በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

የቆሸሸ ገንዘብ

የለንደን ባንክ ካሰራጨው የገንዘብ ኖቶች መካከል 99 በመቶ የሚሆኑት ኮኬይን በተባለው ዕፅ የተበከሉ ወይም የቆሸሹ እንደሆኑ ጋርዴያን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ኤክስፐርቶች 500 በሚሆኑ የገንዘብ ኖቶች ላይ ምርመራ አድርገው 496 የሚሆኑት አደገኛ ዕፅ የነካቸው እንደሆኑ አረጋግጠዋል። ኖቶቹ በዕፆቹ መበከል የሚጀምሩት በዕፅ ተጠቃሚዎች በሚያዙበት ጊዜ ነው። እነዚህ ኖቶች በተራቸው በባንክ ማሽኖች በሚቆጠሩበት ወይም አንድ ላይ ሆነው በሚቀመጡበት ጊዜ ሌሎች ኖቶችን በንክኪ ይበክላሉ። በብሪታኒያ ኮኬይን ከ20 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች መካከል እጅግ እየተስፋፋ የሄደ የመዝናኛ ዕፅ ሆኗል። ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነው የወጣቶች ግንዛቤ ፕሮጄክት እንዳስገነዘበው በአፍላ የጉርምሥና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ኮኬይንን የሚወስዱት ዝናቸውን የሚያስፋፋላቸውና ኃይላቸውን የሚጨምርላቸው ስለሚመስላቸው ነው።

“በጣም የተለመደ ደም ወለድ ኢንፌክሽን”

አሶሲዬትድ ፕሬስ እንደዘገበው “2.7 ሚልዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን የሄፕታይትስ ሲ ቫይረስ ተሸካሚዎች ሲሆኑ በዚህ ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ በስርጭቱ በአንደኛነት የሚገኝ ደም ወለድ ኢንፌክሽን ሊሆን ችሏል። ሄፓታይትስ ሲ በዋነኛነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በወሲባዊ ግንኙነት ወይም በተበከለ ደም አማካኝነት ነው። ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ የሚጋለጡት የኅብረተሰብ ክፍሎች አንድ መርፌ በመጋራት አደገኛ ዕፆችን የሚወስዱና አለምንም መከለያ ወሲባዊ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በተጨማሪም ኢንፌክሽኑ የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎች በሚገባ በማያጸዱ ነቃሾችና አኩምፓክቸሪስቶች ሊተላለፍ ይችላል። ደም የወሰዱ ሰዎችም ለዚሁ አደጋ ይጋለጣሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ 1, 000 የሚያክሉ ሰዎች ጉበታቸው በቫይረሱ ከጥቅም ውጭ ስለሚሆን በቀዶ ሕክምና ሌላ ጉበት ይተካላቸዋል።

ዛሬ ጊዜ የለም

በመላው አውሮፓ ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በሩጫ የተሞላ ሕይወት እንደሚመሩ ጌሰን አልገማይነ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። ከቤት ውጭ የሚሠሩም ሆኑ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚሠሩ ወይም በዕረፍት ጊዜያቸው እየተዝናኑ ያሉ ሰዎች ሁሉም ጊዜ ያጥራቸዋል። የባምበርግ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂስት የሆኑት ማንፍሬድ ጋርሃም “ሰዎች ጥቂት ይተኛሉ፣ በጥድፊያ ይበላሉ እንዲሁም ከ40 ዓመት በፊት ከነበረው ይልቅ ዛሬ በሥራ ላይ በጣም ይዋከባሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ጥናታቸውን ባካሄዱባቸው የአውሮፓ አገሮች በሙሉ የዕለት ተዕለት ኑሮ ሩጫ የበዛበት እየሆነ መምጣቱን ሊገነዘቡ ችለዋል። ጉልበት ቆጣቢ የሆኑ የቤት ውስጥ መሣሪያዎች መኖራቸውና የሥራ ሰዓት መቀነሱ “የተዝናና ኅብረተሰብ” ወይም “የተትረፈረፈ ጊዜ” ማስገኘት አላስቻሉም። ከዚያ ይልቅ በአማካይ ምግብ ለመመገብ የሚወስደው ጊዜ በ20 ደቂቃ እንዲሁም የሌሊት እንቅልፍ በ40 ደቂቃ ተቀንሷል።

