፎም በሌሎች ዘንድ አንዳንድ ጊዜ እንደ ሕፃን ለመታየት ፈቃደኛ መሆን አለብህ።” ሃው ቱ ለርን ኤ ፎሬን ላንጉጅ የተሰኘው መጽሐፍ “እድገት ለማድረግ ከፈለግህ ኩራትን ማስወገድና ስለ ክብርህ ከመጨነቅ መቆጠብ ይኖርብሃል” በማለት ይገልጻል። ስለዚህ እሳሳት ይሆናል ብለህ ከልክ በላይ አትጨነቅ። ቤን “ካልተሳሳትክ አዲሱን ቋንቋህን በበቂ ሁኔታ እየተጠቀምክበት አይደለም ማለት ነው” ብሏል።

ሌሎች ስትሳሳት ቢስቁብህ አይሰማህ፤ ከዚህ ይልቅ አብረሃቸው ሳቅ! እንዲያውም የተሳሳትክባቸውን ነገሮች አንስተህ ከሌሎች ጋር የምትስቅበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። ከዚህም በላይ ፈርተህ ጥያቄ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። አንድ ነገር ለምን እንደዚያ መባል እንዳለበት ማወቅህ ያንን ነገር እንዳትረሳው ይረዳል።

ብዙውን ጊዜ አዲስ ቋንቋ መማር አዲስ ባሕል መማርንም ስለሚጨምር አእምሮህን ሰፋ አድርገህ ከሁኔታዎች ጋር ለመላመድ መጣርህ ጠቃሚ ነው። ጁሊ ይህን በሚመለከት ስትናገር “ሌላ ቋንቋ መማሬ ነገሮችን እኔ ከማውቀው በተለየ መንገድ መመልከትና ማድረግ እንደሚቻል እንድገነዘብ ረድቶኛል። ነገሮችን መመልከት ወይም ማድረግ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ከሌላው የተለየ ስለሆነ ብቻ ከሌሎቹ የተሻለ ነው ማለት አይቻልም” ብላለች። ጄይ ሐሳብ ሲሰጥ “የምትማረውን ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ጓደኛ ለመሆንና ከእነሱ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርግ” በማለት ያበረታታል። እርግጥ ክርስቲያኖች ጓደኝነት የሚመሠርቱት አነጋገራቸው ንጹሕ ከሆነ ሰዎች ጋር መሆን እንዳለበት የተረጋገጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ኤፌሶን 5:3, 4) ጄይ አክሎ “እነርሱን ጨምሮ ምግባቸውን፣ ዘፈናቸውንና ሌሎች ነገሮቻቸውን እንደወደድክላቸው ሲያውቁ ያለ አንዳች ችግር ይቀርቡሃል” ብሏል።

ቋንቋውን ለማጥናት፣ ይበልጡንም ደግሞ በቋንቋው ለመግባባት የምታውለውን ጊዜ በጨመርክ መጠን እድገትህም የዚያኑ ያህል ፈጣን ይሆናል። ጆርጅ “የቋንቋ ችሎታችንን የምናዳብርበት መንገድ አንዲት ዶሮ አንድ በአንድ እየለቀመች ጥሬ ከምትበላበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል” በማለት ተናግሯል። “አንዷ ጥሬ ብቻዋን ከግምት የምትገባ ባትሆንም አንድ ላይ ሲሆኑ ግን ይጠራቀማሉ።” ሚስዮናዊ ሆኖ የተወሰኑ ቋንቋዎችን የተማረው ቢል “ቃላትን መዝግቤ የያዝኩበትን ደብተር በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ይዤ በመሄድ ጥቂት ጊዜ ሳገኝ መለስ ብዬ እመለከታቸዋለሁ” ብሏል። ብዙዎች፣ ቋንቋ በምንማርበት ጊዜ አልፎ አልፎ ብዙ ከማጥናት ይልቅ ዘወትር ትንሽ ትንሽ ማጥናቱ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነ ተገንዝበዋል።

ቋንቋ የሚማሩ ሰዎችን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ መጻሕፍትን፣ ካሴቶችን፣ ቁርጥራጭ ካርዶችን ጨምሮ በርካታ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ መሣሪያዎች ቢኖሩም ብዙ ሰዎች ትምህርት ቤት ገብተው በሥርዓት ቢማሩ በጣም የተሻለ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። አንተም ይሻለኛል የምትለውን ዘዴ ከመጠቀም ወደኋላ አትበል። ይሁንና አዲስ ቋንቋ ለመማር የግል ጥረት ከማድረግና ያለመታከት ከመለማመድ የተሻለ አቋራጭ መንገድ እንደሌለ አትዘንጋ። ሆኖም የመማር ሂደቱን ቀላልና አስደሳች ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ። አንደኛው መንገድ ቋንቋውን ከሚናገሩ ሰዎች ጋር መቀራረብና ከባሕላቸው ጋር መላመድ ነው።

