በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደንብ የተደበቀ ምሥጢር

በደንብ የተደበቀ ምሥጢር

በደንብ የተደበቀ ምሥጢር

“ማንም ሰው ባሪያ እንዲሆን ወይም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አይደረግም። ማንኛውም ዓይነት ባርነትና የባሪያ ንግድ መወገድ አለበት።” ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ

በሚቀጥለው ጊዜ ቡናህ ውስጥ ስኳር ስትጨምር ፕሬቮ ስለተባለው የሃይቲ ተወላጅ ለማሰብ ሞክር። ፕሬቮ በሌላ የካሪቢያን አገር ጥሩ ሥራ እንደሚያገኝ ቃል ተገብቶለት የነበረ ቢሆንም በስምንት ዶላር የመሸጥ ዕጣ የገጠመው ሰው ነው።

ፕሬቮ እንደ እሱ ያሉ በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁና አነስተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው አለዚያም ያላንዳች ክፍያ ለስድስት ወይም ለሰባት ወራት ሸንኮራ አገዳ እንዲቆርጡ ከሚገደዱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአገሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ ግዞተኞች በተጨናነቀና በሚቀፍ ሁኔታ የሚኖሩ ናቸው። ንብረታቸውን ሁሉ ከተገፈፉ በኋላ ቆንጨራ ይሰጣቸዋል። የሚበሉት ምግብ ለማግኘት የግድ መሥራት አለባቸው። ለማምለጥ ከሞከሩ ሊደበደቡ ይችላሉ።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትኖረውን ሊን-ሊን የተባለች ልጃገረድ ሁኔታም ተመልከት። ሊን-ሊን እናቷ ስትሞት የ13 ዓመት ልጅ ነበረች። አንድ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ጥሩ ሥራ እንደሚያስይዛት ቃል በመግባት ከአባቷ ላይ በ480 የአሜሪካ ዶላር ገዛት። የተከፈለው ዋጋ እንደ “ቅድሚያ ክፍያ” ተደርጎ የተወሰደ በመሆኑ አዲሶቹ ባለቤቶቿ ለዘለቄታው በእነሱ ሥር እንድትሆን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቸው ነበር። ሊን-ሊን ጥሩ ሥራ ለማግኘት አልታደለችም። ከዚህ ይልቅ ወደ ሴተኛ አዳሪዎች ቤት ተወሰደች። ወደዚያ የሚመጡ ደንበኞች ከእሷ ጋር ለሚያደርጉት የአንድ ሰዓት ቆይታ ለባለቤቷ 4 የአሜሪካ ዶላር ይከፍላሉ። ሊን-ሊን ያለባትን ዕዳ እስካልከፈለች ድረስ ሥራዋን ጥላ መሄድ ስለማትችል ያለችበት ሁኔታ ከእስር ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ዕዳው ደግሞ ወለዱንና የሴተኛ አዳሪዎቹ ባለቤት ለእሷ የሚያወጣውን ወጪ የሚጨምር ነው። ሊን-ሊን ከአሠሪዋ ፈቃድ ጋር ተስማምታ ለመኖር አሻፈረኝ ካለች ልትደበደብ ወይም ሥቃይ ሊደርስባት ይችላል። ከዚህ ይበልጥ የከፋው ደግሞ ለማምለጥ ብትሞክር ልትገደል የምትችል መሆኑ ነው።

ነፃነት ለሁሉም?

አብዛኞቹ ሰዎች ባርነት ሙሉ በሙሉ ተወግዷል የሚል እምነት አላቸው። እንዲያውም ከበርካታ ስምምነቶች፣ ድንጋጌዎችና ውሳኔዎች በኋላ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ባርነት እንደተወገደ በይፋ ተነግሯል። ባርነት በሁሉም ቦታ ክፉኛ ሲወገዝ ይደመጣል። ብሔራዊ ሕጎች ባርነትን ያገዱ ሲሆን በዓለም አቀፋዊ ሰነዶች በተለይም ከላይ በተጠቀሰው በ1948 በወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ 4ኛ አንቀጽ አማካኝነት ውሳኔው ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።

ሆኖም ለአንዳንዶች በጣም የተደበቀ ምሥጢር ቢሆንባቸውም እንኳ ባርነት አሁንም ሕያው ከመሆኑም በላይ በደንብ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ከፕኖም ፔን እስከ ፓሪስ እንዲሁም ከሙምባይ እስከ ብራዚሊያ በሚልዮን የሚቆጠሩ እንደ እኛው ያሉ ሰዎች ማለትም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ባሪያዎች ሆነው ወይም ከባርነት ባልተለየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመኖርና ለመሥራት ተገድደዋል። መቀመጫውን ለንደን ያደረገው በግዳጅ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎችን ጉዳይ የሚከታተለው ቀደምትነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የፀረ-ባርነት ድርጅት በባርነት ቀንበር ሥር የወደቁት ሰዎች ቁጥር በመቶ ሚልዮን እንደሚቆጠር ገምቷል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ከምንጊዜውም የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል!