ሕፃናትና ቴሌቪዥን

የአሜሪካ የሕፃናት አካዳሚ ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ቴሌቪዥን መመልከት የለባቸውም ሲል መግለጹን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሚኖረው የአንጎል ዕድገት ላይ የተካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ሕፃናት ከወላጆቻቸውና እንክብካቤ ከሚያደርጉላቸው ሌሎች ሰዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል። ቴሌቪዥን መመልከት “ለማኅበራዊ፣ ለስሜትና ለአእምሮ ዕድገት የሚ​ረዳቸውን ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ሊያስተጓጉልባቸው” ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ አባባል የሚስማሙት ሁሉም ጠበብት አይደሉም። ለምሳሌ ያህል የካናዳ የሕፃናት ሕክምና ማኅበር ጥሩ ፕሮግራም በማውጣት በወላጅ ክትትል በቀን ውስጥ ከ30 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት ሕፃኑ “በወላጁ መማር የሚችልበትን አጋጣሚ” ይከፍትለታል ይላል። ይሁን እንጂ ሕፃናት ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒዩተር መኝታ ቤታቸው ውስጥ ሊኖራቸው እንደማይገባና ቴሌቪዥን እንደ ሞግዚት ሆኖ ማገልገል እንደሌለበት ሁለቱም ድርጅቶች ይስማማሉ። ቴሌቪዥን መመልከት የልጆችን ጤንነት ሊያውክ የሚችል በመሆኑ “ልጆች ውጪ እንዲጫወቱ፣ መጻሕፍት እንዲያነቡ ወይም የተበታተነ ምስል መልሶ መገጣጠምን የመሰሉ አእምሮ የሚያሠሩ ጨዋታዎች እንዲጫወቱ ማበረታታት” ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክቷል።

በሥራ ቦታ መበሳጨት

አንዳንድ ሰዎች በሥራ ቦታ በጣም የሚበሳጩት አልፎ ተርፎም ጠበኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? የቶሮንቶው የሥነ ልቦና ባለሙያ ሳም ክላራይክ እንዳሉት ከሆነ ምክንያቱ ውጥረት ብቻ ሳይሆን ቶሎ ግንፍል የማለት ችግርም ሊሆን ይችላል። እንደ ክላራይክ እምነት ይህ ሁኔታ “ከልክ በላይ እንዲሠሩ ከተደረጉ በኋላ ከሠሩት ሥራ ጋር የማይመጣጠን ክፍያ በሚያገኙ” አንዳንድ ሠራተኞች ላይ ይከሰታል ይላል ግሎብ ኤንድ ሜይል የተሰኘው ጋዜጣ። ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ቁጣ ስትሮክ ወይም ልብ ድካም ሊያስከትል የሚችል “አደገኛ ስሜት ነው” ሲሉ ክላራይክ ያስጠነቅቃሉ። ሠራተኞች ሊያበሳጩ የሚችሉ ነገሮችን መቀበል መቻልንና አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን የሥራ መጠን በተመለከተ ከአሠሪዎቻቸው ጋር ቁጭ ብለው በረጋ መንፈስ መወያየትን መማር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አሠሪዎች ቶሎ የመገንፈል ጠባይ ያለባቸው የሚመስሉ ሠራተኞቻቸውን በንቃት እንዲከታተሉና ተጨማሪ እርዳታ እንዲያደርጉላቸው፣ ሸክማቸውን በተወሰነ ደረጃ እንዲያቀሉላቸው ወይም ዕረፍት እንዲወስዱ ሐሳብ እንዲያቀርቡላቸው ክላራይክ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የሰብል ስርቆት

በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች የሰብል ስርቆት እየጨመረ በመምጣቱ ገበሬዎች መማረራቸውን ዚገነ ሳይቱንግ ዘግቧል። ሌቦች ኪዩከምበር በባሊ እየሞሉና የአስፓራገስ ተክሎችን በመኪናዎቻቸው ውስጥ እያጨቁ ይወስዳሉ። በአንድ ወቅት 7, 000 የእንጆሪ ተክሎችን ሰርቀዋል። ምንም እንኳ አንዳንዶች የሚሰርቁት ባለባቸው አስከፊ የገንዘብ ችግር ቢሆንም ሌሎቹ ግን እንዲሁ ደስ ስለሚላቸው ብቻ የሚያደርጉት ይመስላል። ገበሬዎች ዝርፊያው በሚካሄድባቸው የእርሻ ቦታዎች አቅራቢያ “ሁሉንም ዓይነት መኪናዎች” እንደሚመለከቱ ሪፖርት አድርገዋል። ብዙውን ጊዜ የእርሻ ቦታዎቹ ከባለቤቶቹ መኖሪያዎች ርቀው የሚገኙ ሲሆን ሌቦቹ በእነዚህ የእርሻ ቦታዎች ለመስረቅ የበለጠ ድፍረት ያገኛሉ። አንድ አማካሪ ገበሬዎች ሌቦቹን ለማሳነፍ ሰብሎቻቸውን በፍግ እንዲሸፍኑ ሐሳብ አቅርበዋል።

ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ረጅም ዕድሜ ሊኖሩ ይችላሉ

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ አንድ አዲስ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ምግብ ቤት፣ የስፖርት ውድድር ወደሚካሄድባቸው ቦታዎችና ወደ ሲኒማ ቤቶች መሄድን በመሳሰሉ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ የሚያደርጉ አረጋውያን ብዙም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ሰዎች በአማካይ በሁለት ዓመት ተኩል የበለጠ ዕድሜ ይኖራሉ። ሰዎችን የረዳቸው ነገር በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት የሚያደርጉት አካላዊ እንቅስቃሴ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር ይላሉ የሃርቫርድ ባልደረባ የሆኑትና ጥናቱን የመሩት ቶማስ ግላስ። ይሁን እንጂ ይህ ጥናት “በሕይወት መገባደጃ ላይ ትርጉም ያለው ዓላማ ይዞ መንቀሳቀስ መቻል ዕድሜን እንደሚያራዝም የሚጠቁም እስከ ዛሬ ካገኘናቸው መረጃዎች ሁሉ የላቀ ጠንካራ ማስረጃ ሳይሆን አይቀርም” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። ግላስ እንዳሉት ከሆነ እንቅስቃሴው ምንም ይሁን ምን የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ማለት ይቻላል፣ ዕድሜን ለማራዘም ይረዳል።

ብልህ የሆኑ ወፎች!

