በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስገራሚው የሦስት አፅቄዎች ዓለም

አስገራሚው የሦስት አፅቄዎች ዓለም

አስገራሚው የሦስት አፅቄዎች ዓለም

ስፔይን የሚገኘው የንቁ ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ሦስት አፅቄዎች (insects) ችግር ፈጣሪ እንደሆኑ አድርገህ ብቻ ነው የምትመለከታቸው? ዓለማችን ከእነዚህ የሚያውኩ ተባዮች የጠራች እንድትሆን ትመኛለህ? ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ትነፋባቸዋለህ፣ ባገኘኸው ነገር ትመታቸዋለህ ወይም ደግሞ ትረግጣቸዋለህ? ባየኸው ተባይ ሁሉ ላይ ጦርነት ከማወጅህ በፊት ስለ ሦስት አፅቄዎች ዓለም ትንሽ ለመማር ለምን አትሞክርም? ለእያንዳንዱ ሰው 200, 000, 000 ገደማ የሚደርሱት ሦስት አፅቄዎች ወደድንም ጠላን አብረውን መኖራቸው አይቀሬ ነው!

ከእነዚህ አስደናቂ ፍጥረታት መካከል አንዳንዶቹን በጥቂቱ ቀረብ ብሎ መመልከቱ ሦስት አፅቄዎች አክብሮት ሊሰጣቸው የሚገቡ ፍጥረታት እንደሆኑ እንድታምን ሊያደርግህ ይችላል።

በረራን የተካኑና ልዩ የማየት ተሰጥዖ ያላቸው

ብዙዎቹ ሦስት አፅቄዎች ከፍተኛ የመብረር ችሎታ አላቸው። ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ ተመልከት። የወባ ትንኞች ተገልብጠው መብረር ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ በዝናብ ጠብታዎች መካከል እየተሽሎኮሎኩ ምንም ዝናብ ሳይነካቸው መብረር ይችላሉ! በሐሩር ክልል የሚገኙ አንዳንድ ተርቦችና ንቦች በሰዓት እስከ 72 ኪሎ ሜትር ይበርራሉ። ሞናርክ በተርፍላይ ተብለው የሚጠሩ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ቢራቢሮዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው በሚፈልሱበት ጊዜ 3, 010 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ። ሆቨር ፍላይስ ተብለው የሚጠሩት ዝንቦች ክንፎቻቸውን በሴኮንድ ውስጥ ከአንድ ሺህ ጊዜ በላይ ማርገብገብ ይችላሉ። ይህ ከሃሚንግበርድ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የላቀ ነው። ድራገንፍላይስ ተብለው የሚጠሩት ሦስት አፅቄዎች ወደ ኋላ መብረር የሚችሉ ሲሆን ይህም ተመራማሪዎች የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው ይበልጥ ጥልቅ ምርምር እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል።

አንድን ዝንብ ለመምታት ወይም ለመያዝ ሞክረህ የምታውቅ ከሆነ እነዚህ ሦስት አፅቄዎች እጅግ ልዩ የሆነ የማየት ችሎታ እንዳላቸው ሳትገነዘብ አልቀረህም። በዚህ ላይ ደግሞ በደመ ነፍስ ቅጽበታዊ ምላሽ በመስጠት ረገድ ያላቸው ችሎታ እኛ ካለን ችሎታ በአሥር እጥፍ ይበልጣል። ዝንቦች በሺህዎች የሚቆጠሩ ባለ ስድስት ጎን ሌንሶችን ያቀፈ ጥርቅምቅም ዓይን ያላቸው ሲሆን እያንዳንዱ ሌንስ ራሱን ችሎ ይሠራል። በመሆኑም የዝንቦች እይታ በጥቃቅኑ የተቆራረጠ ነው።