እርግጥ ነው፣ እንደ እግር ብረት፣ ጅራፍና ባሪያዎችን አጫርቶ እንደ መሸጥ ያሉ የተለመዱት የባርነት ገጽታዎች የዘመናዊው ባርነት ዓይነተኛ መለያዎች አይደሉም። በዛሬው ጊዜ ይበልጥ የሚታወቁት የባርነት ዓይነቶች በግዳጅ የሚፈጸም ሥራን፣ ከባርነት ተለይቶ የማይታይ የትዳር ሕይወትን፣ በዕዳ ሳቢያ በባርነት ቀንበር ሥር መውደቅን፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛንና ብዙውን ጊዜም ዝሙት አዳሪነትን የሚጨምሩ ናቸው። ባሪያዎቹ ቁባቶች፣ የግመል ግልቢያ ተወዳዳሪዎች፣ ሸንኮራ አገዳ ቆራጮች፣ ምንጣፍ ሸማኔዎች ወይም በመንገድ ግንባታ ላይ የተሠማሩ ግንበኞች ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ በሕዝብ ፊት በተካሄደ ጨረታ የተሸጡ አይደሉም። ሆኖም ያሉበት ሁኔታ ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩት ባሪያዎች የተሻለ አይደለም። እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ሲታይ ይበልጥ አሳዛኝ ነው።

ባሪያዎች የሆኑት እነማን ናቸው? ለባርነት የተዳረጉትስ እንዴት ነው? እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ምን እየተደረገ ነው? ባርነት ሙሉ በሙሉ የሚወገድበት ጊዜ ቀርቧል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዘመናዊ ባርነት ምንድን ነው?

ይህ ጥያቄ የተባበሩት መንግሥታት እንኳ ሳይቀር ከብዙ ዓመታት ጥሮሽ በኋላም አጥጋቢ መልስ ሊሰጥበት ያልቻለ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። አንዱ የባርነት ፍቺ በ1926 ባርነትን አስመልክቶ በተካሄደው ስምምነት ላይ የተገለጸው ሲሆን “ባርነት የባለቤትነት መብት ያለው ኃይል ወይም ኃይሎች የሚሰለጥኑበት ሰው የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው” ይላል። ሆኖም ቃሉ አሁንም ተጨማሪ ፍቺ ሊሰጥበት ይችላል። ጋዜጠኛዋ ባርብራ ክሮሴት እንዳሉት ከሆነ “ባርነት ውጪ አገር በሚገኙ የልብስ ኢንዱስትሪዎችና በአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ባሉ ፋብሪካዎች ውስጥ በአነስተኛ ደሞዝ የሚሠሩ ሠራተኞችን የሚያመለክት ቃል ነው። የወሲብ ኢንዱስትሪንና የእስረኞች ጉልበት ብዝበዛን ለማውገዝ ይሠራበታል።”

የዓለም አቀፋዊው የፀረ-ባርነት ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ማይክ ዶትሪጅ “ባርነት አዲስ መልክ እየያዘ የመጣ በሚመስልበት ጊዜ ወይም ደግሞ ቃሉ ለሌሎች ሁኔታዎችም ሲሠራበት ትርጉሙ ሊደበዝዝ አልፎ ተርፎም እየጠፋ ሊሄድ ይችላል” የሚል እምነት አላቸው። እንደ እሳቸው እምነት “ባርነት በሌላ ሰው የባለቤትነት መብት ወይም ቁጥጥር ሥር ያለን ሕይወት ያመለክታል።” ኃይል መጠቀምንና እንቅስቃሴን መገደብን ማለትም “አንድ ሰው ለቅቆ ለመሄድና አሠሪውን ለመቀየር ያለውን ነፃነት መንፈግን” የሚጨምር ነው።

ኤ ኤም ሮዘንታል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ባሪያዎች የባርነት ኑሮ ይገፋሉ። በጭቆና ቀንበር ሥር ሆነው ይሠራሉ፣ ተገድደው ይደፈራሉ፣ ይራባሉ፣ ሥቃይ ይደርስባቸዋል፣ ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነገር ሁሉ ይፈጸምባቸዋል።” አክለውም “አንድ ባሪያ በሀምሳ ዶላር የሚገዛ በመሆኑ [ባለቤቶቹ] አስከሬኑ አንድ ወንዝ ውስጥ ከመጣሉ በፊት ባሪያው ረጅም ዕድሜ ኖረ አልኖረ ግድ አይሰጣቸውም” ብለዋል።

[ምንጭ]

Ricardo Funari