ጆርጅ “ስለ አዲሱ ቋንቋ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን በደንብ አጣርተህ ካወቅህና ከአንድ ጀማሪ ተናጋሪ የሚጠበቀውን ያህል መነጋገሪያ ቃላት ካሉህ አዲሱ ቋንቋህ ወደሚነገርበት አገር ሄደህ የተወሰነ ጊዜ ብታሳልፍ ጥሩ ነው” በማለት ተናግሯል። ባርብ ከዚህ ሐሳብ ጋር በመስማማት “ቋንቋው ወደሚነገርበት አገር መሄድህ ቅላጼውን በደንብ እንድታውቅ ያስችልሃል” ትላለች። ከዚህም በላይ ቋንቋው በሚነገርበት አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ መኖርህ በአዲሱ ቋንቋ እንድታስብ ይረዳሃል። እርግጥ ነው፣ ብዙዎች ወደ ሌላ አገር ሄደው ለመኖር ሁኔታቸው አይፈቅድላቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ባሉበት ቦታ ሆነው ከቋንቋውም ሆነ ከባሕሉ ጋር መተዋወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በምትማረው ቋንቋ የሚዘጋጁ ከሥነ ምግባር አኳያ ተቀባይነት ያላቸውና ጤናማ የሆኑ ጽሑፎች፣ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሊኖሩ ይችላሉ። በአካባቢህ ቋንቋውን በደንብ የሚናገሩ ሰዎችን ፈልግና ከእነሱ ጋር ተነጋገር። ሀው ቱ ለርን ኤ ፎሬን ላንጉጅ የተሰኘው መጽሐፍ “በመጨረሻ፣ እድገት ለማድረግ የሚረዳው ብቸኛውና ከሁሉ የተሻለው መንገድ ብዙ ልምምድ ማድረግ ነው” በማለት ተናግሯል። *

እድገት ማድረግ እንዳቆምክ በሚሰማህ ወቅት

ቋንቋውን እየተማርክ እያለህ አንዳንድ ጊዜ እድገት ማድረግህን እንዳቆምክና እንዲያው በከንቱ እየደከምክ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ልታደርግ ትችላለህ? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቋንቋውን ለመማር የተነሳህበትን ምክንያት መለስ ብለህ አስብ። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ቋንቋ ለመማር የተነሳሱት ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ለመርዳት በማሰብ ነው። አንተም አዲስ ቋንቋ ለመማር የተነሳህበትን የመጀመሪያ ግብህን ወይም ዓላማህን መለስ ብለህ ማሰብህ ቁርጠኝነትህን ሊያጠናክርልህ ይችላል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን። ሃው ቱ ለርን ኤ ፎሬን ላንጉጅ የተሰኘው መጽሐፍ “ምንም ቢሆን አፉን በዚያ ቋንቋ እንደፈታ ሰው አቀላጥፈህ መናገር አትችል ይሆናል፤ አንተም ብትሆን ዋናው ግብህ ይህ አይደለም። አንተ የምትፈልገው ሰዎች ለመናገር ያሰብከውን ሐሳብ መረዳታቸውን ብቻ ነው” በማለት ይናገራል። ስለዚህ የምትማረውን ቋንቋ የአፍ መፍቻ ቋንቋህን ያህል አቀላጥፈህ መናገር ስላልቻልክ ብቻ ከማማረር ይልቅ በተማርከው መሠረት ሐሳብህን በግልጽ ማስተላለፍ በመቻልህ ላይ አተኩር።

በሦስተኛ ደረጃ፣ እድገት ማድረግህን የሚጠቁሙ ነገሮችን ለማስተዋል ሞክር። አንድን ቋንቋ መማር የሣርን እድገት ከመመልከት ጋር ይመሳሰላል፤ ሣር የሚያደርገው እድገት ባይታይም እንኳ በየዕለቱ ቁመት ይጨምራል። በተመሳሳይም አዲሱን ቋንቋ መማር የጀመርክበትን ጊዜ መለስ ብለህ ካሰብክ በእርግጥ እድገት ማድረግህን ማስተዋልህ አይቀርም። የአንተን እድገት ከሌሎች ጋር አታወዳድር። መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 6:4 ላይ ልትከተለው የሚገባ ጥሩ መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም በኋላ፣ ከሌላ ሰው ጋር ራሱን ሳያወዳድር፣ ስለ ራሱ የሚመካበትን ያገኛል።”