አንዳንድ ሦስት አፅቄዎች ሰዎች የማይታያቸውን ልእለሃምራዊ ብርሃን መመልከት ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ለእኛ ምንም የማትስብ ሆና የምትታየን ነጭ ቢራቢሮ ተባዕቱን ቢራቢሮ ትማርከዋለች። በእርግጥም እንስቷ በልእለሃምራዊ ብርሃን ስትታይ ተጣማጃቸውን በመፈለግ ላይ ያሉ ተባዕቶችን ትኩረት በእጅጉ የሚስቡ ማራኪ ንድፎች አሏት።

የብዙዎቹ ሦስት አፅቄዎች ዓይኖች እንደ ኮምፓስ ሆነው ያገለግላሉ። ለምሳሌ ያህል ንቦችና ተርቦች የባለ አንድ አቅጣጫ ብርሃንን ጠለል ማየት ስለሚችሉ ፀሐይ በደመና ተሸፍና ባለበት ወቅት እንኳ የት ቦታ ላይ እንዳለች መለየት ይችላሉ። እነዚህ ሦስት አፅቄዎች ይህ ችሎታ ያላቸው በመሆኑ ምግብ ፍለጋ ከጎጆአቸው ብዙ ርቀው ከሄዱም በኋላ ያላንዳች ስህተት ይመለሳሉ።

በፍቅር መልእክት የተሞላ አየር

በሦስት አፅቄዎች ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ ድምፅና ጠረን ተጣማጅ ለማግኘት መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። ዕድሜ በሳምንታት ብቻ በሚቆጠርበትና ተጣማጅ ሊሆኑ የሚችሉት ሦስት አፅቄዎች ጥቂት በሆኑበት ዓለም ውስጥ ይህ እንደ ቀላል የሚታይ ስኬት አይደለም።

እንስት የእሳት እራት ተጣማጅዋን የምታገኘው ከፍተኛ ኃይል ያለው ጠረን በማውጣት ሲሆን ተባዕቱ የእሳት እራት ወደ አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ከሚደርስ ርቀት ላይ ሆኖ ይህን ጠረን ሊለይና እንስቷ ወዳለችበት ሊመጣ ይችላል። ከፍተኛ የመለየት ችሎታ ያላቸው አንቴናዎቹ የጠረኑን አንዲት ነጠላ ሞሊኪውል መለየት ይችላሉ።

ዋዝንቢቶች፣ ፌንጣዎችና ሲኬዳ ተብለው የሚጠሩት ሦስት አፅቄዎች ድምፅ ማሰማት ይመርጣሉ። ሲኬዳዎች መላ ሰውነታቸውን ድምፅን ወደሚያስተጋባ መሣሪያነት በመለወጥ የፍቅር መልእክት ሲያስተጋቡ የሚያወጡትን ድምፅ እኛም እንኳ ልንሰማው እንችላለን። እንዲያውም ተጣማጃቸውን በመፈለግ ላይ ያሉ በርካታ ሲኬዳዎችን ያቀፈ አንድ ትልቅ ቡድን በአየር ግፊት ከሚሠራ መሰርሰሪያ የሚበልጥ ድምፅ ሊፈጥር ይችላል! በአንጻሩ አንዳንድ እንስቶች ደግሞ ምንም ድምፅ አያሰሙም።

ከእንቅልፍ ነቅቶ ሰውነትን ማሞቅ

ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ንብረት የሚኖሩ ሰዎች የሰውነታቸውን ሙቀት መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት በብርድ ተቆራምደው የሚነሱ ደመ ቀዝቃዛ ሦስት አፅቄዎችም ሁኔታ ልክ እንደዚሁ ነው። ፀሐይ ለዚህ ጥሩ አጋራቸው በመሆኗ አጋጣሚውን ሙሉ በሙሉ ይጠቀሙበታል።

