በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዘን ለደረሰባቸው የሚሆን እርዳታ

ሐዘን ምን ሊያስከትል ይችላል?

ሐዘን ምን ሊያስከትል ይችላል?

አንዳንድ ባለሙያዎች ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች፣ ደረጃ በደረጃ የተለያዩ ስሜቶች እንደሚፈጠሩባቸው ይናገራሉ፤ ያም ቢሆን እያንዳንዱ ግለሰብ ሐዘኑን የሚገልጽበት መንገድ ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም። ታዲያ ሰዎች የሚያዝኑበት መንገድ የሚለያይ መሆኑ አንዳንዶች ጥልቅ ሐዘን እንዳልተሰማቸው ወይም ስሜታቸውን “እያፈኑት” እንደሆነ የሚጠቁም ነው? ላይሆን ይችላል። ሐዘን የደረሰበት ግለሰብ፣ የሚወደው ሰው መሞቱን አምኖ መቀበሉና ሐዘኑን መግለጹ ለመጽናናት ሊረዳው ቢችልም ሐዘን የሚገለጽበት “ትክክለኛ” መንገድ አንድ ብቻ ነው ማለት ግን አይደለም። የአንድ ሰው ባሕል፣ ተፈጥሯዊ ባሕርይ፣ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ነገሮች እንዲሁም የሚወደው ሰው የሞተበት መንገድ ሐዘኑን በሚገልጽበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

ሐዘኑ ምን ያህል ሊከብድ ይችላል?

ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች የሚወዱትን ሰው ማጣታቸው ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥርባቸው እንደሚችል ግራ ይገባቸው ይሆናል። በእርግጥ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ አብዛኞቹ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎችና የሚፈጠሩባቸው ስሜቶች ተመሳሳይ ናቸው። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት፦

ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት። ማልቀስ፣ ሟቹን መናፈቅና ድንገተኛ የሆነ የስሜት መለዋወጥ ሊያጋጥም ይችላል። በተጨማሪም ሐዘን የደረሰበት ሰው ከሟቹ ጋር የተያያዙ ትዝታዎች ፊቱ ላይ ድቅን እያሉ ያስቸግሩት አሊያም ስለ ሟቹ የሚያያቸው ሕልሞች ይረብሹት ይሆናል። እርግጥ አንድ ሰው፣ የሚወደው ግለሰብ መሞቱን ሲያውቅ መጀመሪያ ላይ በድንጋጤ ይዋጥ እንዲሁም ነገሩን ለማመን ይቸገር ይሆናል። ቲና የተባለች ሴት፣ ባሏ ቲሞ በድንገት ሲሞት የተፈጠረባትን ስሜት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ደነዘዝኩ። ማልቀስ እንኳ አልቻልኩም። አንዳንድ ጊዜ ሐዘኑ ከአቅሜ በላይ ሲሆንብኝ መተንፈስ እንኳ ያቅተኝ ነበር። ነገሩን ማመን በጣም ከብዶኝ ነበር።”

ጭንቀት፣ ንዴትና የጥፋተኝነት ስሜትም የተለመደ ነው። አይቫን እንዲህ ብሏል፦ “ልጃችን ኤሪክ በ24 ዓመቱ ከሞተ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እኔና ባለቤቴ ዮላንዳ ብስጩ ሆነን ነበር! ቁጡ ሰዎች እንደሆንን ከዚያ በፊት አስበን ስለማናውቅ እንዲህ ያለ ባሕርይ ማሳየታችን አስገርሞናል። ‘ለልጃችን ሳናደርግ የቀረነው ነገር ይኖር ይሆን?’ የሚለው ሐሳብ ደግሞ በጥፋተኝነት ስሜት እንድንዋጥ አደረገን።” ባለቤቱ ለረጅም ጊዜ በሕመም ተሠቃይታ የሞተችበት አሌሃንድሮ የጥፋተኝነት ስሜት ይበጠብጠው ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ፣ ‘አምላክ ይህን ያህል እንድሠቃይ ከፈቀደ መጥፎ ሰው ነኝ ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ። ከዚያ ደግሞ ለደረሰው ነገር አምላክን ተወቃሽ እያደረግኩት እንደሆነ ስለተሰማኝ የጥፋተኝነት ስሜት አደረብኝ።” ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ኮስታስም እንዲህ ብሏል፦ “ሶፊያ በመሞቷ በእሷ ላይ የተናደድኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲህ በማሰቤ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። ሶፊያ፣ በመሞቷ ጨርሶ ተጠያቂ ልትሆን አትችልም።”

