በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተወዳጅ የቤት እንስሳ ወይስ ጨካኝ አውሬ?

ተወዳጅ የቤት እንስሳ ወይስ ጨካኝ አውሬ?

ተወዳጅ የቤት እንስሳ ወይስ ጨካኝ አውሬ?

ፖላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሶምሶማ በመሮጥ ላይ የነበረ አንድ ሰው ኃይለኛ በሆነ ውሻ በደረሰበት ንክሻ ምክንያት ብዙ ደም ስለፈሰሰው ሕይወቱ አለፈ። አንዲት ትንሽ ልጅ የሮትዋይለር (የጀርመን) ዝርያ ባለው ውሻዋ ተገደለች። ሌላ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ወላጆቹ እያዩት አንድ በመቅበዝበዝ ላይ የነበረ የጀርመን ሼፐርድ (ፖሊሶችና ዓይነ ስውራን የሚጠቀሙበት የውሻ ዝርያ) ባደረሰበት ከባድ ጉዳት ለሞት ተዳረገ። እነዚህ ጥሩ ዝርያ አላቸው የሚባሉ ውሾች በፖላንድ ከፈጸሟቸው አሰቃቂ ድርጊቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ አደጋዎችን ለመከላከል ሲባል በአንዳንድ ቦታዎች ያሉ ባለሥልጣናት ሰዎች የተወሰነ ዝርያ ያላቸውን ውሾች እንዲያሳድጉ የሚፈቅዱላቸው የፈቃድ ወረቀት ከተሰጣቸው በኋላ ብቻ ነው። ሆኖም የፖላንድ የውሾች ጥበቃ ማህበር አባል የሆኑት ባርባራ ዛሌስካ የተባሉ ሴት “ማስቲፍ፣ ሮትዋይለርም ሆነ ቡልቴሪየር የተባሉት የውሻ ዝርያዎች ወደ አውሬነት እንዲለወጡ አሊያም ገራም እንዲሆኑ የሚያደርገው ባለቤቱ በመሆኑ” የፈቃድ ወረቀት የሚያስፈልገው ውሻው ሳይሆን ባለቤቱ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

አንዳንድ ጊዜ ውሾች አውሬ እንዲሆኑ ሆን ተብሎ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። አሠልጣኙ ውሻውን በመምታት፣ በማስራብ ከዚያም አልፎ አሻንጉሊቶችን እንዲነክስና እንዲበጣጥስ በማስተማር “የግድያ ሥልጠና” ይሰጠዋል። ቀጥሎም ውሻው እንዲሞቱ በሚፈለጉ ደካማ ውሾች ላይ ጥቃት መሰንዘር ይማራል። ሥልጠናው ሲያበቃ ውሻው ቁማርተኞችንና የጭካኔ ድርጊቶችን መመልከት የሚያስደስታቸውን ተመልካቾች ለማዝናናት ሲባል በውሾች መካከል በሚደረጉ ፍልሚያዎች ላይ ለመካፈል ዝግጁ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በእንስሳት ላይ ስለሚፈጸም የጭካኔ ተግባር ምን እንደሚሰማው በግልጽ አስፍሯል። እንዲህ ይላል:- “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።” (ምሳሌ 12:10) አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ እንስሳትን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ አይዟቸውም። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለስፖርትም ሆነ ለሌላ ለማንኛውም ምክንያት ሲባል እንስሳት ጨካኝ አውሬ እንዲሆኑ ማሠልጠን የሚቀር መሆኑን ማወቃችን ያስደስታል።​—⁠መዝሙር 37:9-11