ዝንቦችና ጢንዚዛዎች ገና በጠዋቱ የፀሐይን ሙቀት ወደሚመጡት አበቦች ወይም ቅጠሎች ይሰማራሉ። አንዳንዶቹ ጢንዚዛዎች አበቦቻቸውን ከአካባቢው የአየር ሙቀት በበለጠ እስከ 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ ማሞቅ የሚችሉትንና ስነ እፃዊ (botanical) ምድጃዎች ሆነው የሚያገለግሉትን ዎተር ሊሊ ተብለው የሚጠሩትን የአውስትራሊያ አበቦች ያዘወትራሉ። በአንጻሩ ደግሞ ቢራቢሮዎች የራሳቸው የሆነ ሰውነታቸውን የሚያሞቁበት ዘዴ አላቸው። ሰውነታቸውን ማሞቅ ሲፈልጉ በፀሐይ ኃይል እንደሚሠራ ጥሩ ባትሪ ሆነው የሚያገለግሉትን ክንፎቻቸውን ወደ ፀሐይ ይዘረጋሉ።

ሦስት አፅቄዎች የማይሠሩት ነገር የለም!

በሦስት አፅቄዎች ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ዝርያ ማለት ይቻላል የራሱ የሆነ ባሕርይ አለው። አንዳንዶቹ ሦስት አፅቄዎች ያላቸው ባሕርይ በጣም የሚያስገርም ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የእሳት እራቶች የጎሽን እንባ በመምጠጥ ሕይወት ሰጪ የሆነ ጨውና ተን ለማግኘት ይጥራሉ። ፀረ ቀረት (antifreeze) ኃይል ያላቸው ሌሎች ሦስት አፅቄዎች ደግሞ በረዷማ በሆኑ የተራራ ጫፎች ላይ በመኖር በቅዝቃዜው ያለቁ ትንንሽ ነፍሳትን በመለቃቀም ሕይወታቸውን ያቆያሉ።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት እንደገለጸው ጉንዳኖች በጣም ታታሪዎች ናቸው። ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንተ ታካች፣ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፣ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች።” (ምሳሌ 6:​6-8) አንዳንዱ የጉንዳን ጭፍራ እስከ 20 ሚልዮን የሚደርሱ ጉንዳኖችን ያቀፈ ሊሆን ስለሚችል ገዥ የሌላቸው መሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል! ሆኖም መላው የጉንዳኖች ጭፍራ ምግብ፣ ጥበቃና መኖሪያ ያገኝ ዘንድ እያንዳንዱ ጉንዳን የራሱን የሥራ ድርሻ የሚወጣ በመሆኑ ይህ የሦስት አፅቄ “ከተማ” ፍጹም ሥርዓት የሰፈነበት ነው።

ከሁሉ ይበልጥ አስደናቂ የሆነው የሦስት አፅቄዎች መኖሪያ የምስጦች ኩይሳ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንዶቹ ኩይሳዎች 7.5 ሜትር ከፍታ አላቸው። * እነዚህ ዕፁብ ድንቅ የግንባታ ሥራዎች ውስብስብ የሆነ የአየር ማቀዝቀዣ ዘዴና የምድር ውስጥ የፈንገስ የአትክልት ቦታዎች አሏቸው። ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህን ግዙፍ ፒራሚዶች የሚገነቡት ምስጦች ዓይነ ስውር መሆናቸው ነው!

ሦስት አፅቄዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

ሦስት አፅቄዎች በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እንዲያውም ከምንመገበው ምግብ 30 በመቶ የሚሆነውን ማግኘት የምንችልበት ሁኔታ የተመካው ንቦች በሚያከናውኑት ርክበብናኝ (pollination) ነው። ከእነዚህ ንቦች መካከል አብዛኞቹ የዱር ንቦች ናቸው። ይሁን እንጂ ሦስት አፅቄዎች የሚያከናውኑት ጠቃሚ ተግባር በርክበብናኝ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሦስት አፅቄዎች የበሰበሱና የሞቱ ዕፅዋትና እንስሳት ለየት ባለ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ በተዋጣለት የድግመ ኡደት ዘዴ ምድርን ያጸዳሉ። በዚህ መንገድ አፈሩ የሚዳብር ከመሆኑም በላይ የሚመነጩት ንጥረ ምግቦች ለዕፅዋት ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የስነ ሦስት አፅቄ ባለሞያ የሆኑት ክርስቶፈር ኦቱል ኤሊየን ኢምፓየር በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ሦስት አፅቄዎች ባይኖሩ ኖሮ በበሰበሱና በሞቱ ዕፅዋትና እንስሳት እንዋጥ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል።