በአራተኛ ደረጃ፣ ቋንቋ የመማሩን ሂደት ከረዥም ጊዜ ልፋትና ጥረት በኋላ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ሥራ አድርገህ ተመልከተው። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብበት:- የሦስትና የአራት ዓመት ሕፃን የመናገር ችሎታ ምን ያህል ነው? የተወሳሰቡ ቃላትንና የተራቀቀ ሰዋስው ይጠቀማል? በጭራሽ! ሆኖም ከሌሎች ጋር መግባባት ይችላል። አንድ ልጅም እንኳ ቋንቋ መማር በርካታ ዓመታት ይወስድበታል።

በአምስተኛ ደረጃ፣ አዲሱን ቋንቋህን በተቻለህ መጠን ሁልጊዜ ተጠቀምበት። ቤን “ቋንቋውን አዘውትሬ ሳልጠቀም ስቀር እድገት ማድረጌን እንዳቆምኩ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል። ስለዚህ አዘውትረህ ተጠቀምበት። በምታገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቋንቋው ተነጋገር! የምታውቃቸው ቃላት ብዛት አንድ ትንሽ ልጅ ከሚያውቃቸው ቃላት እምብዛም የማይበልጥ ከሆነ ከሌሎች ጋር ለመነጋገር የምታደርገው ሙከራ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንብህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሜላቬ “በጣም የከበደኝ ነገር ቢኖር በምፈልግበት ጊዜ የምፈልገውን ሐሳብ መናገር አለመቻሌ ነው” በማለት በምሬት ተናግራለች። ነገር ግን እንዲህ ማድረግ አለመቻልህ የሚፈጥርብህ የእልህ ስሜት ራሱ ጥረትህን እንድትገፋበት ሊያነሳሳህ ይችላል። ማይክ ተሰምቶት የነበረውን ስሜት አስታውሶ ሲናገር “ተሞክሮዎችና ቀልዶች ሲነገሩ መረዳት አለመቻሌ በጣም ያበሳጨኝ ነበር። እንዲህ ያለው ስሜት እድገት ለማድረግ ይበልጥ እንድጣጣር የገፋፋኝ ይመስለኛል” ብሏል።

ሌሎች መርዳት የሚችሉበት መንገድ

ቋንቋውን መናገር የሚችሉ ሰዎች የሚማረውን ሰው ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቢል “በቀስታ ተናገሩ፤ ሆኖም ትንሽ ልጅ እንደሚናገረው ሳይሆን በትክክል ተናገሩ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ጁሊ ደግሞ “ቋንቋውን የሚማረው ሰው በሚናገርበት ጊዜ የጀመረውን ዓረፍተ ነገር እስኪጨርስ ታገሡት እንጂ እናንተ አትጨርሱለት” ትላለች። ቶኒም ያጋጠመውን ሁኔታ አስታውሶ ሲናገር “ሁለቱንም ቋንቋዎች የሚያውቁ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ማናገር ይቀናቸዋል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው እድገቴ አዝጋሚ እንዲሆን አድርጎት ነበር” ብሏል። በመሆኑም አዲስ ቋንቋ የሚማሩ አንዳንድ ሰዎች ጓደኞቻቸው በተወሰኑ ወቅቶች ላይ በአዲሱ ቋንቋ ብቻ እንዲያነጋግሯቸውና ማሻሻል ያለባቸውን ነገር እንዲጠቁሟቸው ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ተማሪዎች፣ ሰዎች ያደረጉትን ጥረት አንስተው ከልብ ሲያደንቋቸው ደስ ይላቸዋል። ጆርጅ “ከጓደኞቼ ፍቅርና ማበረታቻ ባላገኝ ኖሮ ሊሳካልኝ አይችልም ነበር” ብሏል።

ታዲያ ሌላ ቋንቋ መማር ይህን ያህል ሊለፋለት የሚገባው ነገር ነው? ብዙ ቋንቋዎችን የሚናገረውና ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቢል “እንዴታ!” በማለት መልሷል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ስለ ሕይወት ያለኝን አመለካከት አስፍቶልኛል፤ እንዲሁም ነገሮችን ከሌላ አቅጣጫ መመልከት እንድችል ረድቶኛል። በተለይም ደግሞ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት መቻሌና እውነትን ተቀብለው መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ማየቴ ድካሜን ሁሉ ያስረሳኛል። እንዲያውም አንድ 12 ቋንቋዎችን መናገር የሚችል ሰው በአንድ ወቅት ‘በጣም እቀናብሃለሁ። ምክንያቱም እኔ እነዚህን ቋንቋዎች የተማርኩት እንዲያው ደስ ስለሚለኝ ነበር፤ አንተ ግን የተማርከው ሰዎችን ለመርዳት ስትል ነው’ ብሎኛል።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድን ቋንቋ እንድንማር የሚያነሳሳን ኃይለኛው ግፊት ሌሎችን ለመርዳት ያለን ፍላጎት ነው