ማቴዎስ 20:1-34

20  “ምክንያቱም መንግሥተ ሰማያት በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ ከወጣ የእርሻ ባለቤት ጋር ይመሳሰላል።  በቀን አንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከሠራተኞቹ ጋር ከተዋዋለ በኋላ ወደ ወይን እርሻው ላካቸው።  በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤  እነዚህንም ሰዎች ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ፤ ተገቢውንም ክፍያ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው።  እነሱም ሄዱ። ዳግመኛም በስድስት ሰዓት እንዲሁም በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ።  በመጨረሻም በአሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው።  እነሱም ‘የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው’ አሉት። እሱም ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ’ አላቸው።  “በመሸም ጊዜ የወይኑ እርሻ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ‘ሠራተኞቹን ጠርተህ በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በመጀመሪያ እስከተቀጠሩት ድረስ ደሞዛቸውን ክፈላቸው’ አለው።  በአሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ሰዎች መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10  በመሆኑም በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲመጡ እነሱ የበለጠ የሚከፈላቸው መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሱም የተከፈላቸው አንድ አንድ ዲናር ነበር። 11  ክፍያውን ሲቀበሉ በእርሻው ባለቤት ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ 12  ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ነው የሠሩት፤ እንደዚያም ሆኖ ግን አንተ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንቃጠል ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው!’ አሉት። 13  ይሁን እንጂ የወይኑ እርሻ ባለቤት ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው:- ‘የኔ ወንድም፣ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ? 14  ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ። በመጨረሻ ለተቀጠረው ለዚህ ሰውም ለአንተ የሰጠሁትን ያህል መስጠት ፈለግሁ። 15  በገዛ ገንዘቤ የፈለግሁትን የማድረግ መብት የለኝም? ወይስ እኔ ደግ በመሆኔ ዓይንህ ተመቀኘ?’* 16  ስለሆነም ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ይሆናሉ።” 17  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ተነስቶ ሳለ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ነጥሎ ወሰዳቸው፤ በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ አላቸው:- 18  “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዝን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል፤ እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ 19  እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።” 20  ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋር ወደ እሱ ቀርባ እየሰገደች አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። 21  እሱም “ምንድን ነው የፈለግሽው?” አላት። እሷም “በመንግሥትህ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ፣ አንዱ በቀኝህ አንዱ ደግሞ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው። 22  ኢየሱስም መልሶ “እናንተ ሰዎች የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ በቅርቡ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁ?” አላቸው። እነሱም “እንችላለን” አሉት። 23  እሱም “በእርግጥ የእኔን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ በቀኜ ወይም በግራዬ የመቀመጡ ጉዳይ ግን አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” አላቸው። 24  የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ተቆጡ። 25  ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠራቸውና እንዲህ አላቸው:- “የአሕዛብ ገዥዎች በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። 26  በእናንተ መካከል እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ግን አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባዋል፤ 27  እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባዋል። 28  የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” 29  ከዚህ በኋላ ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ ሳሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 30  በዚህ ጊዜ በመንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዓይነ ስውሮች ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ጮኹ። 31  ሆኖም ሕዝቡ ዝም እንዲሉ ገሠጿቸው፤ እነሱ ግን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ይበልጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። 32  ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33  እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይኖቻችን እንዲያዩ አድርግልን” አሉት። 34  ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑም ማየት ቻሉ፤ ከዚያም ተከተሉት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማቴ 20:15 * ቃል በቃል፣ “ዓይንህ ክፉ ሆነ።”