ሦስት አፅቄዎች ተፈላጊነታቸው በእጅጉ የሚጎላው ሥራቸው ሳይሠራ በሚቀርበት ጊዜ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ከብቶች በሚገኙባት በአውስትራሊያ ምን ተከስቶ እንደነበር ተመልከት። የከብት መንጎች በየቦታው እበታቸውን ይጥላሉ። ፍጉ ለዓይን የሚያስቀይም ከመሆኑ በተጨማሪ ለሰውም ሆነ ለከብቶች መቅሠፍት ለሆነው የጫካ ዝንብ መራቢያ ሆነ። በመሆኑም የፍግ ጢንዚዛዎች ከአውሮፓና ከአፍሪካ እንዲመጡ ተደረገ። ችግሩ በዚህ መንገድ ተፈታ!

ወዳጆች ወይስ ጠላቶች?

አንዳንድ ሦስት አፅቄዎች ሰብሎችን እንደሚያጠፉና በሽታ ተሸካሚዎች እንደሆኑ የታወቀ ነው። ሆኖም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ሦስት አፅቄዎች መካከል እንደ ተባይ ተደርገው የሚቆጠሩት 1 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ የበለጠ ጉዳት የሚያደርሱት ሰው ራሱ ተፈጥሮን በማዛባቱ ምክንያት ነው። ለምሳሌ ያህል የወባ በሽታ ተሸካሚ የሆነችው ትንኝ በመሬት ሰቃዊ ጫካ የሚኖሩትን የአገሬው ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን እምብዛም አታስቸግራቸውም። ሆኖም በአንድ ቦታ ያቋረ ውኃ በብዛት በሚገኝባቸው የጫካው አዋሳኝ በሆኑ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችን በእጅጉ ታጠቃለች።

ብዙውን ጊዜ የሰው ልጅ አንድም ሰብሎችን እያቀያየረ በመዝራት አለዚያም ደግሞ የተፈጥሮ አዳኞችን በመጠቀም ወይም በመንከባከብ ሰብልን የሚያጠቁ ሦስት አፅቄ ተባዮችን መቆጣጠር ይችላል። ሌዲበግ ተብለው የሚጠሩት ተራዎቹ ጢንዚዛዎችና ሌስዊንግ ተብለው የሚጠሩት ሦስት አፅቄዎች የአፊድ ን ወረርሽኝ በተሳካ ሁኔታ ለመቆጣጠር ያስችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ የሕዝብ የጤና አገልግሎት ሠራተኞች ሁለት የድራገንፍላይ እጮች አንድን የውኃ ማጠራቀሚያ ከወባ ትንኝ እጮች ነፃ ማድረግ እንደሚችሉ ደርሰውበታል።

እንግዲያው ሦስት አፅቄዎች ሊያስከትሉት የሚችሉት ጉዳት ቢኖርም እንኳ ሕይወታችን በተመካበት ተፈጥሯዊ ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። ክርስቶፈር ኦቱል እንዳመለከቱት ሦስት አፅቄዎች ያለ እኛ መኖር የሚችሉ ሲሆን “እኛ ግን ያለ እነርሱ መኖር አንችልም።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 ይህ ከሰዎች አንፃር ሲታይ ከ9 ኪሎ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እንደ መሥራት ይቆጠራል።

