በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖር

የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖር

የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ መኖር

ምንጊዜም ቢሆን ስለ እሳተ ገሞራዎች እርግጠኛ ሆኖ መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። እሳተ ገሞራዎች ለዘመናት ምንም ጉዳት ሳያስከትሉ ከቆዩ በኋላ አስደናቂና ቀሳፊ በሆነ መልኩ ድንገት ሊፈነዱ ይችላሉ። የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አካባቢውን እንዳልነበረ ሊያደርግና ሕይወት ሊያጠፋ ይችላል።

እሳተ ገሞራዎች አደገኛ መሆናቸውን ማንም ሰው አይጠራጠርም። ባለፉት ሦስት መቶ ዘመናት ብቻ እንኳ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን የምንኖረው እንደነዚህ ካሉት አደገኛ አካባቢዎች ርቀን ነው። ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዱ በሚችሉ እሳተ ገሞራዎች አቅራቢያ ይኖራሉ። ለምሳሌ፣ የኢኳዶር ዋና ከተማ የሆነችው ኪቶ የምትገኘው ከከተማዋ በስተ ሰሜን ምዕራብ ካለው የፒቺንቻ ገሞራ ጥቂት ራቅ ብሎ ነው። በአዝቴክ ቋንቋ ስሙ “የሚጨስ ተራራ” የሚል ትርጉም ያለው ፖፖካቴፔትል የሚባለው ተራራ ከሜክሲኮ ሲቲ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ኒው ዚላንድ ውስጥ የምትገኘው ኦክላንድና የጣሊያኗ ኔፕልስም የተቆረቆሩት በእሳተ ገሞራዎች ላይ ወይም አጠገብ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩት በቆሙበት ምድር ከርስ ውስጥ ያሉት ኃይሎች በእሳተ ገሞራ መልክ ፈንድተው ሊወጡ በሚችሉበት አካባቢ ነው።

አደገኛ ተራራ

የኔፕልስ ከተማ ነዋሪዎች ቬሱቪየስ በተባለው ተራራ አጠገብ ለ3,000 ዓመታት ኖረዋል። ይህ ተራራ ከኔፕልስ በ11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ጥንታዊው የሞንቴ ሶማ ተራራ ቬሱቪየስ የግማሽ ክብ ቅርጽ እንዲኖረው አድርጎታል። ቬሱቪየስ በምድር ላይ ካሉ በጣም አደገኛ እሳተ ገሞራዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ተራራ ከላይ እንደሚታየው ትንሽ አይደለም፤ መነሻው ከባሕር ወለል በታች ስለሆነ በጣም ትልቅ ነው።

ቬሱቪየስ ከእሳተ ገሞራ ጋር በተያያዘ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ተራራ ነው። በ79 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፈንድቶ ፖምፔ እና ሄርኩላኒየም የተባሉትን ከተሞች ካጠፋበት ጊዜ ጀምሮ ከ50 ለሚበልጡ ጊዜያት ፈንድቷል። በ1631 በደረሰው ፍንዳታ 4,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እሳተ ገሞራው ሲፈነዳ የሚፈሰው ቅልጥ ድንጋይ “ላቫ” ተብሎ መጠራት የጀመረውም የዚያን ጊዜ ነው። ቃሉ “መንሸራተት” የሚል ትርጉም ካለው ላባይ ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን በቬሱቪየስ ተራራ ላይ ቁልቁል የወረደውን የቀለጠ ድንጋይ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ተስማሚ ስያሜ ነው።

ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ የቬሱቪየስ ተራራ በተደጋጋሚ ፈንድቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ማለትም በ1944 ፈንድቶ የኅብረ ብሔሩን ጦር አመድ አልብሶታል። በዚህ ፍንዳታ ተራራውን ለመውጣትና ለመውረድ ያገለግል የነበረው በካቦ ላይ የሚንቀሳቀስ መኪና በአመድ እንደተቀበረው ሁሉ በአቅራቢያው የሚገኙት ማሳ እና ሳን ሴባስትያኖ የተባሉት ከተሞችም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል። ይህ መኪና “ፉኒኩሊ ፉኒኩላ” በተባለው የጣሊያን ባሕላዊ ዘፈን ላይ ተወድሶ ነበር።

ዛሬም ቢሆን የኔፕልስ ነዋሪዎች አደጋ ባንዣበበበት በዚህ ቦታ ይኖራሉ። አገር ጎብኚዎች ታሪካዊ የሥነ ሕንጻ ጥበቦችን በማየት ይደመማሉ። ሱቆችና መዝናኛ ቦታዎች ገበያቸው ደርቶ የሚውል ሲሆን በኔፕልስ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ነጫጭ ጀልባዎችን ማየት የተለመደ ነው። የቬሱቪየስ ተራራም እንደ አደገኛ ቦታ ሳይሆን ምንም ጉዳት የማያደርስ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።

