በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 85

ኢየሱስ ጋጣ ውስጥ ተወለደ

ኢየሱስ ጋጣ ውስጥ ተወለደ

ይህ ትንሽ ሕፃን ማን እንደሆነ ታውቃለህ? አዎ፣ ኢየሱስ ነው። ጋጣ ውስጥ ገና መወለዱ ነው። ጋጣ እንስሳት የሚያድሩበት ቦታ ነው። ማርያም ኢየሱስን አህዮችና ሌሎች እንስሳት ምግብ በሚመገቡበት ግርግም ውስጥ አስተኛችው። ይሁን እንጂ ማርያምና ዮሴፍ እዚህ እንስሳቱ ጋር ምን ያደርጋሉ? ይህ ሕፃን የሚወለድበት ቦታ አይደለም፤ ነው እንዴ?

በፍጹም አይደለም። እዚህ ቦታ ሊመጡ የቻሉበት ምክንያት ግን የሚከተለው ነው:- የሮም ገዥ የሆነው አውግስጦስ ቄሣር እያንዳንዱ ሰው ስሙ በመዝገብ እንዲጻፍ ወደ ተወለደበት ከተማ እንዲመለስ የሚያዝ አዋጅ አወጣ። ዮሴፍ የተወለደው በዚህ በቤተ ልሔም ከተማ ነበር። ይሁን እንጂ እሱና ማርያም ወደዚች ከተማ ሲደርሱ የሚያርፉበት ክፍል ማግኘት አልቻሉም። ስለዚህ ከእንስሳቱ ጋር በዚህ ቦታ ለማረፍ ተገደዱ። በዚያው ቀን ማርያም ኢየሱስን ወለደች! ሆኖም ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ኢየሱስ ሙሉ ጤናማ ነበር።

ኢየሱስን ለማየት እየመጡ ያሉት እረኞች ይታዩሃል? ሌሊት በሜዳ ላይ ሆነው በጎቻቸውን እየጠበቁ ነበር። አንድ ደማቅ ብርሃን በዙሪያቸው በራ። መልአክ ነበር! እረኞቹ በጣም ፈሩ። ሆኖም መልአኩ ‘አትፍሩ! የምሥራች እነግራችኋለሁ። ዛሬ፣ በቤተ ልሔም ጌታ ክርስቶስ ተወልዷል። እርሱ ሕዝቡን ያድናል! በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኙታላችሁ’ አላቸው። በድንገት ብዙ መላእክት መጡና አምላክን ማመስገን ጀመሩ። ስለዚህ ወዲያውኑ እነዚህ እረኞች ኢየሱስን ለማየት በፍጥነት ሄዱና አገኙት።

ኢየሱስን በጣም ለየት ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? በእርግጥ ኢየሱስ ማን እንደሆነ ታውቃለህ? በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ታሪክ ላይ ስለ አምላክ የመጀመሪያ ልጅ እንደተማርን አስታውስ። ይህ ልጅ ሰማያትን፣ ምድርንና የተቀሩትን ነገሮች በሙሉ ከይሖዋ ጋር ሆኖ ሠርቷል። ኢየሱስ ማለት እርሱ ነው!

አዎ፣ ይሖዋ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወስዶ በማርያም ማኅፀን ውስጥ አስቀመጠው። ወዲያውኑ፣ ሌሎች ሕፃናት በእናቶቻቸው ማኅፀን ውስጥ እንደሚያድጉ ሁሉ በማርያም ማኅፀን ውስጥም አንድ ሕፃን ማደግ ጀመረ። ይሁን እንጂ ይህ ሕፃን የአምላክ ልጅ ነበር። በመጨረሻ ኢየሱስ በቤተ ልሔም በዚህ ጋጣ ውስጥ ተወለደ። መላእክቱ ኢየሱስ መወለዱን ለሰዎች መንገር በመቻላቸው በጣም የተደሰቱት ለምን እንደሆነ አሁን ግልጽ ሆነ⁠ልህ?