በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕክምና ምርጫህ

የሕክምና ምርጫህ

የሕክምና ምርጫህ

ዶክተር ኢዘዶር ሮዘንፌልድ ስለ አማራጭ ሕክምና ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ነጥብ ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል:- “እንዲሁ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው አንድ ዓይነት ሕክምና ቢደረግላቸውና ‘እንደሚሠራላቸው’ ማረጋገጫ ቢሰጣቸው ሕክምናው እስከ ግማሽ በሚደርሱት ላይ ውጤት ይኖረዋል።”

ይህ ዓይነቱ ውጤት በእንግሊዝኛ ፕላሴቦ ኢፌክት ሲባል ሰውዬው ካመነበት በክኒን መልክ የተዘጋጀ ስኳር ሳይቀር ሊያድነው ይችላል ማለት ነው። ፕላሴቦ ኢፌክት እንደ ማጥወልወል፣ ድካም፣ መጫጫን፣ ጭንቀት እና ድብታ የመሳሰሉትን ውጫዊ የሆኑ የሕመም ምልክቶች ሊያስታግስ ይችላል። ይህ እውነታ ምን ነገር ያረጋግጥልናል?

በአንደኛ ደረጃ አንድ ሰው የሚሰጠው ሕክምና ያድነኛል የሚል የእርግጠኝነት ስሜት ያለው መሆኑ ብዙውን ጊዜ በጤናው መሻሻል ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያሳያል። ቢሆንም የምንወስደው ሕክምና ችግሩን ከሥሩ ነቅሎ የሚያስወግድ እንጂ ውጫዊ የሕመም ምልክቶችን ብቻ የሚያስታግስ አለመሆኑን ማረጋገጡ ጥበብ ይሆናል። ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ እንደ ላቦራቶሪና ራጅ ባሉት ተጨባጭ መንገዶች የምርመራውን ውጤት ማየት ሲቻል ነው።

ይሁንና አንድ ሰው አንድ ዓይነት ሕክምና በሚመርጥበት ጊዜ ሊያደርገው የሚችለው ከዚህ የበለጠ ነገር አለ።

መወሰድ ያለባቸው አስፈላጊ እርምጃዎች

አንድ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት በቂ ጥናት ማድረግ ጥበብ ነው። ጥያቄዎች ጠይቅ። ምን ውጤት መጠበቅ ይቻላል? ጥቅሙና ጉዳቱ እንዲሁም የሚጠይቀው ወጪና ሕክምናው የሚወስደው ጊዜ ምን ያህል ነው? ይህን ዓይነት ሕክምና ከወሰዱ ሰዎች ጋር ተነጋገር። ሕክምናው ረድቷቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ጠይቃቸው። ይሁን እንጂ ከሰዎች አፍ የሚገኘው መረጃ ብቻውን ሊያሳስት እንደሚችል አትዘንጋ።

አንድ መደበኛ ያልሆነ ሕክምና አንድን ሰው በጣም የተሳካ ነው ባይባልም መጠነኛ መሻሻል እንደሚያስገኝ የሚታወቀውን መደበኛ ሕክምና እንዲያቋርጥ የሚያስገድደው ከሆነ መደበኛ ያልሆነውን ሕክምና መምረጡ የሚደገፍ አይሆንም። ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን የተባለ መጽሔት ላይ በማስረጃ ቀርቧል። መጽሔቱ ሁለት ወጣት ታካሚዎች አማራጭ ሕክምናዎችን ለመጠቀም ሲሉ መደበኛውን ሕክምና ለመከታተል ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ካንሰሩ በሰውነታቸው እንደተሠራጨ ገልጿል። እንዲያውም አንደኛው ሕይወቱን አጥቷል።

ሥር የሰደደ ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ሕመም ያለባቸው ሰዎች የሐሰት ሕክምናዎችን ለሚያካሂዱ አጭበርባሪዎች ሲሳይ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ ንቁ መሆናቸው ጥበብ ይሆናል። የተለያዩ ዓይነት የጤና ችግሮችን ይፈውሳል የሚባልላቸውን መድኃኒቶች በጥንቃቄ መርምሩ። ለዚህ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ የሚሆነን “ከአተነፋፈስ ችግርና ከአቅም ማነስ አንስቶ ለሕይወት አስጊ እስከሆኑ ሕመሞች ድረስ የመፈወስ ኃይል አለው” የተባለለት አንድ አዲስ ቪታሚን ነው። በዚሁ “ቪታሚን” ላይ የተካሄደ ምርመራ ግን ጨዋማ ውኃ እንጂ ሌላ ነገር እንዳልሆነ አረጋግጧል።

አንዳንድ አማራጭ ሕክምናዎች ለጥሩ ጤና የሚረዱ እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ለማግኘት ስለምትጠብቁት ውጤት ሚዛናዊ መሆን አለባችሁ። ገንቢ ምግብ በመመገብ፣ በቂ እንቅልፍ በመተኛት፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም የምንወስደውን የሕክምና ዓይነት በጥንቃቄ በመምረጡ ላይ ማተኮሩ ጥበብ ይሆናል።

ሕልሙ እውን ሲሆን

ሁሉንም ዓይነት ሕመምና በመጨረሻም ሞትን ሊያስቀር የሚችል አንድም የሰው ልጅ ሕክምና የለም። ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ከመጀመሪያው አባታችን ከአዳም የተወረሱ ነገሮች በመሆናቸው ነው። (ኢዮብ 14:​4፤ መዝሙር 51:​5፤ ሮሜ 5:​12) ብዙ የሕክምና ዓይነቶች ጠቃሚ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። ይሁንና ሕይወትን ከማራዘምና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ደህና ኑሮ እንዲኖር በማድረግ ለጊዜው እንደ ማስታገሻ ከማገልገል አያልፉም። ይሁን እንጂ ለጤና ችግሮች አስተማማኝ ፈውስ የሚገኝበት መንገድ አለ። ዛሬም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ዘዴ አውቀውታል።

ይህን ፈውስ ያዘጋጀው ታላቁ ሐኪም ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው። በእርሱ በማመንና ኃጢአትን በሚያነጻው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በመጠቀም ከሕመም ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት ልታገኝ ትችላለህ! (ማቴዎስ 20:​28) መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ “የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም” የሚል ተስፋ ይሰጣል።​—⁠ኢሳይያስ 33:​24

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፍጹም ጤና የሚገኝበትን ብቸኛ አስተማማኝ ተስፋ አግኝተዋል