በትክክል ለማሰብ መቸገር። የሐዘንተኛው አስተሳሰብ ግራ የሚያጋባ ወይም ከትክክለኛው ወጣ ያለ የሚሆንባቸው ጊዜያትም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዘንተኛው የሟቹን ድምፅ እንደሰማ ወይም ሟቹን እንዳየው አድርጎ ሊያስብ ይችላል፤ አሊያም ሟቹ አጠገቡ ያለ ያህል ሆኖ እንደሚሰማው ይናገር ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሐዘንተኛው ሐሳቡን ለመሰብሰብ ወይም ነገሮችን ለማስታወስ ሊቸገር ይችላል። ቲና እንዲህ ትላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር እየተጫወትኩ ቢሆንም ከቀልቤ ላልሆን እችላለሁ! አእምሮዬ የሚያውጠነጥነው ከቲሞ አሟሟት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ነው። በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አለመቻሌ በራሱ ጭንቀት ይፈጥርብኛል።”

ራስን ማግለል። ሐዘን ላይ ያለ ሰው ከሌሎች ጋር ሲሆን ይነጫነጭ ይሆናል፤ አሊያም ከሰዎች ጋር መሆን ላይፈልግ ይችላል። ኮስታስ “ከባለትዳሮች ጋር ስሆን አለቦታዬ እንደገባሁ ይሰማኝ ነበር። ካላገቡ ሰዎች ጋር መሆንም ተመሳሳይ ስሜት ይፈጥርብኛል” ብሏል። የአይቫን ባለቤት ዮላንዳም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “እኛ ከደረሰብን ሐዘን ጋር ሲወዳደር ያን ያህል ከባድ በማይመስል ነገር ከሚያማርሩ ሰዎች ጋር መሆን በጣም አስቸጋሪ ነበር! አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ልጆቻቸው ስላገኙት ስኬት ይነግሩናል። ልጆቻቸው ስለተሳካላቸው ደስ ቢለኝም የሚነግሩኝን መስማቱ ግን ይረብሸኛል። እኔና ባለቤቴ ሕይወት እንደተለመደው እንደሚቀጥል ብናውቅም ከሌሎች ጋር እንዲህ ዓይነት ነገር ለማውራት ፍላጎቱም ሆነ ትዕግሥቱ አልነበረንም።”

የጤና ችግሮች። ብዙዎች የምግብ ፍላጎታቸውና ክብደታቸው ይቀንሳል እንዲሁም እንቅልፋቸው ይዛባል። አሮን አባቱ ከሞተ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ያጋጠመውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ እንቅልፍ ስለማይወስደኝ በጣም እቸገር ነበር። ሁልጊዜ የተወሰነ ሰዓት ላይ የምነቃ ሲሆን ስለ አባቴ ሞት እያሰብኩ እቆዝም ነበር።”

አሌሃንድሮ ደግሞ መንስኤው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሕመም ይሰማው እንደነበረ ያስታውሳል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጊዜ የተመረመርኩ ሲሆን ሐኪሙ ጤነኛ እንደሆንኩ አረጋግጦልኛል። ሕመም ይሰማኝ የነበረው በሐዘኑ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም።” ውሎ አድሮ የሕመሙ ምልክቶች እየጠፉ ሄዱ። ያም ቢሆን አሌሃንድሮ ሐኪም ቤት መሄዱ ጠቃሚ ነበር። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያዳክም፣ ቀድሞውንም የነበረ የጤና ችግርን ሊያባብስ አልፎ ተርፎም ሌላ ሕመም ሊያስከትል ይችላል።

አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ለማከናወን መቸገር። አይቫን እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ኤሪክ መሞቱን ለዘመዶቻችንና ለወዳጆቻችን ብቻ ሳይሆን ለአሠሪውና ለቤት አከራዩ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች መናገር ነበረብን። ከሕግ ጋር የተያያዙ በርካታ ሰነዶችንም መሙላት ያስፈልገን ነበር። ከዚያም የኤሪክን የግል ንብረቶች ቦታ ቦታ ማስያዝ ነበረብን። ይህ ሁሉ ትኩረት የሚጠይቅ ሲሆን እኛ ደግሞ በዚያ ወቅት አእምሯችንም ሆነ አካላችን ዝሎና ስሜታችን ተደቁሶ ነበር።”