ኦክላንድ—እሳተ ገሞራዎች የሞሉባት ከተማ

የወደብ ከተማ በሆነችው በኦክላንድ፣ ኒው ዚላንድ እሳተ ገሞራ የፈጠራቸው ጉብታዎች በብዛት ይታያሉ። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ በ48 ትናንሽ እሳተ ገሞራዎች መካከል ይኖራሉ። በጥንት ጊዜ የፈነዱ እሳተ ገሞራዎች ደሴቶችን በፈጠሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሁለት ሰርጎድ ያሉ ቦታዎች በወደብነት ያገለግላሉ። ከሌሎቹ ደሴቶች ይልቅ ጎላ ብሎ የሚታየው የ600 ዓመት ዕድሜ ያለው ራንጊቶቶ ሲሆን ከቬሱቪየስ ጋር ተመሳሳይ ቅርጽ አለው። ለዚህ ደሴት መፈጠር ምክንያት የሆነው እሳተ ገሞራ በአቅራቢያው የምትገኘውን የማዉሪዎችን መንደር በአመድ ቀብሯል።

የኦክላንድ ነዋሪዎች እሳተ ገሞራ በበዛበት በዚህ አካባቢ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። በኦክላንድ እምብርት ላይ የሚገኘው ማዉንጋኪኪ ተብሎ የሚጠራው እሳተ ገሞራ የፈጠረው ጉብታ በዛሬው ጊዜ የሕዝብ መናፈሻና የበግ እርባታ የሚካሄድበት ቦታ ሆኖ ያገለግላል። እሳተ ገሞራ የፈነዳባቸው አንዳንድ ቦታዎች በአሁኑ ጊዜ ሐይቆች፣ መናፈሻ ቦታዎችና የስፖርት ሜዳዎች ሆነዋል። እንዲያውም አንደኛው መካነ መቃብር ነው። ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢውን በደንብ ማየት እንዲችሉ እሳተ ገሞራ በፈጠረው ከፍታ ቦታ ላይ መኖር ይመርጣሉ።

በኦክላንድ የመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች ማዉሪዎች ሲሆኑ ከ180 ዓመት በኋላ ደግሞ አውሮፓውያን በዚያ አካባቢ መኖር ጀምረዋል። እነዚህ ሰዎች አካባቢው ከዚያ ቀደም እሳተ ገሞራ የፈነዳበት ቦታ መሆኑ ያን ያህል አላሳሰባቸውም ነበር። እነርሱ የታያቸው በአካባቢው መሬት በቀላሉ መገኘቱ፣ ለባሕር ቅርብ መሆኑና የአፈሩ ለምነት ብቻ ነበር። እርግጥ ነው፣ በሌላም የምድር ክፍል እንደሚታየው እሳተ ገሞራ የፈነዳበት አካባቢ የሚኖረው መሬት ለም ነው። ለምሳሌ ያህል በኢንዶኔዥያ ጥሩ የሩዝ ምርት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል አንዳንዶቹ ንቅ ገሞራ ያለባቸው ቦታዎች ናቸው። በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ለእርሻ ሥራ በጣም ተስማሚ የሆነ አፈር ያላቸው እሳተ ገሞራ በፈነዳበት አካባቢ ያሉ ቦታዎች ናቸው። በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ወቅት በሚወጣ ቅልጥ ድንጋይ ተሸፍኖ የነበረ መሬት ሁኔታዎች ከተመቻቹለት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዕፅዋት ማብቀል ይችላል።

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘዴዎች

ብዙዎች ‘በእሳተ ገሞራ አቅራቢያ መኖር አደገኛ አይደለም እንዴ?’ ብለው ይጠይቃሉ። በእርግጥ አደገኛ ነው። ነገር ግን ሳይንቲስቶች የመሬት መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በቅርበት መከታተል የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም በዓለም ዙሪያ ንቅ ገሞራዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በትኩረት ይከታተላል። ይህም ጥሩ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ የተነደፈላቸውን ኔፕልስንና ኦክላንድን ይጨምራል። ሳይንቲስቶች ሳተላይቶችንና ርዕደ መሬት መኖሩን የሚጠቁሙ መሣሪያዎችን በመጠቀም በምድር ውስጥ የሚገኘውን የቅልጥ ድንጋይ ሁኔታ 24 ሰዓት ሙሉ ይከታተላሉ።