ቴር ሶቫዥ የተባለው የፈረንሳይኛ የተፈጥሮ መጽሔት “በካልካታ የሚገኙ ድንቢጦች ራሳቸውን ከወባ የሚከላከሉበት ዘዴ አላቸው” ሲል ዘግቧል። ጠበብቶች እንደተገነዘቡት በአሁኑ ጊዜ ወባ በጣም እየተስፋፋ በመሄዱ ድንቢጦች ራቅ ወዳለ ሥፍራ እየበረሩ የወባ መድኃኒት የሆነው ኲኒን የተባለ ቅመም በከፍተኛ መጠን የሚገኝበትን የአንድ ዛፍ ቅጠል ይፈልጋሉ። ቅጠሎቹን በጎጆአቸው ውስጥ ከመጎዝጎዛቸው በተጨማሪ ይበሏቸዋል። መጽሔቱ እንዳለው “የከተማውን ኑሮ የወደዱ ወፎች ራሳቸውን ከወባ የሚከላከሉበትን ዘዴ ያገኙ ይመስላል።”

ጥንታዊዎቹ የዓለማችን የመርከብ አደጋዎች

የሥነ ውቅያኖስ ባለሙያዎች በ750 ከዘአበ ገደማ የነበሩ ሁለት የፊንቄያውያን ጀልባዎች ስብርባሪዎችን ማግኘታቸውን ስዮንስ ኤ አቨኒር የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት ዘግቧል። በእስራኤል የባሕር ዳርቻ 500 ሜትር ገደማ የሚሆን ጥልቀት ላይ የተገኙት 15 እና 18 ሜትር የሚሆኑት ጀልባዎች በውቅያኖስ ውስጥ ከተገኙት መርከቦች ሁሉ እጅግ ጥንታውያን ናቸው። ጀልባዎቹ የወይን ማሰሮዎች ጭነው ከጢሮስ ወደብ በመነሳት ወደ ግብፅ ወይም በሰሜን አፍሪካ ወደምትገኘው ካርቲጅ ከተማ በማምራት ላይ የነበሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። መርከቦቹን ያገኙት ሮበርት ባላርድ “የውቅያኖሶች ከፍተኛ ጥልቀት፣ የፀሐይ ብርሃን አለመኖርና ያለው ከፍተኛ ግፊት ታሪክን እኛ ካሰብነው በላይ በሚገባ ጠብቆ ያቆየው ይመስላል” ሲሉ መናገራቸውን ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን ጠቅሶ ዘግቧል። ተመራማሪዎቹ ይህ ግኝት “በዚህ ጥንታዊ የባሕር ላይ ጉዞ ሥልጣኔ ላይ በሚካሄደው ምርምር ሙሉ በሙሉ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ሊረዳ ይችላል” ብለዋል።

ዘና ለማለት ቀዳሚው ምርጫ

በቅርቡ በተካሄደ አንድ ጥናት በ30 የተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 1, 000 ሰዎች ውጥረትን ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ምን መጠቀም እንደሚመርጡ ተጠይቀው ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል 56 በመቶዎቹ የመጀመሪያ ምርጫቸው ሙዚቃ ሆኖ መገኘቱን ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። በሰሜን አሜሪካ 64 በመቶዎቹ ሙዚቃን በግንባር ቀደምትነት የመረጡ ሲሆን በበለጸገው የእስያ ክፍል ከሚገኙት መካከል ሙዚቃን የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደረጉት 46 በመቶዎቹ ናቸው። በጥቅሉ ሲታይ ቴሌቪዥን መመልከት በሁለተኛነት ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ገላን መታጠብ ሦስተኛውን ደረጃ ይዟል። “ሙዚቃ የሚጠይቀውን ዋጋ እንዲሁም በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በግል ሲ ዲ ማጫወቻዎች፣ በኢንተርኔትና በሌሎች በርካታ አዳዲስ መንገዶች በቀላሉ ሊገኝ የሚችል መሆኑን ቆም ብላችሁ ስታስቡ ከዓለማችን ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ራሱን ዘና ለማድረግ ሙዚቃ የሚያዳምጥ መሆኑ ምንም አያስገርማችሁም” ሲሉ በሮፐር ስታርች ዎርልድዋይድ ድርጅት የተካሄደው ጥናት ዲሬክተር የሆኑት ቶም ሚለር ተናግረዋል።