አንዳንዶች ደግሞ የበለጠ ፈታኝ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው በኋላ ላይ ይኸውም ሟቹ ያከናውናቸው የነበሩትን ጉዳዮች ማከናወን በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ነው። ቲና ያጋጠማት ሁኔታ ይህ ነበር። እንዲህ ትላለች፦ “ከባንክ ጋር የተያያዙም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮቻችንን ምንጊዜም የሚከታተለው ቲሞ ነበር። አሁን ኃላፊነቱ ሁሉ እኔ ላይ ወደቀ፤ ይህም ይባስ እንድጨነቅ አደረገኝ። ‘ይህን ሁሉ ኃላፊነት በትክክል መወጣት እችላለሁ?’ የሚል ስጋት አደረብኝ።”

ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ያጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ ሐዘን የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም በጣም ከባድ እንዲመስል ሊያደርጉ ይችላሉ። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከባድ ሐዘን እንደሚያስከትል የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን በቅርቡ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ይህን አስቀድመው ማወቃቸው ሐዘናቸውን ለመቋቋም ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ሁሉም ሰው ከሐዘን ጋር ተያይዘው የሚመጡት ችግሮች በሙሉ ይደርሱበታል ማለት እንዳልሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። ከዚህም ሌላ በሐዘን የተደቆሱ ሰዎች፣ ሌሎችም የሚወዱትን ሰው ሲያጡ እንደ እነሱ ዓይነት ስሜት እንደተፈጠረባቸው ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል።

እንደገና ደስታ ማግኘት እችል ይሆን?

ምን መጠበቅ ትችላለህ? የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ግለሰብ መጀመሪያ ላይ የተሰማው መሪር ሐዘን እያደር እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው ከሐዘኑ ሙሉ በሙሉ ይጽናናል ወይም የሞተውን ሰው ይረሳዋል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ጊዜ ባለፈ መጠን ሐዘኑ እየቀለለው ይሄዳል። በእርግጥ አንዳንድ ትዝታዎች ወደ አእምሮው ሲመጡ አሊያም ደግሞ እንደ ሠርጋቸው ቀን ባሉት ጊዜያት ሐዘኑ ያገረሽበት ይሆናል። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ስሜታቸው ቀስ በቀስ እየተረጋጋ ስለሚሄድ እንደ ቀድሞው በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ይጠመዳሉ። በተለይ ደግሞ የሐዘንተኛው ቤተሰብ ወይም ጓደኞቹ ግለሰቡን የሚደግፉት ከሆነና እሱም አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎችን ከወሰደ ሐዘኑን መቋቋም ይችላል።

ከሐዘን ለመጽናናት ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? አንዳንዶች ሐዘኑ በጣም የሚከብዳቸው ለተወሰኑ ወራት ሊሆን ይችላል። ሌሎች ብዙ ሰዎች ደግሞ ሐዘናቸው ቀለል እያለላቸው እንደሆነ የሚሰማቸው ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ግን ከዚህም የበለጠ ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። * አሌሃንድሮ “ለሦስት ዓመት ያህል ሐዘኑ በጣም ከብዶኝ ነበር” ብሏል።

ትዕግሥተኛ ሁን። ነገ የሚሆነውን እያሰብክ አትጨነቅ፤ ከሐዘንህ ለመጽናናት የሚወስድብህን ጊዜ ከሌሎች ጋር አታወዳድር፤ እንዲሁም መሪር ሐዘን በጊዜ ሂደት እየቀለለ እንደሚሄድ አስታውስ። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሐዘንህን ለማቅለል ብሎም ሳያስፈልግ እንዳይራዘም ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች ይኖራሉ?

ብዙዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው መሪር ሐዘን ያስከትልባቸዋል

^ አን.17 አንዳንዶች ሐዘናቸው በጣም ሊጸናባቸውና ከሐዘኑ መላቀቅ ሊቸግራቸው ይችላል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች የአእምሮ ጤና ባለሙያ እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።