[በገጽ 16 ,17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ልውጠተ ቅርጽ—አዲስ መልክ፣ አዲስ የአኗኗር ዘይቤ

አንዳንድ ሦስት አፅቄዎች ልውጠተ ቅርጽ በሚባል ሂደት አማካኝነት መልካቸውን ሙሉ በሙሉ ይለውጣሉ። ቃል በቃል “ቅርጻቸው ይለወጣል።” ለውጦቹ እጅግ አስደናቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ትሌ እጭ (maggot) ወደ ዝንብነት፣ አባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮነት እንዲሁም ውሃዊ እጭ ወደ አየር ወለድ ድራገንፍላይ ይለወጣሉ። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሦስት አፅቄዎች በልውጠተ ቅርጽ ሂደት ውስጥ ያልፋሉ።

ባቡርን ወደ አውሮፕላንነት ከመለወጥ ጋር ሊነጻጸር የሚችለውን ይህን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማድረግ በሦስት አፅቄው አካል ውስጥ ትልልቅ ለውጦች መካሄድ አለባቸው። ቢራቢሮን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አባጨጓሬው በሙሽሬነት (pupa) ደረጃ ላይ ባለበት ወቅት ምንም እንቅስቃሴ የማያደርግ ቢሆንም እንኳ ከቀድሞዎቹ ሕብረ ሕዋሳቱና አባላካላቱ መካከል አብዛኞቹ ይፈራርሱና በምትኩ እንደ ክንፎች፣ ዓይኖችና አንቴናዎች ያሉ አዳዲስ አባላካላት ያድጋሉ።

ብዙውን ጊዜ የለውጥ ሂደቱ አዲስ የአኗኗር ዘይቤንም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል ድራገንፍላይ በእጭ ደረጃ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ትንንሽ ዓሦችን ወይም እንቁሪዎችን (tadpoles) ይይዛል፤ በራሪ አካል ወደሚሆንበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን ሦስት አፅቄዎችን መመገብ ይጀምራል። ይህ ሁኔታ አንድ ሰው የሕይወቱን የመጀመሪያ 20 ዓመታት በባሕር በመዋኘት ካሳለፈ በኋላ ቀሪውን ሕይወቱን እንደ ወፍ በመብረር ያሳልፋል እንደ ማለት ይሆናል።

እነዚህ አስደናቂ የሆኑ የለውጥ ሂደቶች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሊከናወኑ ይችላሉ? አንድ አባጨጓሬ እንዲሁ ከምንም ተነስቶ እንዴት ራሱን ወደ ቢራቢሮነት መለወጥ ይችላል? መጀመሪያ የተገኘውስ የትኛው ነው? አባጨጓሬው ወይስ ቢራቢሮው? እንቁላሎቹን መፈልፈልም ሆነ መጣል የምትችለው ቢራቢሮዋ በመሆኗ አንዱ ያለሌላው ሊገኝ አይችልም።

በእርግጥም የልውጠተ ቅርጽ ሂደት መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉ ነገር ፈጣሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ብሎ የሚጠራው አንድ ታላቅ ንድፍ አውጪ እንዳለ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው።​—⁠መዝሙር 104:​24፤ ራእይ 4:​11

[ሥዕሎች]

ከሙሽሬው ገና የወጣ ስዋሎውቴል ክንፎቹን ሲዘረጋ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከላይ:- ወንዴ ዘር የሚመገብ ጢንዚዛ

ከላይ በስተቀኝ:- ቅጠላ ቅጠል የሚመገብ በጤዛ የተሸፈነ ጢንዚዛ ሰውነቱን ሲያሞቅ

በስተቀኝ ጥግ:- ራይኖሰርስ ቢትል ተብሎ የሚጠራው ጢንዚዛ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጭር አንቴና ያለው የአፍሪካ ፌንጣ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደም የሚመጥ ዝንብ