ቬሱቪየስ ቋሚ የሆነ ክትትል የሚደረግበት ተራራ ነው። የጣሊያን መንግሥት በ1631 የተከሰተው ዓይነት ከፍተኛ ፍንዳታ ቢከሰት ከአደጋው ለማምለጥ የሚያስችል ተጨማሪ ጥንቃቄ ለማድረግ የሚረዳ ዕቅድ ነድፏል። ተመራማሪዎች በአደጋው ቀጠና ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ መስጠትና የእሳተ ገሞራው ፍንዳታ ከመከሰቱ በፊት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መርዳት እንደሚቻል ይናገራሉ።

ሳይንቲስቶች በኦክላንድ የሚገኙ እሳተ ገሞራዎችን አንድ ጊዜ ብቻ ፈንድተው የሚያበቁ ከሚባሉት ወገን ይመድቧቸዋል። ይህም ሲባል ከዚህ ቀደም ፈንድተው የነበሩ እሳተ ገሞራዎች እንደገና አይፈነዱም ማለት ነው፤ ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ እሳተ ገሞራ በሌላ ቦታ ይፈነዳል። ተመራማሪዎች እንዲህ ያለው እሳተ ገሞራ ከመፈንዳቱ በፊት ለቀናት አንዳንድ ጊዜም ለሳምንታት የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚኖር ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ሰዎች ከአደጋው ለመሸሽ የሚያስችል ጊዜ ያስገኝላቸዋል።

አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አለመዘንጋት

ምንም እንኳ እሳተ ገሞራዎችን መከታተል ወሳኝ ሥራ ቢሆንም ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ ካልወሰዱ ምንም ዋጋ የለውም። በ1985 በኮሎምቢያ የአርሜሮ ከተማ ባለ ሥልጣናት ኔቫዶ ዴል ሩዪዝ የተባለው እሳተ ገሞራ እንደሚፈነዳ አስቀድሞ ተነግሯቸው ነበር። ተራራው ከመፈንዳቱ በፊት እስከ 50 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚሰማ ድምፅ እያወጣ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም የከተማዋ ነዋሪዎች ተረጋግተው እንዲቀመጡ ተነግሯቸው ነበር። በመጨረሻም ከተማዋ የድንጋይ ቅላጭ በዘነበባት ወቅት ከ21,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ የሚያጋጥመው ከስንት አንዴ ቢሆንም በፍንዳታዎች መካከል ያለው የተረጋጋ ጊዜ ለተጨማሪ ምርምር እንዲሁም ዝግጅት ለማድረግ ጥቅም ላይ ውሏል። ስለዚህ ያልተቋረጠ ክትትልና በቂ ዝግጅት ማድረግ ብሎም የአካባቢውን ሕዝብ ማስተማር የእሳተ ገሞራ አደጋ ባንዣበበበት አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ይረዳል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዝግጁ ሁን!

በድንገት ለሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ ዝግጁ ነህ? በአካባቢህ ምን ዓይነት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል እወቅ። ከቤተሰቦችህ አባላት ጋር ብትጠፋፋ እንኳ የት እንደምትገናኙ እንዲሁም የምትገኙበትን ቦታ ለማን እንደምታሳውቁ አስቀድማችሁ ወስኑ። ምግብ፣ ውኃ፣ የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ሣጥን፣ ልብስ፣ ሬዲዮ፣ ውኃ የማይገባው የእጅ ባትሪ፣ ትርፍ ባትሪ ድንጋዮችንና የመሳሰሉትን ጨምሮ ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር በአስቸኳይ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች ምንጊዜም ዝግጁ አድርጋችሁ አስቀምጡ። ለበርካታ ቀናት እንዳይቸግራችሁ እነዚህ ነገሮች በበቂ መጠን ቢኖሯችሁ ጥሩ ነው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎብኚዎች እሳተ ገሞራው በፈነዳበት በቬሱቪየስ ተራራ አናት ላይ ሲጓዙ

[ምንጭ]

©Danilo Donadoni/Marka/age fotostock

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቬሱቪየስ ተራራ አጠገብ የተቆረቆረችው ኔፕልስ የምትባለው የጣሊያን ከተማ

[ምንጭ]

© Tom Pfeiffer

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰዓሊ ቬሱቪየስ በ79 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፈንድቶ ፖምፔ እና ሄርኩላኒየም የተባሉ ከተሞችን ባጠፋበት ወቅት ተፈጽሟል ብሎ ያሰበውን ሁኔታ የሚያሳይ ስዕል

[ምንጭ]

© North Wind Picture Archives

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኦክላንድ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሳቢያ ከተፈጠሩት በርካታ ደሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው የራንጊቶቶ ደሴት

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ እና በስተ ቀኝ:- የፖፖካቴፔትል ተራራ፣ ሜክሲኮ

[ምንጭ]

AFP/Getty Images

Jorge Silva/AFP/Getty Images

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

USGS, Cascades Volcano Observatory